(ዘ-ሐበሻ ነቆራ) በቋንቋችን ውስጥ መዝገበ-ቃላት እና እውነታ ሁሌም የድመትና አይጥ ጸብ አላቸው። ለምሳሌ "ጉቦ" የሚለውን ቃል ብትወስድ፣ ቃሉ ራሱ ሲጠራ ልክ እንደ ደረቅ ሳል ጆሮ ይጎረብጣል። ስለዚህ ዘመናዊዎቹ የኪስ ጠላፊዎች፣ ለጆሮ እንዲጥም "የማበረታቻ ሽልማት"፣ "የእጅ መንሻ" ወይም "የፍቅር ስጦታ" እያሉ አቆላምጠውታል። ሙስና በሀገራችን ስሟን እንደቀየረች ኮከብ ዘፋኝ አዲስ ገጽታ ተላብሳለች።
ሰሞኑን ታዲያ አንዱ ስማቸውን ለጊዜው የማልጠቅስላችሁ ባለሀብት አንድ ባለስልጣን ቢሮ ብቅ ይላሉ። አረማመዳቸው ራሱ "ጨረታ ስጠኝ" የሚል ዜማ አለው። እጃቸውን ደረታቸው ላይ አጣምረው፣ አንገታቸውን እንደ ጤፍ ዛላ ሰብረው፣ የጂ-ፕላስ-ስሪ ቪላ ቁልፍ ከነሙሉ እቃው፣ ለክቡር ሚኒስትሩ አቀረቡ።
ሚኒስትሩ የህዝብ ብሶት ከረባት አድርጎ ያነቃቸው ይመስል፣ ፊታቸውን እንደ ጦርነት ዋዜማ አኮሳትረው.. “ይሄ ምንድነው አንተ ሰው?” ብለው በቁጣ ጠየቁ።
ባለሃብቱም የቃላት ዶክተር ናቸውና፣ ድምፃቸውን እንደ ማታ ራዲዮ አሳምረው እንዲህ አሉ.. “ክቡር ሚኒስትር... የህዝቡ አደራ ጫንቃዎ ላይ ሲወጣ ሲወርድ አከርካሪዎን እንዳይጎዳው፣ እንዲሁም የሀገሪቱ ጉዳይ ሀሳብ ሲያበዛብዎት፣ ከከተማው ትርምስ ራቅ ብለው ንጹህ አየር የሚቀበሉባት... አንዲት ጠባብ ባለ ሶስት ፎቅ የሳር ጎጆ አዘጋጅቼልዎት ነው።”
ባለስልጣኑ የቁልፉን ብረት በስሱ እያሻሹ፣ ግን ደግሞ ቅሬታ እንደገባው ሰው አሁንም ፊታቸው አልተፈታም፡-
“አይ እናንተ ባለሃብቶች... ህዝብ እኮ አይን አለው! ፀረ-ሙስና የሚባል የጨጓራ በሽታስ ዝም ይላል? ደግሞ ጂ ፕላስ ስሪ መቼ ወዲህ ነው ጎጆ የሆነው? ይሄ እኮ ከባድ ሙስና ነው!”
ባለሃብቱ ግን መቼ ይደናገጣሉ? ቃላትን በወንፊት እያነጠሩ መለሱ፡-
“ለእርስዎ ትልቅነትማ ባለ ሶስት ፎቅ ቪላም ጎጆ እንጂ ምንድነው ጌታዬ! ደግሞም እኮ ይሄን የገዛሁት ለእርስዎ ብዬ አይደለም። እርስዎ ሲደክምዎት ውሳኔ እንዳይዛባብዎት፣ እረፍት አግኝተው ለህዝቡ የተሻለ ስራ እንዲሰሩ በማሰብ... ለህዝቡ ስል የገዛሁት 'የህዝብ ቤት' ነው። እርሶ በህዝብ ስም ይረፉበት ብዬ ነው።”
ይሄን ጊዜ በሚኒስትሩ ፊት ላይ የነበረው ደመና በአንድ ጊዜ ተገፎ በፀደይ ፀሀይ ተተካ። ቁልፉን ወደ ኪሳቸው እያሸረተቱ፣ “እህህ... አየህ አንተ ሰው፣ ለህዝቡ ጥቅም ከሆነማ... እኔ ማነኝና የህዝብን ስጦታ እመልሳለሁ? የህዝብን አደራ አለመቀበል እኮ ትዕቢት ነው!” ብለው የህዝቡን ቪላ፣ በህዝቡ ስም፣ በራሳቸው ካርታ አዙረውታል። በሀገራችን "ሌብነት" እና "ብልህነት" አንድ አባትና እናት እንዳላቸው መንታ ልጆች ናቸው፤ የሚለዩት በለበሱት የሹመት ካፖርት ብቻ ነው!
በማግስቱ ታዲያ ነገሮች እንደ ጃፓን ባቡር ፈጠኑ። የሚኒስትሩ መሥሪያ ቤት ያወጣው የብዙ መቶ ሚሊዮን ብር ግዙፍ ፕሮጀክት የጨረታ ውጤት ሲለጠፍ፣ አሸናፊው ሩቅ አልነበረም። ያው "የህዝቡን ቪላ" አበርካች፣ የዘመናችን ሩህሩህ ቱጃር ሆነው እርፍ አሉ!
ይሄን ጊዜ ሌሎቹ ተጫራቾች… ማለትም ጨረታ በወረቀት፣ በማህተምና በፊርማ ብቻ የሚሸነፍ የሚመስላቸው የዋሃን ነጋዴዎች… አንጀታቸው አረረ። “እንዴት እርሳቸው ያሸንፋሉ? የእኛ ዋጋ እኮ በጣም አነስተኛ ነበር! የቴክኒክ ሰነዳችንም ቢሆን ከአውሮፓ ስታንዳርድ የሚስተካከል ነበር!” በማለት የጨረታ ኮሚቴውን አፍጠው ጠየቁ።
ኮሚቴው መልስ ቢያጣ፣ ጉዳዩ ወደ ክቡር ሚኒስትሩ ጆሮ ደረሰ። ሚኒስትሩ ግን ይህን ሲሰሙ ከመቆጣት ይልቅ፣ እንደ አንድ ሩቅ አላሚ "ልማታዊ አባት" ፈገግ አሉ። የተወሰኑትን ተጫራቾች ቢሯቸው አስጠርተው በለዘበ አንደበት እንዲህ ሲሉ የጨረታውን ስነ-መለኮት አስረዷቸው፡-
“እህህ... እናንተ ሰዎች ግብዞች ናችሁ፣ ፊደል እንጂ አገር አላነበባችሁም! የጨረታ ሰነድ ማለት እኮ በወረቀት ላይ የተጻፈ የውሸት ተስፋ ነው። እናንተ 'ነገ እንገነባለን፣ አቅሙ አለን፣ እናደርጋለን' ብላችሁ በባዶ ወረቀት ስታነበንቡ፣ አቶ [እገሌ] ግን ማታ አስቦ፣ ጧት ጂ-ፕላስ-ስሪ ቪላ አሰርቶ፣ ከነሙሉ ዕቃው ቁልፍ የሚያስረክብ 'የተግባር ሰው' መሆኑን ለህዝብ (ማለትም ለእኔ) በተጨባጭ አሳይቷል። ታዲያ ሀገር የምትለወጠው በወረቀት ቃል ኪዳን ነው ወይስ በተጨባጭ አቅርቦት?”
ተጫራቾቹ አንገታቸውን ደፉ። እውነትም መመዘኛውን አልተረዱትም ነበር። አቶ [እገሌ] የተባሉት ባለሃብት ጨረታውን ያሸነፉት "በቴክኒክ እና በፋይናንስ" ብቃት ሳይሆን፣ "በቅድመ-ክፍያ እና በፍቅር" ብቃት እንደሆነ አሁን ገባቸው። ደግሞም እኮ የአቶ እገሌ ሰነድ ከሌሎቹ የሚለየው በኮምፒውተር ታይፕ የተመታ ሳይሆን፣ በብሎኬት እና በኮንክሪት የታነጸ መሆኑ ነው።
ሚኒስትሩ ንግግራቸውን ሲያጠቃልሉ፣ “አቶ እገሌ ለዚህ መሥሪያ ቤት ያሳዩት 'የማስረከብ ፍጥነት' ወደር የሌለው ነው። ትናንት ማታ ቃል የገቡትን ቪላ... ይቅርታ ፕሮጀክት፣ ወዲያው ነው እጄ ላይ ያስቀመጡት። ስለዚህ የህዝቡን ፕሮጀክት ከእርሳቸው የተሻለ ማንም አያሳካውም!” በማለት በጭብጨባ አሰናበቷቸው።
በእርግጥም በሀገራችን የጨረታ ሳጥን የሚከፈተው በሰም እና በታሸገ ኤንቨሎፕ አይደለም፤ የጨረታ ሳጥን የሚከፈተው በቪላ በር ቁልፍ ነው! "የሰጠህን አብላው፣ የቀበጠህን አባርረው" የሚለው የቀድሞ አባቶቻችን ጥልቅ ፍልስፍና በዘመናዊው ቢሮክራሲ ውስጥ ሲተረጎም እንዲህ ያምራል። ባለሃብቱ ቤቱን ለህዝብ ሰጡ፣ ሚኒስትሩ ደግሞ የህዝቡን ፕሮጀክት ለባለሃብቱ ሰጡ። ፍትሃዊ የሀብት ክፍፍል ማለት ይሄው አይደል?
አበጀ በለው የላኩልን

9 days ago