Logo
EBC
የገላን ጉራ ኢንዱስትሪ ፓርክ ስልጣኔና የሥራ ባህል ፈተና
**********************
(የዕለቱ መልክዕት)

የገላን ጉራ ኢንዱስትሪ ፓርክ መመረቅ ተራ የህንፃዎች ስብስብ ሳይሆን የኢትዮጵያን የከተማነት መልክዓ-ምድር በአጭር ጊዜ የመቀየር ትልቅ ማሳያ ነው። የዛሬ ሁለት ዓመት መኪና የማይደርስበት ገጠር የነበረው ይሄው ቀጠና ዛሬ በዘመናዊ አስፓልት፣ በቤት ግንባታ እና በአረንጓዴ መናፈሻዎች ደምቆ የአዲስ አበባ አዲስ የኢኮኖሚ ማዕከል ሆኗል።

ይህ ዓይነቱ መሠረተ-ልማት የውጭ ኢንቨስተሮች ችግር ሲፈጠር ጥለውት ለሚሄዱት የብድር ፓርክ ሳይሆን ነገ የሀገራችንን የኢንዱስትሪ መፃኢ እድል ለሚወስኑት የሀገር ውስጥ ወጣቶች እንደ "መዋዕለ-ህጻናት" የሚያገለግል የስትራቴጂ ለውጥ ነው፤ አባቶቻችን "የአባት እዳ ለልጅ፣ የቤት እዳ ለባለቤት" እንደሚሉት ሀገርን በራስ ልጅ እውቀትና አቅም ካልገነቡት የሰው እጅ መመልከት ማብቂያ የለውም።

ሆኖም ግን ይህንን አካላዊ ለውጥ ወደ ዘላቂ ብልጽግና ለመቀየር ትልቁ ፈተና የዜጎች የሥራ ባህልና የአስተሳሰብ አድማስ መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ተናግረዋል። በሀገራችን በአንድ በኩል "ሥራ የለም" የሚል ሰበብ እየተደመጠ፣ በሌላ በኩል የሰው ኃይል እጥረት መከሰቱ ትልቅ እንቆቅልሽ ሆኗል፤፡ ይህማ "ሰነፍ እረኛ ከጅብ ይማከራል" እንደሚባለው ሆኖ ሥራን እየናቁ የሥራ እጥነትን ማማረር ነው።

ይህንን ክፍተት ለመሙላት የውጭ ሀገር ዜጎች ወደ ኢትዮጵያ እየገቡ በመሆኑ ዜጎች ከተራ ወሬና የሶሻል ሚዲያ ስድብ ወጥተው፣ "ሳይቀድሙኝ የቀደሙትን መቅደም" እንዲሉ ላባቸውን በማንጠባጠብ የሥራ እድሎችን ለመጠቀም በአስቸኳይ መንቃት አለባቸው።

"እጅ ከአፍ አይጠፋም" እንዲሉ ልማት ከድህነት መውጫ ብቸኛ መንገድ በመሆኑ አርሶ አደሩንና አቅመ-ደካሞችን ያቀፈ መሆን እንዳለበት የገላን ጉራ ኢንዱስትሪ ፓርክ ህያው ማሳያ ነው። በሀገራችን በሚሰሩ ልማቶች አርሶ አደሩን አፈናቅሎ ከመጣል ይልቅ ምቹ የገበያ ሁኔታ መፈጠሩ፣ የጎዳና ተዳዳሪዎችንና በቡና ቤት ያሉ እህቶችን አሰልጥኖ ወደ ሥራ ማስገባት፣ ኢኮኖሚው 10.2 ፐርሰንት እንዲያድግ ከሚያደርገው የቁጥር ስሌት ባሻገር ማህበራዊ ፍትህን ያረጋገጠ ትውልድ የመገንባት ትልቅ ህልም ነው።

በመሆኑም የተጀመረው ትልቅ ጉዞ እንዳይደናቀፍ በሥራው ውስጥ የሚዘሩ "የሌብነት አረሞች" በአስቸኳይ ሊነቀሉ እንደሚገባ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ጠንካራ ማስጠንቀቂያ ተሰጥቷል፡፡ ሙስና የሀገርን ልፋት የሚያቀልጥ አደገኛ ደዌ ነውና። የገንዘብም ሆነ የጊዜ እጥረት ሳይበግረው በንፁህ ልቦና እየተከናወነ ያለው ለውጥ ስኬታማ የሚሆነው ዜጎች በእምነት፣ በቋንቋ እና በጾታ ሳይገፋፉ እርስ በርስ ሲከባበሩ ብቻ ነው፤ ምክንያቱም "ድር ቢያብር አንበሳ ያስር" ነውና።

"ልጆቻችን በፍጹም አይለምኑም" የሚለውን የተስፋ ስንቅ ይዞ የኢትዮጵያን ብልጽግና በጋራ ለማየት እያንዳንዱ ዜጋ ጓዳው እስኪደርስ ሳይሆን በሰፈሩ ለሚመጣው ለውጥ አጋዥና የቀና ልብ ያለው መሆን ይጠበቅበታል።

የኢቢሲ ዶት ስትሪም ኤዲቶሪያል

30 days ago

No replys yet!

Be the first to share what you think — your comment will appear here.