Logo
Zehabesha
(ዘ-ሐበሻ ዜና) ህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት) የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር "ፓርቲው ከሱዳን መንግስት ጋር በመተባበር ቀጣናውን ለማተራመስ እየሰራ ነው" ሲል ያወጣውን መግለጫ መሠረተ-ቢስ፣ ኃላፊነት የጎደለው እና የሀሰት መረጃ ስርጭት አካል ነው ሲል ዛሬ ባወጣው ይፋዊ መግለጫ ውድቅ አደረገ።

ድርጅቱ ለውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በሰጠው ምላሽ፣ ቀጣናው መረጋጋት በሚሻበት በአሁኑ ወቅት እንዲህ ያሉ ውንጀላዎች ውጥረትን ከማባባስ ባለፈ እውነተኛ የሰላም ጥረቶችን የሚያደናቅፉ ናቸው ብሏል። ህወሓት ቀጣናዊ መረጋጋትን ከሚያደፈርስ ማንኛውም ድርጊት ነፃ መሆኑንም አረጋግጧል። በትግራይ ክልል ተከስቶ በነበረው ከፍተኛ የጦርነት ጊዜ፣ የሱዳን ህዝብ እና መንግስት ለተፈናቀሉ የትግራይ ተወላጆች ሰብአዊ እርዳታ እና መጠለያ መስጠታቸውን ያስታወሰው መግለጫው፣ ይህን ሰብአዊ ድርጊት አዛብቶ ለፖለቲካ ትርፍ ማዋል ተገቢ አለመሆኑን አስገንዝቧል።

የትግራይ ህዝብ የፕሪቶሪያውን የግጭት ማቆም ስምምነት (CoHA) ሙሉ እና ታማኝ ትግበራ በትዕግስት እየጠበቀ መሆኑን የጠቆመው ህወሓት፣ በተለይም የተፈናቀሉ ዜጎችን በሰላማዊ፣ በፈቃደኝነት እና በክብር ወደ ቀያቸው የመመለስ ሂደት ላይ ትኩረት ማድረጉን አመልክቷል። በምዕራብ ትግራይ የሚገኙትን ጨምሮ የድርጅቱ ኃይሎች የተፈናቃዮች ምላሽ በሰላማዊ እና ደህንነቱ በተጠበቀ ሁኔታ እንዲከናወን የበኩላቸውን ሚና ለመጫወት ቁርጠኛ መሆናቸውንም አክሏል።

በተጨማሪም ኢትዮጵያን እና ቀጣናውን ዳግም ወደ ጦርነት ሊያስገቡ የሚችሉ ትንኮሳዎች፣ የውጭ ጣልቃ ገብነቶች እና አጋጣሚን ጠባቂ የፖለቲካ አሰላለፎች በእጅጉ እንደሚያሳስቡት ፓርቲው ገልጿል። እነዚህ አጭር እይታ ያላቸው ስሌቶች ከጎረቤት ሀገራት ጋር ያለውን ግንኙነት ከማሻከር ባለፈ ለሀገሪቱ የረጅም ጊዜ ሰላም አደጋ መሆናቸውን አስጠንቅቋል። የትግራይ ህዝብ ለሰላም ሲል እጅግ ከፍተኛ ዋጋ መክፈሉን ያነሳው ህወሓት፣ ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ሁሉን አሳታፊ እና አሳማኝ በሆነ የውይይት መድረክ ላይ ለመሳተፍ ዝግጁ መሆኑን አረጋግጧል።

የሚመለከታቸው አካላት እና ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ቀስቃሽ ትርክቶችን በማውገዝ፣ ተጠያቂነትን በማስፈን እና የስምምነቱን ሙሉ ትግበራ በመደገፍ የበኩላቸውን እንዲወጡ ጥሪ አቅርቧል። ዘላቂ ሰላም ሊረጋገጥ የሚችለው በውይይት እና በኃላፊነት ስሜት እንጂ በፕሮፓጋንዳ እና ግጭትን በማባባስ አለመሆኑን መግለጫው በአጽንዖት አስምሮበታል።

29 days ago

No replys yet!

Be the first to share what you think — your comment will appear here.