Logo
FBC
የሙዚቃ አርበኛው ጥላሁን ገሠሠ……
------------------------
ታላቁ የሙዚቃ ሰው ለግማሽ ምዕተ ዓመት በዘለቀው የሙያ ሕይወቱ ያልዳሰሳቸው ርዕሠ ጉዳዮች የሉትም፡፡

ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ሁነቶች ሁሉ አልቀሩትም፡፡

አርቲስቱ በረዥሙ የድምፃዊነት ሕይወቱ ዘመን የተጫወታቸውን ዘፈኖች ትክክለኛ ቁጥር ደፍሮ መናገር የሚችል ሰው የለም።

ከባንዶች ጋር አልያም በመድረክ የተጫወታቸው ነገር ግን የመቀረጽ ዕድል ያላገኙ ብዙ ዘፈኖች ሊኖሩ እንደሚችሉ ይታመናል።

ቀድሞም በልጅነቱ አንጎራጓሪ የነበረው ታላቁ የሙዚቃ ሰው፣ የድምጻዊነት ሕይወቱን በይፋ የጀመረው 1947 ሀገር ፍቅር ማኅበር ሲቀጠር ነው፡፡

በሀገር ፍቅር ማኅበር የሁለት ዓመት ተኩል አካባቢ ቆይታው፣ ጥላ ከለላዬ፣ ጽጌረዳ ነሽ፣ ደጉ ንጉሥ እና ፍቅሬ ሰውነቴ የተሰኙ ዘፈኖችን ለህዝብ አቅርቦ ተወዳጅነትን አትርፎ ነበር።

በክብር ዘበኛ ኦርኬስትራ አባልነት ከተቀጠረ በኋላ ከ1950ዎቹ የመጀመሪያ ዓመታት ጀምሮ እስከ 1960ዎቹ አጋማሽ ድረስ በክብር ዘበኛ ኦርኬስትራ አጃቢነት ተጫውቷል።

በመቀጠልም ከክብር ዘበኛ ኦርኬስትራ ወደ አንደኛ ክፍለ ጦር ወይም የማዕከላዊ ዕዝ የሙዚቃ ባንድ ተቀላቅሎ የባንዱ ኮከብ ድምጻዊ ሆኖ እስከ 1970ዎቹ መጨረሻ ድረስ ቆይቷል።
#በምድር ጦር ኦርኬስትራ ፡-ጩኸቴን ብትሰሙ፣ እኔ ነኝ ወይ አንቺ፣ አይከዳሽም ልቤ እና ማስታወሻ፣
#በፖሊስ ኦርኬስትራ፡- ሰው ማንን ይመስላል እና ስማ ፣
#በሬይንቦው ባንድ፡- በይ ደህና ክረሚ እና ስንብት ፣
#በኤግዚቢሽን ባንድ፡- የኔ ፍላጎቴ እና በደህና እስኪገጥመን ፣
#በሙላቱ አስታጥቄ ባንድ፡- ኩሉን ማን ኳለሽ፣ አለኝታዬ፣ ላንቺ ብዬ፣ ስትሄድ ስከተላት፣ ትዝ አለኝ የጥንቱ እና የሀገሬ ሽታን ፣
#ከአይቤክስ ባንድ ጋር፡- ውበትሽ ይደነቃል፣ ጽጌረዳ፣ አካም ነጉማ፣ የቆለኛ ልጅ፣ ፍቅሬ ሆይ ያላንቺ እና ሌሎች አምሥት ዘፈኖች የሚገኙበትን ካሴት ሰርቷል፡፡
#ሮሃ ባንድ ፡- በ1980 የ13 ወር ፀጋ እና በ1984 ደግሞ እንቆቅልሽ የተሰኙትን ካሴቶችን የሰራ ሲሆን፣ በ1981 ጥላሁን፣ ብዙነሽ፣ ማህሙድ እና ሒሩት በጋራ ያወጡት ካሴትም በሮሃ ባንድ የታጀበ ነው።
#በዋሊያስ ባንድ፡- ከሌለህ የለህም እና ይቺ ናት ጨዋታ አልበሞች የታጀቡት ደግሞ በዋሊያስ ባንድ ነው።

ጥላሁን ሀገር ወዳድነትን የሚያጎሉ በርካታ ዘፈኖችን ተጫውቷል። ከተጫወታቸው ሀገራዊ ዘፈኖች ውስጥም በ1969 የተጫወተው "አጥንቴም ይከስከስ" እንዲሁም በ1979 በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ስቱዲዮ ተቀርፆ ለሕዝብ የቀረበው "ቃል ኪዳን" የተሰኘው ዘፈን ለየት ብለው ይታወሳሉ። "ቃል ኪዳን" ባሕር ማዶ የሚኖሩ ወገኖች ወደ ሀገር ቤት እንዲመለሱ በጥላሁን ጥበባዊ አንደበት የቀረበ "የእናት ሀገር ጥሪ" ነበር ማለት ይቻላል።

በሀገር ፍቅር ማኅበር "ጥላ ከለላዬ ኢትዮጵያ ሀገሬ"ን በመጫወት በይፋ የተጀመረው የጥላሁን የግማሽ ምዕተ ዓመት የሙዚቃ ሕይወት "ቆሜ ልመርቅሽ" በሚሰኘውና ሕይወቱ ከማለፉ በፊት ባስቀረፀው የመጨረሻው አልበም ነው የተደመደመው።

ጥላሁን በጥበብ ሕይወቱ ስለ ኢትዮጵያ ሲቀኝና ሲዘምር ኖሯል፡፡ ልዩ የሀገር እና የሕዝብ ፍቅርንም አስተምሮናልም፡፡

በድምፁ ሐውልቱን ሲቀርጽ የኖረው ታላቅ ከያኒ ዛሬ በአዲስ አበባ የተሰራለት ሐውልት በይፋ ተመርቋል፡፡

ታላቁን የጥበብ ሰው ፋና ሚዲያ ኮርፖሬሽን ከቤተሰብ እና ከወዳጆቹ ጋር በመሆን በየአመቱ መስከረም ላይ በትንፋሼ ኮንሰርት እንደሚዘክረው ይታወቃል፡፡

5 months ago

No replys yet!

Be the first to share what you think — your comment will appear here.