Logo
EBC
የእጥፋት ዘመን፡ የኢትዮጵያ መጪው አምስት ዓመታት
***************

( የዕለቱ መልዕክት)

በታሪካዊ እጥፋቶችና ስር በሰደዱ መዋቅራዊ ማነቆዎች ውስጥ ስትመላለስ የኖረችው ኢትዮጵያ ዛሬ ላይ ከትናንት የዳተኝነት ቀንበር ተላቃ ወደ ላቀ ምዕራፍ ለመሻገር የሚያስችላትን ታሪካዊ መሠረት ጥላለች። የሀገራችን የልማትና የለውጥ ጉዞ በመጀመሪያው ምዕራፍ ላይ የጥርጣሬና የፈተና ድንጋዮች ቢወረወሩበትም ዛሬ ግን ኢትዮጵያ በፈጣን እና መዋቅራዊ የኢኮኖሚ ሽግግር ሂደት ውስጥ ትገኛለች።

ለብዙ አስርት ዓመታት የኢኮኖሚው የጀርባ አጥንት ሆኖ የቆየውን ባህላዊ የግብርና መር ሞዴል ወደ ላቀ የኢንዱስትሪ፣ የቴክኖሎጂ እና የአገልግሎት ዘርፍ ለማሸጋገር የተነደፉት ግዙፍና ሁለንተናዊ የልማት ፕሮጀክቶች መሬት በመያዝ ላይ ናቸው።

ይህ ስልታዊ እርምጃ ተራ የድንጋይና የኮንክሪት ክምችት ሳይሆን የኢትዮጵያን የረጅም ጊዜ የኢኮኖሚ ሉዓላዊነት ለማረጋገጥ ስር የሰደደውን የንግድ ሚዛን መዛባት ለመቅረፍ እና የዜጎችን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ለማስፈን የታለመ የሉዓላዊነት ማህተም ነው።

ኢትዮጵያ በአፍሪካ በሕዝብ ብዛት በሁለተኛ ደረጃ ላይ ያለች ብትሆንም የኢኮኖሚ ዕድገቷን የገደቡ ሦስት ዋና ዋና መዋቅራዊ እጥረቶች ነበሩባት። የመጀመሪያው ወደ ውጭ ከምትልካቸው ጥሬ የግብርና ምርቶች የምታገኘው ገቢና ለውጭ መሠረታዊ ቁሳቁሶች የምታወጣው ወጪ አለመመጣጠን የወለደው የንግድ ሚዛን መዛባት እና የውጭ ምንዛሬ እጥረት ነው።

ሁለተኛው ብሔራዊ የምግብ ዋስትናን ሁልጊዜም ለአደጋ የሚያጋልጠውና በየዓመቱ ከዓለም አቀፍ ገበያ በሚመጣ ማዳበሪያ ላይ የተንጠለጠለው የግብርና ዘርፍ የውጭ ጥገኝነት ነው።

ሦስተኛውና ታሪካዊው ተግዳሮት ደግሞ የባህር በር ማጣት ያስከተለው የሎጂስቲክስ ጫና እና ከአንድ የጅቡቲ ወደብ ኮሪደር ጋር ብቻ መተሳሰር የፈጠረው የብሔራዊ ደህንነት ስጋት ነው። እነዚህን ስር የሰደዱ ችግሮች ለመቅረፍ ባለፉት ዓመታት በተለይም በግብርናው ዘርፍ የበጋ ስንዴ ምርታማነትን በማሳደግ ከውጪ አስመጪነት ወደ ላኪነት የተደረገው ሽግግር፣ “የማይሞቅ ፍም አይነድም፣ የማይሆን ነገር አይሆንም” የሚሉትን የጥርጣሬ ድምፆች በተግባር ያፈረሰ ተምሳሌታዊ ስኬት ሆኗል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ ድምፅ ከሰጡ በኋላ እንዳመለከቱት መጪው አምስት ዓመት የኢትዮጵያ በርካታ የታሪክ እጥፋት የሚታይበት ዘመን ነው።

"የትናንትናዋን ኢትዮጵያ በሚቀጥለው አምስት ዓመት አናያትም። የተቀየረች፣ የተለወጠች፣ ቢያንስ የማትለምን፣ ራሷን ችላ የምትቆም፣ በቀጠናው መልህቅ የሆነች አገር ለማየት ብዙ ልፋት ይፈልጋል" ማለታቸው የዚህን ሽግግር ጥልቀትና የሚጠይቀውን ብሔራዊ ቁርጠኝነት ያሳያል።

በመሆኑም መጪው አምስት ዓመት የምክንያትና የውጤት ትስስር የሚታይበት፣ ባለፉት ዓመታት የተጀመሩት ስልታዊና ትላልቅ ስራዎች ፍሬ የሚያፈሩበት ወርቃማ ምዕራፍ ይሆናል።

በዚህም መሠረት በኃይልና ታዳሽ ኢነርጂ ዘርፍ እንደ የኮይሻ ሃይድሮ-ኤሌክትሪክ ያሉ ግዙፍ ፕሮጀክቶችን ማጠናቀቅ ኢትዮጵያን የቀጠናዉ የኃይል ማማ ከማድረግ ባለፈ ለኢንዱስትሪ መስፋፋት አስተማማኝና ርካሽ ግብዓት ይፈጥራል።

በፔትሮ-ኬሚካልና ማምረቻ ዘርፍ የኦጋዴን የተፈጥሮ ጋዝና የሀገር ውስጥ የማዳበሪያ ፋብሪካ ስራ መጀመር የግብርናውን ዘርፍ ከውጭ ጥገኝነት በማላቀቅ የውጭ ምንዛሬን በከፍተኛ ሁኔታ ይታደጋል። በአቪዬሽንና ግሎባል ትራንስፖርት ዘርፍ አዲሱ የቢሾፍቱ ሜጋ አየር ማረፊያ ግንባታ ኢትዮጵያን የአፍሪካ ቁልፍ የሎጂስቲክስና የትራንዚት ማእከልነቷን ያጠናክራል።

በከተማ ውበትና የቦታ ልማት ኢኮኖሚ ረገድ ደግሞ የአዲስ አበባ የኮሪደር ልማትና የገበታ ለትዉልድ ፕሮጀክቶች ከተሞችን የቱሪስት መዳረሻና የኢኮኖሚ መፈልፈያ ማዕከል በማድረግ ረገድ ያላቸው ፋይዳ የጎላ ነው።

ይህንን ታላቅ አህጉራዊ ተስፋ እውን ለማድረግና ኢትዮጵያን በቀይ ባህርና በአፍሪካ ቀንድ አካባቢ ድምፅዋ ጎልቶ የሚሰማ ግዙፍ የአፍሪካ ኃያል ሀገር ለማድረግ የሚቻለው ቀጣናዊና ሀገራዊ የቤት ስራዎችን በብልሃት መወጣት ሲቻል ነው።

በመሆኑም መዋቅራዊ ሽግግሩን በስኬት ለማጠናቀቅ የሀገር ውስጥ ሰላምና ጸጥታን በአስተማማኝ ሁኔታ ማስቀጠል፣ የማክሮኢኮኖሚ መረጋጋትን መፍጠር፣ የዋጋ ንረትን መቆጣጠር እና የፋይናንስ አቅርቦቶችን የበለጠ ማሻሻል ድርድር የማይገባባቸው ቅድመ ሁኔታዎች ናቸው።

ኢትዮጵያ ያላትን ስትራቴጂካዊና ጂኦ-ፖለቲካዊ አቀማመጥ እና የተፈጥሮ ፀጋ በአግባቡ ከተጠቀመች መጪው አምስት ዓመት የልመና ታሪኳ የሚያበቃበት ራሷን ችላ የምትቆምበት እና የበለፀገች ሀገር የመሆን ጉዞዋ በተጨባጭ የሚረጋገጥበት ዘመን እንደሚሆን አያጠራጥርም።

የኢቢሲ ዶትስትሪም ኤዲቶሪያል

Ethiopian Broadcasting Corporation #dot #ebc

3 hours ago

No replys yet!

Be the first to share what you think — your comment will appear here.