Logo
EBC
ብልጽግና ፓርቲ በባሕር ዳር ከተማ የአደባባይ የምርጫ ቅስቀሳ አካሄደ
**********************

የባሕር ዳር ከተማ አስተዳደር ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት፣ "ኢትዮጵያን ወደ ተምሳሌታዊት ሀገር!" በሚል መሪ ቃል ሰፊውን የማኅበረሰብ ክፍል ያሳተፈ የአደባባይ የምርጫ ቅስቀሳ በከተማዋ አካሂዷል።

በከተማ አስተዳደሩ የብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ሞላ ሁሴን በቅስቀሳ መርሐ-ግብሩ ላይ ባደረጉት ንግግር፣ “ባለፉት ዓመታት በባሕር ዳር ከተማ የጀመርናቸው ሥራዎች ከተማዋን ውብ ከማድረግ ባሻገር በልማት ሥራዎች የነዋሪዎችን ተጠቃሚነት እና ምቹነት ያረጋገጡ ናቸው” ብለዋል።

ለአብነትም ለከተማዋ ድምቀት የፈጠረውን የኮሪደር ልማት እና ታላቁን የዓባይ ወንዝ ድልድይን እንደማሳያነት አንሥተዋል።

ይህ ገና ጅማሮ ነው ያሉት ኃላፊው ፓርቲው በምርጫው ካሸነፈ ዘላቂ ሰላምን፣ ልማትንና ህብረብሔራዊ አንድነትን ለማጠናከር ይሰራል ብለዋል።

ከተማዋ ወደ ታላቅ ከፍታ እንድትደርስ ይሠራል ሲሉም ገልጸዋል።

ፓርቲው ለ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ያቀረባቸው ዕጩዎች የከተማዋን የልማት ከፍታ እና የማኅበረሰቡን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ አስተዋፅኦ ያበረከቱ መሆናቸውንም ገልጸዋል።

የባሕር ዳር ከተማ አስተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ አቶ ጎሹ እንዳላማው በበኩላቸው ፓርቲው፣ ግልጽ ዓለማ ያሉት ወንድማማችነትን እና አንድነትን በማጠናከር ጠንካራ እና ተምሳሌት የሆነችውን ኢትዮጵያን ለመገንባት አልሞ እየተንቀሳቀሰ የሚገኝ የሰላም እና የልማት ፓርቲ ነው ብለዋል።

ለዜጎች እኩል ተጠቃሚነት የሚተጋ ፓርቲ መሆኑንም ገልጸዋል። ከተማዋን በለውጥ ጉዞ ናት ያሉት አቶ ጎሹ እንዳላማው ፓርቲው ምርጫውን ካሸነፈ ይህን የለውጥ ጉዞ በተሻለ በማስቀጠል ከተማዋን የኢንቨስትመንት መዳረሻ የማድረግ ልማቶቿን የበለጠ በማፋጠን የዜጎቿን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ይሰራል ነው ያሉት።

በምረጡኝ ቅስቀሳ መርሐ-ግብሩ ላይ በከተማዋ የፓርቲው ዕጩ፣ አባላት እና ደጋፊዎች ወጥተው ተሳትፈዋል።

በከተማ አስተዳደሩ ፓርቲው አቶ ተመስገን ጥሩነህን የብልጽግና ፓርቲ የባሕር ዳር ከተማ ምርጫ ክልል የህዝብ ተወካዮች፣ አቶ አረጋ ከበደ እና ወ/ሮ ሰላማዊት አለማየሁን የክልል ም/ቤት ዕጩዎች በማድረግ በ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ እንደሚወዳደርም ተመላክቷል።

ብልጽግና ፓርቲ "የስንዴ ነዶ" የ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ምልክቱ ማድረግ ይፋ ማድረጉ የሚታወስ ነው።

በሳሙኤል ወርቅአየሁ
#ebc #ethiopia #prosperityparty #demonstration

30 days ago

No replys yet!

Be the first to share what you think — your comment will appear here.