Logo
Zehabesha
(ዘ-ሐበሻ ዜና) በአሜሪካ የኤርትራ አምባሳደር ሶፍያ ተስፋማሪያም፣ "Eritrea’s Sovereignty Claim and the Insecurity It Conceals" (ኤርትራ የሉዓላዊነት ጥያቄ እና የሚደብቀው የደህንነት ስጋት) በሚል ርዕስ በኢትዮጵያ በኩል ለወጣው ጽሁፍ ሰፊ እና ዝርዝር ምላሽ ሰጥተዋል። አምባሳደሯ በኤክስ ገፃቸው ባሰፈሩት ጽሁፍ፣ የኢትዮጵያ የባህር በር ጥያቄ፣ የኤርትራ ሉዓላዊነት ታሪካዊ መነሻዎች፣ እንዲሁም የቀጠናው ጂኦ-ፖለቲካዊ ውጥረቶች ላይ የኤርትራን አቋም አንፀባርቀዋል።

ጽሁፉ የኤርትራን የሉዓላዊነት አቋም እንደ "መደበቂያ ወይም የፖለቲካ ስጋት" አድርጎ ማቅረቡን አምባሳደር ሶፍያ አጥብቀው ተችተዋል። ሉዓላዊነት በዘመናዊው ዓለም አቀፍ ህግ (በተባበሩት መንግስታት ቻርተርም ሆነ በአፍሪካ ህብረት የመመስረቻ ሰነድ) የተረጋገጠ መሰረታዊ መብት እንጂ፣ ኤርትራ የምትደበቅበት ሽፋን አይደለም ብለዋል። በተለይ ለኤርትራ ሉዓላዊነት ማለት ከረዥም የፀረ-ቅኝ ግዛት እና የፀረ-ወረራ ትግል፣ ከተደጋጋሚ ጦርነቶች እና መስዋዕትነት የተገኘ የህልውና ጉዳይ መሆኑን አብራርተዋል።

"ኢትዮጵያ በኤርትራውያን የታሪክ ትውስታ ውስጥ ተራ ጎረቤት ሀገር ብቻ ሳትሆን የቀድሞ ቅኝ ገዥ ነበረች" ያሉት አምባሳደሯ፣ ይህ ታሪካዊ እውነታ ኤርትራ ለድንበር እና ለሉዓላዊነት ጥያቄዎች የምትሰጠውን ትኩረት እንደሚቀርፀው ገልጸዋል። የአማርኛውን "የወጋ ቢረሳ የተወጋ አይረሳም" የሚለውን ምሳሌ በመጥቀስም፣ ጦርነት፣ ወረራ እና ማዕቀብን ያሳለፈ ህዝብ የሉዓላዊነት ጉዳይን በቀላሉ ሊያየው እንደማይችል አስገንዝበዋል።

አምባሳደሯ እንደገለፁት፣ ኤርትራ የባህር በር አልባ የሆነችው ኢትዮጵያ የንግድ የባህር በር (Maritime Access) የማግኘት መብት አላት የሚለውን መርህ ተቃውማ አታውቅም። ዓለም አቀፍ ህግም ይህንን መብት በድርድር እና በስምምነት እንዲፈፀም ይፈቅዳል። ችግሩ ያለው ግን ይህ ጥያቄ እየቀረበበት ያለው መንገድ ነው ብለዋል።

የኢትዮጵያ ከፍተኛ ባለስልጣናት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድን ጨምሮ፣ የባህር በር ጥያቄውን "ታሪካዊ መብት" እና "የህልውና ጉዳይ" አድርገው ማቅረባቸው፣ እንዲሁም "በሰላም ካልሆነ በኃይልም ቢሆን" የሚሉ ዛቻዎች መደመጣቸው በኤርትራ በኩል ስጋት መፍጠሩን አብራርተዋል። ከዚህም በተጨማሪ፣ አሰብን እና የኤርትራን ግዛቶች ከኢትዮጵያ ጋር ቀላቅለው የሚያሳዩ የተጭበረበሩ ካርታዎች በማህበራዊ ሚዲያ እና በወታደራዊ መድረኮች ላይ መሰራጨታቸው ሉዓላዊነትን የሚጋፋ አስገዳጅ ትርክት መሆኑን አምባሳደሯ ተችተዋል። "ዓለም አቀፍ ህግ (አንቀጽ 2(4)) ጥቃት መሰንዘርን ብቻ ሳይሆን በማስፈራራት እና በዛቻ የሚደረግን ጫናም ይከለክላል፤ ስለዚህ ኤርትራ የወሰደችው የጥንቃቄ እርምጃ ምክንያታዊ ነው" ብለዋል። በ2024 በኢትዮጵያ እና በሶማሌላንድ መካከል የተፈረመው የመግባቢያ ስነ-ስነድም በሶማሊያ ሉዓላዊነት ላይ የተቃጣ ጥሰት በመሆኑ ቀጠናዊ ውጥረቱን እንዳባባሰው ጠቅሰዋል።

አምባሳደር ሶፍያ ጽሁፉ የ1998-2000 (እ.ኤ.አ) የኤርትራ እና ኢትዮጵያ ጦርነትን በተመለከተ ያቀረበውን ሀሳብ "የተዛባ" ብለውታል። የኤርትራ ድንበር በማያሻማ ሁኔታ በ1900፣ 1902 እና 1908 በጣሊያን እና በኢትዮጵያ መካከል በተደረጉ ስምምነቶች ህጋዊ መሰረት ያለው መሆኑን አውስተዋል። የጦርነቱ መነሻ የነበረችውን ባድመን በተመለከተም የድንበር ኮሚሽኑ የማያዳግም ውሳኔ ለኤርትራ የሰጠ መሆኑን አስታውሰዋል።

ጦርነቱን ተከትሎ ለዓመታት የቀጠለው ፖለቲካዊ ቀውስ የኤርትራ ህግ አለማክበር ሳይሆን፣ ኢትዮጵያ "የመጨረሻ እና አሳሪ" ነው የተባለውን የድንበር ኮሚሽኑን ውሳኔ ለሁለት አስርት ዓመታት አልቀበልም በማለቷ የመጣ መሆኑን ሞግተዋል። አክለውም፣ በ2009 በኤርትራ ላይ ተጥሎ የነበረው የተባበሩት መንግስታት ማዕቀብ፣ በኢትዮጵያ ጫና ኢጋድን እና አፍሪካ ህብረትን በመጠቀም የተሰራ ፖለቲካዊ ሴራ እንደነበር እና ማዕቀቡ በ2018 መነሳቱ ይህንኑ እንደሚያረጋግጥ ገልጸዋል።

ስለ ኤርትራ ብሄራዊ አገልግሎት የተነሳውን ትችት በተመለከተ፣ አምባሳደሯ ፕሮግራሙ ወታደራዊ ብቻ ሳይሆን ሲቪል እና የልማት ስራዎችንም (እንደ ትምህርት፣ ጤና፣ እና መሰረተ ልማት) ያካተተ መሆኑን አስረድተዋል። የብሄራዊ አገልግሎቱ ጊዜ የተራዘመውም ኢትዮጵያ የፈጠረችውን "የሰላምም የጦርነትም የሌለበት" ሁኔታ እና ተያያዥ የፀጥታ ስጋቶችን ለመቋቋም መሆኑን አብራርተዋል። በሌላ በኩል ኢትዮጵያ በአማራ እና በኦሮሚያ ክልሎች እያካሄደችው ያለው መጠነ-ሰፊ ጦርነት፣ የድሮን ጥቃቶች እና የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ችላ ተብለው የኤርትራን ብቻ ማጉላት ሚዛናዊነት የጎደለው ትንታኔ ነው ብለዋል።

አምባሳደሯ ሲቀጥሉም የኤርትራ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ሁሌም በሉዓላዊ እኩልነት፣ ጣልቃ ባለመግባት እና የቀጠናው ሀገራት የጋራ ተጠቃሚነት ላይ የተመሰረተ መሆኑን ጠቅሰዋል። ኤርትራ በጋራ ስምምነት እና በዓለም አቀፍ ህግ ላይ የተመሰረተ የንግድ እና የባህር በር ትብብርን እንደማትቃወም ደግመው ያረጋገጡት አምባሳደሯ፣ "የማንቀበለው ግን ትልልቅ ሀገራት በስፋታቸው እና በህዝብ ቁጥራቸው ተማምነው የትናንሽ ጎረቤቶቻቸውን ሉዓላዊነት የሚጋፋ ጫና ማድረጋቸውን ነው" ብለዋል።

በኤርትራ እና ኢትዮጵያ መካከል ወደፊት ስለሚኖረው ግንኙነትም ሲያብራሩ፤ "እውነተኛ እና ዘላቂ ሰላም በዲፕሎማሲያዊ መፈክሮች ወይም በውጫዊ ጫና አይመጣም። በጋራ መከባበር፣ መተማመን እና ጊዜን በሚጠይቅ ሂደት ላይ መመስረት አለበት። በተለይም በ2018 የተፈጠረውን ታሪካዊ የሰላም እድል በአግባቡ መጠቀም ያልቻለው የኢትዮጵያ አመራር ባለበት ሁኔታ፣ ሰላምን ማጣደፍ አይቻልም። ዘላቂ ሰላም እንዲመጣ ኢትዮጵያ በመጀመሪያ ከራሷ ጋር ሰላም መፍጠር አለባት" በማለት ጽሁፋቸውን አጠናቅቀዋል።

3 months ago

No replys yet!

Be the first to share what you think — your comment will appear here.