Logo
Zehabesha
(ዘ-ሐበሻ ዜና) የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንጃሚን ኔታንያሁ በቅርቡ በእስራኤል የተመዘገቡትን ተከታታይ ፀረ-ክርስቲያን ጥቃቶች "የተነጠሉ ክስተቶች " ናቸው በማለት ያጣጣሉ ሲሆን፣ አጥፊዎቹም መቀጣታቸውንና ስህተቶች መታረማቸውን ገልጸዋል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህን ያሉት አገራቸው ከክርስቲያኖች እና ከክርስትና እምነት ጋር ያላትን የጋራ እሴትና ታሪክ በማውሳት ነው።

ኔታንያሁ ከሲቢኤስ የቴሌቪዥን ጣቢያ "60 ሚኒትስ" ፕሮግራም ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ፤ የላቲን ፓትርያርክ በፋሲካ በዓል ወደ ቅዱስ መቃብር ቤተክርስቲያን እንዳይገቡ መከልከላቸው፣ አንድ የእስራኤል ወታደር በሊባኖስ የኢየሱስን ሃውልት መስበሩ፣ እንዲሁም በኢየሩሳሌም አሮጌዋ ከተማ በአንዲት መነኩሲት ላይ የደረሰው ጥቃት ተነስተውላቸው ነበር። ጠያቂው ይህ በእስራኤል እያደገ የመጣ "በክርስቲያኖች ላይ ያነጣጠረ የጥላቻ አዝማሚያ" እንደሆነ ቢጠይቃቸውም ኔታንያሁ ግን ይህንን በጥብቅ አስተባብለዋል።

ይህንን ክስ "የፈጠራ ውንጀላ" ሲሉ የጠሩት ኔታንያሁ፣ እስራኤል በቀጣናው ክርስቲያኖች በነጻነት የሚኖሩባት ብቸኛ ሀገር መሆኗን ተናግረዋል። በአጎራባች የአረብ ሀገራት ግን ክርስቲያኖች "እንደሚጨቆኑ እና አንዳንዴም እንደሚገደሉ" ገልጸዋል። አክለውም የኢየሱስ ክርስቶስ የትውልድ ስፍራ የሆነችው ቤተልሔም በእስራኤል ቁጥጥር ስር በነበረችበት ወቅት 80 በመቶው ነዋሪዋ ክርስቲያን እንደነበር፣ አሁን በፓለስቲና ባለስልጣናት ስር ስትተዳደር ግን "20 በመቶ ክርስቲያን፣ 80 በመቶ ደግሞ ሙስሊም" መሆኗን በምሳሌነት አንስተዋል።

እነዚህ ተከታታይ ጥቃቶች ድንገተኛ ስህተቶች ስለመሆናቸው የተጠየቁት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ "እነዚህ ክስተቶች ድንገተኛ ስህተቶች ብቻ ሳይሆኑ፣ ከእኛ እሴት እና ለክርስትና ካለን ክብር ጋር ፍጹም የሚቃረኑ ናቸው" ብለዋል። በድርጊቱ የተሳተፉት ላይ እርምጃ መወሰዱን ሲያብራሩም፣ "ያ የኢየሱስን መስቀል የሰበረው ወታደር አሁን እስር ቤት ነው፤ በመነኩሲቷ ላይ ጥቃት ያደረሰው ግለሰብም ፍርድ ቤት ቀርቦ ጉዳዩ እየታየ ነው" በማለት ማብራሪያ ሰጥተዋል።

ከኢራን ጋር በተፈጠረው ጦርነት ምክንያት የሰዎች ስብስብን ለመገደብ በተጣለው ክልከላ የላቲን ፓትርያርኩ ፒዛባላ ወደ ቤተክርስቲያን እንዳይገቡ ስለመከልከላቸው በተነሳው ጥያቄ፣ ኔታንያሁ "ወዲያውኑ ጣልቃ ገብቼ በሮቹ እንዲከፈቱ አድርጌያለሁ" ብለዋል። ይሁን እንጂ ፓትርያርኩ በሆሳዕና በዓል ወደ ቤተክርስቲያን እንዳይገቡ ከተከለከሉ በኋላ፣ ውስን ሰዎች በተገኙበት ጸሎት ለማድረስ አራት ቀናት እንደፈጀባቸው መረጃዎች ያመለክታሉ።

"እስራኤል በመካከለኛው ምስራቅ ክርስቲያኖችን የምትጠብቅ፣ የምታከብር እና ክርስትናን የምትቀበል ብቸኛ ሀገር ነች። የጋራ ታሪካችንን እና ወቅታዊ ክስተቶችን ለማጣመም የሚደረግ ጥረት አለ፤ እነዚህን የተነጠሉ ስህተቶች በመያዝ የእስራኤል ፖሊሲ አስመስሎ ማቅረብ አስቂኝ ነው" ሲሉ ኔታንያሁ ቃለ ምልልሳቸውን አጠናቅቀዋል።

እነዚህ የጠቅላይ ሚኒስትሩ አስተያየቶች በቴሌቪዥን ስርጭቱ ላይ ያልተካተቱ (off-mic) ሲሆኑ፣ የተገኙት የሲቢኤስ (CBS) ጣቢያ ካወጣው ሙሉ የቃለ ምልልሱ የጽሁፍ ቅጂ ላይ መሆኑ ታውቋል።

1 month ago

No replys yet!

Be the first to share what you think — your comment will appear here.