Logo
FBC
ሰላም፣ ደህና አደራችሁ?

የስልጣን ምንጭ እና ባለቤት….

ኢትዮጵያ ሰባተኛውን ጠቅላላ ምርጫ ግንቦት 24 ቀን 2018 ዓ.ም በተሳካ ሁኔታ አካሂዳለች። በዕለቱ ህዝቡ በነቂስ ወጥቶ በነፃነት ይወክለኛል የሚለውን በመምረጥ፤ የኃይል አማራጭን ለተከተሉት ጆሮ ባለመስጠት ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት መጎለበት ያለውን ውግንና አሳይቷል፡፡

በቅድመ ምርጫ ወቅት መራጩ የተፎካካሪ አካላትን ፖሊሲ፣ ስትራቴጂ እና እሳቤዎች በሚገባ ሲከታተል ቆይቷል፡፡ ሲያሰላስል ቆይቶም በምርጫው ዕለት ይወክለኛል የሚለውን በምስጢር በካርዱ ወስኗል፡፡ አሁን የምርጫውን ውጤት በመጠባበቅ ላይ ይገኛል፡፡ ይህ ዴሞክራሲያዊ እሳቤ ነው፡፡

የኢትዮጵያ ህዝብ ብዙ የትግል ታሪኮችን አሳልፏል፡፡ ረዥም የሰላምና የልማት መንገድ የሚያስኬደውን አቅሙንም በዚሁ ውስብስብ ሂደት ሲያጣ ኖሯል፡፡ የዘንድሮው ሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ ህዝቡ ከኃይል ይልቅ ሰላምን፣ ከጠብመንጃ ይልቅ የምርጫ ካርድን እንደሚመርጥ በግልጽ አስመስክሯል፡፡ ይህ ለምርጫ ያለው ቦታ እያደገ መምጣቱን ያሳየ ነው፡፡ ለዚያም ነው ብርድ፣ ዝናብ፣ ፀሐይ፣ ህመም፣ ኀዘን፣ ሙቀት፣ እርጅና እና ማስፈራሪያ ሳይገድበው ወጥቶ ድምጹን ይወክለኛል ለሚለውና ለሚሻው የሰጠው፡፡

እኔ አውቅልሀለሁ ለሚሉት፣ አይዞን እኔ ለራሴ አውቃለሁ ብሏል፡፡ ይህ የህልውና ጉዳይ ነው፡፡ የዴሞክራሲ ጥማት፡፡ የጥይት አረር በቃኝ ያለበት ውሳኔ፡፡

ሂደቱን ለማደናቀፍ ግዝትና ግዞት ቢኖርም በዕለቱ ኢትዮጵያውያን በሀገራቸው የወደፊት ዕጣ ፈንታ ላይ በቀጥታ በመወሰን በየትኛውም ቦታ ይወክለኛል ላሉት ተመራጭ ድምጻቸውን ሰጥተዋል፡፡ በዚህ ሂደት የስልጣን ምንጭ እና ባለቤትነታቸውንም አረጋግጠዋል፡፡

ይህንንም ያደረጉት ዴሞክራሲ ህዝብ - በህዝብ - ለህዝብ የሚመራበት ስርዓት ስለሆነ ነው፡፡ በዚህም ስለራሳቸው ጉዳይ ከባዳ ባእድ በማምጣት ሳይሆን፣ ራሳቸው በራሳቸው ጉዳይ የወሰኑበት ነው፡፡ ዝም ብሎ ለታዘበ ሰው ኢትዮጵያውያን ምርጫ፣ ዜጎች በሀገሪቱ ፖለቲካዊ እና አስተዳደራዊ ውሳኔዎች ላይ በቀጥታ የሚሳተፉበት ዋና መድረክ እንደሆነ እንደገባቸው ይረዳል፡፡ የስልጣን ምንጭ እና ባለቤት እንደሆነም እንዲሁ፡፡ ለዚህም ነው ከአዋካቢዎች ይልቅ በእርጋታ በካርዳቸው የሚወክላቸውን ለመምረጥ የወሰኑት፡፡

ምርጫ ለኢትዮጵያውያን የይስሙላና የቅንጦት አይደለም፡፡ የህልውና ጉዳይ ነው፡፡ የስልጣን ውክልናቸውን የሚያስተላልፉበት መንገድ፡፡ ይህም ነባሩን የኃይል ልማድ ገርስሶ፣ ዴሞክራሲያዊ እሳቤው ሚዛን መድፋቱን ያሳያል፡፡ በምርጫ ድምፅ ተጠቅሞ ውክልናና ስልጣን የሚሰጥበት እና የሚነሳበት መሆኑ ፍንትው ብሎ ታይቶታል፡፡

በምርጫ ወቅት የታየውን የህዝብ መሻት የገባው ተመራጭ እንደ መራጩ ጨዋ ሆኖ ቃሉን ይጠብቃል፡፡ ህዝቡም ትወክለኛለህ ብሎ በድምጹ ስልጣን የሰጠውን አካል፣ ምን ሰራህልኝ ብሎም ይጠይቃል፡፡ ምርጫ ተጠያቂነትን ያረጋግጣል ማለት ነው፡፡ ህዝቡ በስልጣን ላይ ያሉ መሪዎችን ስራ የሚገመግምበት እና ካላገለገሉት በጠብ መንጃ ሳይሆን ምርጫ ሲካሄድ ጠብቆ በሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ መንገድ በካርዱ ይቀጣቸዋል፡፡

የተመራጭ ኃላፊነት ላልመረጠውም ነው፡፡ በዕለቱ እድሜው የደረሰ ዜጋ ያለ ምንም ልዩነት የመምረጥ እና የመመረጥ መብቱን ተጠቅሞ መርጧል፡፡ ያልመረጠውና ድምጹን ለተሸናፊ የሰጠም፣ ዜጋ ስለሆነ እኩል መስተናገድን ይሻል፤ መብቱም ነው፡፡ ቀጣይም ምርጫ አለና፡፡

የዘንድሮው ምርጫ ሂደቱ ትክክለኛ እንደነበር በርካቶች መስክረውለታል፡፡ የምርጫ አስፈጻሚው አካልም ገለልተኛ እና ግልጽ አሰራር ያለው ስለመሆኑ የአፍሪካ ሕብረት፣ የኢጋድና የሀገር ውስጥ የምርጫ ታዛቢዎች መስክረውለታል፡፡ታዛቢዎቹ ምርጫ ቦርድ ገለልተኛነቱን በቅድመ ምርጫና በምርጫ ዕለት ሥራዎች አስመስክሯል ብለዋል፡፡ ቦርዱ ይህንኑ በማጠናከር አሁንም የድህረ ምርጫ ስራዎችን እየሠራ ይገኛል፡፡

ህዝቡ ዴሞክራሲያዊ መንገድ መሻቱን ካርድ በማውጣት፣ በነቂስ ወጥቶ በመምረጥ አሳይቷል፡፡ ይህ የስልጡንነት መገለጫ ነው፡፡ ሰላማዊ የስልጣን ሽግግር እንዲካሄድ በድምፁ ስለወሰነ፡፡ በዚሁ መሠረት የሚመረጠው አካል ከባድ የቤት ሥራ ይጠብቀዋል፡፡ የልማት፣ የሕግ የበላይነት፣ ሰላምና ደህንነትን የማስፈን፣ አገልግሎት አሰጣጥን ማዘመን፣ ዴሞክራሲያዊ እና ሰብዓዊ መብቶችን ማክበርና ማስከበር፣ ሉዓላዊነት፣ ብሔራዊ ክብር፣ ሀገራዊ አንድነት፣ ብቻ ብዙ ብዙ፡፡

እናማ መራጩ የድርሻውን ከተወጣ፣ ተመራጩ የሚሰጠውን ህጋዊ ውክልና መወጣቱ የግድ ነው፡፡ ውክልናው በየአምስት ዓመቱ የሚታደስ ኮንትራት በመሆኑ፣ ተመራጭ በቅድመ ምርጫ ወቅት በየሚዲያው ቃል የገባውን ሁሉ ህዝቡ ቆጥሮ ይዟል፡፡ አሸናፊነቱ በምርጫ ቦርድ ይፋ ሲደረግና መንግሥት ሲመሠርትም ገና የሚገባው መሀላ አለ፤ ህዝቡ ይህንንም ይከትባል፡፡ቃል የሚገባውም ድምጽ ለሰጠው ብቻ ሳይሆን ላልመረጠውም ነው፡፡ በቀጣይ ልቡን ለመግዛት፡፡ ተመራጩ ቃሉን ከጠበቀ ህዝቡ የስልጣን ምንጭና ባለቤት ስለሆነ የአምስት ዓመት ኮንትራቱን ያድስለታል፡፡ ቃላባይ ከሆነ ግን የካበተ ባህል፣ ታሪክ፣ ፍልስፍናና ጥብቅ ማህበራዊ እሴት ያለው ሰላምና ዴሞክራሲ መወዳዱ ህዝብ በሰላማዊ መንገድ ይወስናል፡፡ ስለዚህ ወደ ስልጣን የሚያደርሰውም የሚመልሰውም መንገድ ቃልን መጠበቅና ምርጫ ብቻ ነው ማለት ነው፡፡

መችም በዘንድሮው ምርጫ ካርድ ወስዶ ምንም ሳያሰናክለው በነቂስ ወጥቶ የመረጠውን ህዝብ ያየና የሰማ ሌላ መንገድ አያስብም፡፡ ወጥቶ ጢሻ ያለውም ቢመለስ፤ ያሰበም ካለ የህዝቡን ስነልቦና የበላይነት ቢረዳ ይበጀዋል፡፡ ምክንያቱም ሥልጣን ለመያዝ ህዝብን ማሳመንና በካርድ መመረጥ ብቻ በቂ ስለሆነ፡፡ የስልጣን ምንጭ እና ባለቤት፣ ሰጪም ነሺም ህዝብ ነውና፡፡

ኑ ሀገር እንሥራ!

8 hours ago

No replys yet!

Be the first to share what you think — your comment will appear here.