Logo
FBC
የልማት አስተዳደር ሪፎርሙ ፖሊሲዎች በተናበበ መንገድ እንዲዘጋጁ አስችሏል - የፕላንና ልማት ሚኒስቴር

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 11፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ኢትዮጵያ ተግባራዊ ያደረገችው የተቀናጀ የልማት አስተዳደር ሪፎርም የተለያዩ ፖሊሲዎች በተናበበ መንገድ እንዲዘጋጁ አስችሏል አለ የፕላንና ልማት ሚኒስቴር፡፡

“የመረጃ ሉዓላዊነት ለፖሊሲ ነጻነት'' በሚል መሪ ሐሳብ ኢትዮጵያ በመረጃና በስታቲስቲክስ የሉዓላዊነት ጉዞ ባስመዘገበችው ስኬት ላይ ያተኮረ ሀገራዊ ጉባኤ ተካሂዷል።

የፕላንና ልማት ሚኒስትር ዴኤታ አቶ በረከት ፍስሃጽዮን በዚሁ ወቅት እንዳሉት፥ በሀገር ደረጃ የሚታቀዱ እቅዶች እስከታችኛው የአስተዳደር እርከን ድረስ የሚወርዱበት አሰራርና ማዕቀፍ ሊኖር ይገባል፡፡

ባለፉት ጊዜያት ለእቅድ፣ ክትትልና ግምገማ የሚሰጠው ትኩረት ዝቅተኛ እንደነበር አስታውሰው፥ በዚህም የሀብትና የሰው ኃይል አመዳደብ ችግር እንደነበረበት ጠቅሰዋል፡፡

የአካባቢ አስተዳደሮች ሚናቸው በግልጽ ያልተለየ በመሆኑ በየደረጃው ተጠያቂነትን የሚያረጋግጥ አሰራር አልነበረም ነው ያሉት፡፡

ከይፋዊ ስታቲስቲክስ ባለፈ የእቅድና ግምገማ ሂደቱ እንዲሁም መረጃዎች በአግባቡ የሚያልፉ ባለመሆናቸው ሀሰተኛና የተጋነኑ ሪፖርቶች ለመንግስት ሲቀርቡ ነበር ብለዋል፡፡

እቅድ እና ፋይናንስ ያልተሳሰረበት አሰራርና በዘፈቀደ የሚከናወን የፕሮጀክት አተገባበር ሀገሪቱን ለማክሮ ኢኮኖሚ መናጋት ዳርገው እንደነበር አንስተዋል፡፡

ባለፉት የለውጥ አመታት በፖሊሲ ሪፎርም እንዲሁም በእቅድና ክትትል ላይ ትኩረት ተሰጥቶ ሲሰራ መቆየቱን ያነሱት ሚኒስትር ዴኤታው፥ በዚህም ችግሮቹን በተቀናጀ የልማት አስተዳደር መፍታት መቻሉን አስረድተዋል፡፡

የመንግስትን የውሳኔ አሰጣጥ በተጨባጭ መረጃ መደገፍና ዲጂታል አገልግሎት አሰጣጥን ማጠናከር በቀጣይ በትኩረት የሚሰራባቸው መስኮች መሆናቸውን ጠቁመዋል፡፡

በአቤል ነዋይ

1 month ago

No replys yet!

Be the first to share what you think — your comment will appear here.