Logo
Zehabesha
(ዘ-ሐበሻ ዜና) አቶ ጌታቸው ረዳ በአፍሪካ ሪፖርት ላይ ላቀረቡት ፅሁፍ ህወሀት መልስ ሰጠ፡፡ ህወሀት ‹‹ለዲፕሎማቲክ ማህበረሰብና እውነትን ለሚፈልጉ ሁሉ›› በሚል ርእስ ዛሬ ባሰራጨው ባለ 6 ገፅ ዘለግ ያለ ፅሁፍ አቶ ጌታቸው ረዳ በአፍሪካን ሪፖርት ላይ ላቀረቡት ፅሁፍ መልስ ሰጥቷል፡፡ በፅሁፉ አቶ ጌታቸው ረዳን ‹‹ስነምግባር የጎደለው፣ ሆነ ብሎ የተሳሳተና ህዝብን የዘለፈ›› በሚል የገለፀው ህወሀት ካነሳቸው ነጥቦች መካከል የጦርነቱን አጀማመር የተመለከተው ይገኝበታል፡፡ አቶ ጌታቸው በመፅሄቱ ላይ ‹ጦርነቱ ሊነሳ የቻለው ህወሀት ክልላዊ ምርጫ ማካሄዱን ተከትሎ ነው›› ብለው የፃፉ ሲሆን ህወሀት በመልሱ ላይ ‹‹ይህ ሞኝነት ብቻ ሳይሆን በስነምግባርም ሆነ በፖለቲካ እጅግ አፀያፊ አገላለፅ ነው›› ብሏል፡፡

ሲያስረዳም በትግራይ ምርጫ ከመካሄዱ በፊት በፌዴራል መንግስቱ ፖለቲካዊ ሴራ፣ የኢኮኖሚ አፈና፣ ወታደራዊ ከበባ፣ የጥላቻ ፕሮፖጋንዳና የተቀናጀ የጦርነት ዝግጅት ሲደረግ መቆየቱን አቶ ጌታቸው ረዳ ሆነ ብለው እንደዘለሉት አስታውቋል፡፡ እንዲሁም በአቶ ጌታቸው ረዳ ፅሁፍ ህወሀት ጦርነቱ ውስጥ የገባው በተሳሳተ ስሌት መሆኑን መግለፁን ‹‹በጦርነቱ ጉዳት የደረሰባቸውን ተጠያቂ ማድረግ ነው›› ያለው ህወሀት ጨምሮም ይህ አስተሳሰብ አደገኛ መሆኑን አስረድቷል፡፡

‹‹ትግራይ ወደገደል አፋፍ እየተወሰደች ነው›› የሚለውን የአቶ ጌታቸው ረዳ ገለፃ ደግሞ ህወሀት ‹‹እንደእውነቱ ከሆነ በትግራይ ውስጥ ያሉ ሰዎች በብዛት የሚናገሩት ተቃራኒውን ነው፡፡ ትግራይ በአብይ አህመድ የተቀየሰውን የፖለቲካ ወጥመድ ለማምለጥ ፖለቲካዊና ስትራቴጂያዊ አማራጮችን እየፈለገች ነው›› ብሎታል፡፡ ህወሀት በማስከተልም ‹‹በአቶ ጌታቸው ረዳ በፅሁፋቸው በመቶ ሺዎች መገደላቸውንና በሚሊዮኖች መፈናቀላቸውን እንዲሁም ትግራይ መውደሟን አምነዋል፡፡ ይሁንና የዚህን ግፍ ዋና አርክቴክ አብይ አህመድን ስም ከመጥቀስ ግን ተቆጥበዋል›› ያለ ሲሆን በፅሁፉ ውስጥ በአብዛኛው ደብረፅዮን ገብረሚካኤልን መውቀሱን ተቃውሟል፡፡

ረዘም ያሉ ሀተታዎችን የያዘው ይህ የህወሀት ፅሁፍ ‹‹ትግራይ አሁን ጦርነት ሳይሆን አማራጭ በመፈለግ ላይ ናት›› ብሏል፡፡ የአቶ ጌታቸውን ፅሁፍ በአብዛኛው የአብይ አህመድን መንግስት ፍላጎቶችና ስትራቴጂያዊ ስሌቶች የያዘ ነው ሲልም አጣጥሎታል፡፡

3 months ago

No replys yet!

Be the first to share what you think — your comment will appear here.