"እጇ ሲያጥር የአፏን"
ደራሲ ሕይወት እምሻው
#ethiopia | በትንሿ የአፓርታማዬ በረንዳ ላይ፣ ለእርግብ እናቶች መውለጃ የለቀቅኳት አንዲት ስፍራ አለች።
የግቢያችን እርግቦች ከለመዷት ከረሙ።
አሁንማ ድርስ እርጉዝ እርግቦች አንዳቸው እንዳቸውን እያዩ፣ ወይ ደግሞ በእርግብኛ እያወኩ በየተራ የበረንዳዬን ቁራሽ በጊዜያዊነት ተከራይተው፣ ልጆቻቸውን በቅርፊት ታቅፈው፣ እኔንና ቤተሰቤን እንደ ወዳጅ አምነው፣ እንቁላሎቻቸው እርግብ ሆነውና ክንፍ አውጥተው እስኪበሩ ድረስ በሰላም የሚቆዩባት መጠጊያ ሆናለች።
በዚያ ሰሞን እናቲቱ በእርግብ ጥበቧና በማያልቅ ትዕግሥቷ እንቁላሎቿን ለቀናት ታቅፋ ትቀመጣለች።
በሂደትም እነዚያ ገና ዓይናቸውን በግማሽ እንኳ ያልገለጡ ትንንሽ ጫጩቶች ከቅርፊታቸው ወጥተው፣ አፋቸውን ወደ እናታቸው ምንቃር ለምግብ ቀና ሲያደርጉ ማየት የማልለምደውና ሁሌም አዲስ የሚሆንብኝ ትንሽ የእግዚአብሔር ተአምር ነው።
ብዙ ጊዜ ቤት ስለምውል፣ እናት ለምግብ ፍለጋ ወይ ለሌላ 'እርግባዊ' ጉዳይ አጠር ያለ በረራ አድርጋ እስክትመለስ ድረስ፣ ልጆቿን በታማኝነት ከሩቁ እጠብቃቸዋለሁ።
ስንቴም ይሁን በበረንዳዬ ደጋግሞ የሚከሰተውን ይህን ተፈጥሯዊ ሂደት መታዘብ ከቶ አይሰለቸኝም።
ከሰሞኑ በአንዱ ጠዋትም ያ ሚጢጢ ተአምር ዳግም ሲገለጥ፣ ሜሪ ኦሊቨር "ዛሬ ማለዳ" (This Morning) በሚለው ግሩም ግጥሟ የገለጸችው እውነት ትዝ አለኝ።
የገጠመኝ ትዕይንት ዛሬ ከምናከብረው የእናቶች ቀን ጋር ፍጹም የተጋመደም መሰለኝ።
ሜሪ በግጥሟ እንዳለችው የእኔም የእርግብ ልጆች እንቁላሎች ተሰበሩ።
ትናንት በቅርፊቱ ጨለማ ውስጥ በቀስታ እየተላወሱ ተኝተው የነበሩት ጫጩቶች፣ ዛሬ አፋቸውን ከፍተው ለምግብ አንጋጠጡ፤ በሰላላ ድምፃቸውም በሕይወት መኖራቸውን፣ ዓለምን መቀላቀላቸውን አበሰሩ።
በአፋቸው የሚገባው ሲሳይ ከየት እንደመጣ፣ ማን እንደሚያዘጋጀው እንኳን ሳያውቁ፣ "ጨመር አድርጊልን! አሁንም ጨምሪልን!" በሚል ልበ-ሙሉነት ለሕይወት ግብዣ ድግስ አፋቸውን ከፍተው ይጠባበቃሉ።
ጫጩቶቹ 'አያ ሙሌ' እንዳለው «ፈጣሪዋን አምና የአፏን ጥሬ ሰጥታ»፤ ሳይጠይቁ ለምትመግባቸው፣ ሳይርባቸው ለምታጠግባቸው፣ ከራሷ ምንቃር ለምታጎርሳቸው እናታቸው ራሳቸውን ሙሉ በሙሉ አሳልፈው ሰጥተዋል።
ገና ዓይናቸው እንኳ ሳይገለጥ አፋቸውን የሚከፍቱት በዚሁ እናታቸው ላይ ባላቸው ጽኑ እምነት ነው። እሷም አታሳፍራቸውም፤ ሳታርስና ሳትሸምት፣ ወይ ደግሞ እፍኝ ጥሬ ሳትለምን የአፏን "እንካችሁ" ትላቸዋለች።
እነዚህ ጫጩቶች ከዚህች ቅጽበት ውጭ ሌላ ምንም ዓይነት ረቂቅ ሐሳብ የላቸውም።
ነገ የሚበሩበትን ግዙፍና ሰፊ ሰማይ፣ ማረፊያ የሚሆኑዋቸውን የጫካ ዛፎች፣ አልፎ ተርፎም አሳዳጅ አዳኞቻቸውን ገና አያውቋቸውም። የዓለም ሐሳብና የመኖር ትካዜ አልተጫናቸውም፤ ዞሮ፣ በሮና ለቅሞ የመብላት እዳም ገና አልተገለጸላቸውም።
ይባስ ብሎ በጀርባቸው ላይ ክንፍ እንዳላቸውና መብረር እንደሚችሉ እንኳ ገና አልተረዱም። የእናታቸው ክንፍ የእነሱ፣ ምንቃሯም ምንቃራቸው ነው—እምነታቸው ሁሉ በእናታቸው ላይ ብቻ!
እንዳልኴችሁ ይህ ምትሃታዊ ትዕይንት ልክ እንደ ተራና ቀላል የዕለት ተዕለት ድርጊት በበረንዳዬ ላይ ስንቴ ይደጋገማል።
በዚህች ሚጢጢ ስፍራ፣ ሕይወት ያለ ምንም አጃቢ ትርክትና ያለ ፍልስፍናዊ ጥያቄ፣ በራሷ ምት የእናትነትን ጥልቅነትና የልጅን እናትን አምኖ የመኖር ጅማሮን እንደ ዋዛ ታውጃለች።
ለማንኛውም ዛሬ የእናቶች ቀን አይደል...?
አያ ሙሌ ለአበበ ተካ «ወፊቱ» ዜማ በጻፈው ውብ ግጥም ላይ፦
“ወልዶ ማሳደጉን ብዙ ሰው ሲያውቅበት
የአፉን ማን ይሰጣል የእጁ ሲርቅበት”
ብሎ ያሞገሳት ያቺ ሳታርስና ሳትሸምት ጫጩቶቿን ደፋ ቀና ብላ የምትመግብ ወፍ፣ ዛሬም በእርግብ እናትነት ተመስላ ልቤን ብትገዛውም፤ አርሰውና ሸምተውም እጃቸው ሲያጥር የአፋቸውን የሚሰጡ ብዙ የሰው እናቶችንም አውቃለሁ።
ልጆቻቸውን ለቻሉት ጊዜ ያህል ከዓለም ሐሳብና የመኖር ትካዜ ከልለው ያቆዩ፤ ጥሮ እና ግሮ ከመኖር እዳ ያዳኑ፣ በጎበጠ ትከሻቸው አዝለው ረጅምና መራራ መንገድን ለልጆቻቸው ያሳጠሩ ስንት ሴቶችን አውቃለሁ፡፡
እንዲህ ያሉ እናቶች ያላችሁ እድለኛ ልጆች ሁሉ "እኔም እጇ ሲያጥር የአፏን የሰጠችኝ ከወፍ የምትበልጥ እናት አለችኝ" ብላችሁ አውጁ፡፡
መልካም የእናቶች ቀን!
😘😘😘

25 days ago