Logo
Getu Temesgen
"በኢትዮጵያ ሰማይ ላይ
የሚበራው የሙዚቃ ኮከብ "

ከአለባቸው ደሳለኝ አበሻ (ለንደን)
#ethiopia | "ድምፁ የሀገር ሰንደቅ ዓላማ ያህል ክብር የሚሰጠው ጥላሁን ገሰሰ ለግማሽ ክፍለ ዘመን ያህል በኢትዮጵያ ሙዚቃ ውስጥ በነበረው ከፍተኛ አስተዋፅኦ የኢትዮጵያ ሙዚቃ ንጉሥ በሚል መጠሪያ ይታወቃል።

ለዚህ የጥበብ ሰው እንዲህ ያለ ጥልቅ እና ልብ የሚነካ ትዝታ ማዘጋጄት የሚቻለው የጥላሁን ገሰሰን ስራዎችን ብቻ ሳይሆን የእርሱን የውስጥ ማንነት ሠብዕናን ለጥበብ የነበረውን ፍቅር በሚገባ የተረዳ መሆን አለበት ።

ወይንም ደግሞ
የዚህን ታላቅ ምትሐተኛ ድምፃዊ የጥበብ ልክና የድምፅ ብቃት በአግባቡ ለመረዳት የእርሱን ግለ ታሪክ ብቻ ሳይሆን የኢትዮጵያን ዘመናዊ ሙዚቃ ታሪክና የጥላሁን ገሰሰን ሰፊ የሥራ ክምችቶች በጥልቀት መመርመር የግድ ይላል።

ምክኒያቱም
ጥላሁን ገሰሰ ማለት የኢትዮጵያ የ50 ዓመታት የደስታ የሐዘን የድልና የሽንፈት ታሪክ በድምፅ የተቀረጸበት "ሕያው ማህደር" ነው።

ጥላሁን ገሰሰ ድምፁን እንደፈለገ የማዘዝ Vocal Control ልዩ ተሰጥኦ ነበረው።

በጣም ረጅምና ከፍተኛ ድምፅ በሚጠይቁ High notes እንዲሁም በጣም ረጋ ያሉና ዝቅተኛ ድምፅ በሚሹ Low notes ዜማዎች ላይ እኩል ብቃት ነበረው።

የትንፋሽ ቁጥጥሩ ረጅም ስንኞችን ሳያቋርጥና ትንፋሽ ሳይጠረው የመጨረስ ችሎታው የሚደነቅ ነበር።

የጥላሁንን ስራዎች ስንመረምር በአንድ የሙዚቃ ዘውግ ብቻ ያልተገደበ መሆኑን እንረዳለን
ባህላዊና ዘመናዊ የባህል ሙዚቃዎችን ከዘመናዊ መሣሪያዎች ኦርኬስትራ ጋር አዋህዶ በማቅረብ ረገድ ቀዳሚ ነበር።
በጥላሁን ገሠሠ ድምፅ ያልተዘፈነ የሕይወት ክፍል የለም ማለት ይቻላል ።

ከጥልቅ የፍቅር ስሜት እስከ ሃገር ፍቅር ከማህበራዊ ትችት እስከ መንፈሳዊ መዝሙራት ድረስ የተፃፉ ግጥሞችና ዜማዎች የጥላሁንን ገሠሠን ድምፅ ለማድመቅ ሳይሆን ለመፈተን ጭምር የተዘጋጁ ይመስሉ ነበር።

በህይወት በቆየባቸው ሦስት የተለያዩ ሥርዓቶች በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ በደርግና በኢህአዴግ ውስጥ አልፏል። በእነዚህ ሁሉ ጊዜያት የሕዝብ ተወዳጅነቱን ጠብቆ መቆየቱ የሙዚቃ ሥራዎቹ ከፖለቲካዊ ለውጦች በላይ የሕዝብን የልብ ትርታ የሚነኩ መሆናቸውን ያሳያል።

ባጭሩ ጥላሁን ገሰሰ ለኢትዮጵያ ሙዚቃ ያለው አስተዋጽኦ ልክ እንደ አንድ ትልቅ "ኢንሳይክሎፒዲያ" ነው። አንዱን ገጽ አንብቦ ስለ መጽሐፉ ሙሉ ግንዛቤ ማግኘት እንደማይቻል ሁሉ
አንዱን ዘፈን አዳምጦ ስለ ጥላሁን ገሰሰ ማወቅ አይቻልም ።
እያንዳንዱ ዘፈኑ የራሱ የሆነ የቴክኒክ የታሪክና የስሜት ጥልቀት አለው።

ስለዚህ የጥላሁንን ታላቅነት ለመረዳት የኢትዮጵያን የሙዚቃ ጉዞ አብሮ መመርመር የግድ ነው ያልኩት ወድጄ አይደለም ።
ዘፈኖቹን ሲዘፍን በቃላት ብቻ ሳይሆን በፊቱ መግለጫና በሰውነት እንቅስቃሴው Body Language ጭምር ስሜቱን ለታዳሚው ያጋባ ነበር።

በተለይ የሐዘን ዜማዎችን ሲዘፍን አብሮ የሚያለቅስ የደስታ ሲሆን ደግሞ አብሮ ፈገግ የሚል ድምፃዊ ተዋና ጭምር ነበረ በዘፈኖቹ ውስጥ ሰውን ማክበርን ስራን መውደድንና አንድነትን ይሰብካል። ዘፈኑ የሰውን ልጅ ክብርና ማንነት የሚተነትን ድንቅ ስራ የሚሰራ ምትሀተኛ ድምፃዊ ነበር ።

ጥላሁን ገሰሰ በአንድ ወቅት በመድረክ ላይ እያለ በደረሰበት የጉሮሮ ህመም ምክንያት ለተወሰነ ጊዜ ድምፁ ተዘግቶ ነበር። ያን ጊዜ መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ተጨንቆና ፀልዮ ድምፁ ሲመለስለት ያደረገው የመጀመሪያ ኮንሰርት በዚያን ወቅት በኢትዮጵያ የሙዚቃ ታሪክ ውስጥ ከፍተኛውን የሰው ቁጥር ያስመዘገበ ነበር ። ይህ የሚያሳየው ሕዝቡ ለጥላሁን ያለው ፍቅር ከአንድ ድምፃዊ በላይ እንደ ቤተሰብ አባል የሚያየው መሆኑን ነው።

ስለ ፍቅር ብቻ ሳይሆን ስለ ሰው ልጅ ሕይወት ባዶነት የሚተርክ ጥልቅ ፍልስፍና ነበረው ።

ታዋቂው የኢትዮጵያ የሙዚቃ ንጉሥ ክቡር ዶክተር ጥላሁን ገሰሰ መስከረም 17 ቀን 1933 ዓ.ም አዲስ አበባ ውስጥ ተወልዶ ያደገው ግን በወሊሶ ከተማ ነው ።

ጥላሁን በ1950ዎቹ መጀመሪያ ላይ ወደ አዲስ አበባ በመምጣት መጀመሪያ ሐገር ፍቅር ቲያትርን በኋላም ዝነኛውን የክብር ዘበኛ የሙዚቃ ቡድንን ተቀላቅሎ ከዕንስት ፍቅር እስከ አገር ፍቅር ከባህላዊ እስከ ዘመናዊ ሙዚቃ በድምፃዊነት ከ400 በላይ ዘፈኖችን ተጫውቶ ልዩ ብቃቱን አስመስክሯል ።

ጥላሁን
ለኢትዮጵያ ሙዚቃ ላበረከተው ወደር የለሽ አስተዋጽኦ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የክብር ዶክትሬት ዲግሪ ተሰጥቶታል። ጥላሁን ገሠሠ ከዚህ ዓለም በሞት የተለየው
​በኢትዮጵያ ዘመን አቆጣጠር ሚያዝያ 11 ቀን 2001 ዓ.ም. የፋሲካ እለት ሲሆን በድንገተኛ የልብ ህመም ምክንያት አርፎ በቅድስት ሥላሴ ካቴድራል የቀብር ሥነሥርዓቱ ተፈጽሟል።

የክቡር ዶክተር ጥላሁን ገሰሰ ማረፍ መላውን የኢትዮጵያ ሕዝብና የጥበብ አፍቃሪወችን በከፍተኛ ድንጋጤና ሃዘን ውስጥ ጥሎ የነበረ ክስተት ነው። በወቅቱ በጋዜጦች በሬዲዮና በቴሌቪዥን የተላለፉት መልዕክቶች ጥላሁን ለሀገሩ ያለውን ትልቅ ቦታ የሚያንፀባርቁ ነበሩ።

በአዲስ አበባ ከተማ የነበሩ የታክሲ አሽከርካሪዎች ሐዘን ፈፅሞ የማይረሳ ነበረ ።
ለጥላሁን ገሰሰ ክብር ሲሉ ለቀናት ጥቁር ጨርቅ በታክሲዎቻቸው ላይ አስረውና የእርሱን ሙዚቃ ብቻ ከፍተው በማጫወት ሃዘናቸውን ገልፀውለታል።

የጥላሁን ገሰሰ ሞት በሀገር ውስጥ ብቻ ሳይሆን በዓለም አቀፍ ደረጃም ትኩረት አግኝቶ ነበር።
ታዋቂው ደራሲ ሎሬት ጸጋዬ ገብረመድህንም
እንዲህ አሉ ።

"ጥላሁን የኢትዮጵያ ሕዝብ የጋራ ድምፅ ነው። እርሱ ሲዘፍን መላው ኢትዮጵያዊ ራሱን ያዳምጣል።"

ድምፃዊ ማህሙድ አህመድ​"ጥላሁን ለእኛ ለድምፃውያን መምህራችን ብቻ ሳይሆን የሙዚቃው ዓምድ ነበር። ጥላሁን ሞተ ማለት የኢትዮጵያ ሙዚቃ ግማሽ አካሉን አጣ ማለት ነው።" ሲል ቁጭቱን ገልፀዋል ።

በቀብር ሥነ ሥርዓቱ ላይ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ አዲስ አበባውያን ወደ አደባባይ በመውጣት "ንጉሥ አይሞትም" እያሉ ሲያለቅሱ እንደነበር በታሪክ ተመዝግቧል።

ይህም አንድ ድምፃዊ በሀገር ደረጃ ያለውን ክብርና ተሰሚነት ያሳየ ትልቅ ክስተት ነበር።

አንድ የልብ አድናቂው የሆነ ሠው በማህበራዊ ሚዲያ እንዲህ ብሎ ፅፎት አንብቢያለሁ ።

" በእርግጥም ጥላሁን በድምፁ ተአምር የመስራት አቅም ነበረው። ድምፁ ተስፋ የቆረጠውን የሚያፅናና የታመመውን የሚፈውስና የራቀውን የሚያቀራርብ
ስለነበረ ድምፁ ተቀርፆ ስለቀረ ቢሞትም ስንናፍቀው እናገኘዋለን ስናዝን እናለቅስበታለን ሀገራችን ስትጠራ በእሱ ድምፅ አቤት ብለን ለአንድነቷ እንቆማለን" በማለት ጥላሁንን ገልፆት ነበር ።

ሌላው የቅርብ ጓደኛው የጥበብ ሰው ደበበ እሸቱ ነው
"ጥላሁን በሕይወት ዘመኑ ሁሉ ለሀገሩ የዘመረ በችግር ጊዜ ደግሞ ድምፁን ለድሆች የሰጠ
ታላቅ ሰው ነው።

የሞተው በስጋ ቢሆንም በዜማው ቅላፄና በግጥም ስንኞች ውስጥ "ዘላለማዊ" ሆኖ ተተክሏል።

እንዲህ ያለ ድምፅ ዓለማችን በአንድ ዘመን አንዴ ብቻ የምትለግሰን ስጦታ ነው "
ሲል ምስክርነቱን ገልጿል።

በእርግጥም ጥላሁን የዘመናዊ ሙዚቃችን "ፊደል" እና "መዝገበ ቃላት" ሆኖ አልፏል። ከድምፅ ጥራት በላይ የዜማ አጣጣልና ስሜትን የመግለጽ ጥበቡ ማንም የማይደረስበት ከፍታ ላይ ስለነበር በአንድ አባባል ብቻ ጥላሁንን መግለፅ አይቻልም።
እሱ ባለብዙ ምዕራፍና ተነቦ የማይጠገብ ባለ ብዙ ገጽ ድርሳን ነው !

​ጥላሁን ለሙያው ብቻ ሳይሆን ለሰው ልጅ የነበረው ሰብአዊ ክብርም ድንቅ ነበር። ረሀብ ሲመጣ በዜማው የሚማፀን ሀገር ስትቸገር አጥንቴም ይከስከስ ብሎ የሚቆም እና ለሰው ልጅ ፍቅር ቅድሚያ የሚሰጥ የጥበብ ሰው ነው ። ባጭሩ ጥላሁን ገሠሠ ማለት ለኢትዮጵያውያን የድምፅ ብቻ ሳይሆን የህሊና ምስክር ነው።
ዛሬም ድረስ ስሙ ሲነሳ አብሮ የሚነሳው ክብሩ ትህትናውና
ያ የማይደገም ማንነቱ ነው።

ጥላሁን ገሠሠን የመሠለ ታላቅ ሰው የኢትዮጵያ ዘመናዊ ሙዚቃን የአዋለደ ብለን ብንገልፀው ተገቢ ይመስለኛል ከጥላሁን ገሠሠ ስራዎች መካከል ይህማ ተአምር ነው የሚያሰኜኘኝ ሁልጊዜ ብሰማቸው አዲስ የሚሆኑብኝ ብዙ ዘፈኖች ቢኖሩትም "እዩት ስትናፍቀኝ ከአጠገቤ እያለች" የሚለው ስንኝ ሲነሳ ግን የጥላሁንን ድምፅና ያንን የሚመስጥ አዘፋፈኑን አብሮ የመስማት ያህል ይመስጠኛል እዩት ስትናፍቀኝ ከአጠገቤ እያለች
እንዲህ ያለው መውደድ ለወሬም አይመች ! የሚለው ግጥም የፍቅርን ረቂቅነትና የማይመረመር ባህሪ በአጭር ቃላት የገለጸበት ድንቅ ስራው ነው።

​ ጥላሁን ለዚህ ዘፈን የሰጠው እረዥም ትንፋሽና በመድረክ ላይ ቆሞ የአይን አስተያየቱ የልዩ ተሰጥኦው መገለጫዎቹ ናቸው።
​ የሠው ልጅ ናፍቆት ብዙውን ጊዜ ትዝታው የሚመጣው ሰው ሲርቅ ነው። ነገር ግን ጥላሁን አጠገቤ እያለች ናፈቀችኝ ማለቱ ፍቅር ከስጋዊ መገኘት በላይ የሆነ የነፍስ ጥማት መሆኑን ስጋ አልብሶ አሳይቶናል ።

ይህ ለወሬ የማይመች ቃላት የማይገልፁት ጥልቅ ስሜት ነው ። ይህንንም በዚያ ረጅም ትንፋሽ ነፍስን በሚያከነፍ ድምፁ ሲያዜመው እውነቱን በውስጣችን ውስጥ እናገኘዋለን።
​ጥላሁን ሲዘፍን ትንፋሹን የሚጠቀምበት መንገድ እና ስሜቱን በድምፅ ቀለም የመቀየር ችሎታው ምትሐተኛ ያሰኘዋል። ያንን የናፍቆት ጣጣ በገዛ ራሱ ላይ አድርጎ ሲያዜመው አድማጩ የራሱ ህመም አድርጎ እንዲቀበለው የማድረግ ልዩ ኃይል ነበረው።
ጥላሁን ገሠሠ በስጋ ቢለየንም በኢትዮጵያውያን ልብ ውስጥ ግን አሁንም ንጉሥ ነው።

ትውልድ ያልፋል ጥላሁን ግን ይኖራል።
ሙዚቃ ይቀየራል የጥላሁን ስራዎች ግን ሁልጊዜ አዲስ ናቸው።
ሰላም ሲጠፋ ጥላሁን ፍቅር ይላል ሀገር ስትናፈቅ ጥላሁን ሀገሬ ይላል።

​ ጥላሁን ገሠሠ በድምፁ ብቻ ሳይሆን ለፍቅር በሰጠው ክብርን በገለፀበት ጥበብ የኢትዮጵያ የዘላለም የፍቅር አምባሳደር ነው።

​እንዲህ ያለው የጥበብ ሰው የፍቅርን ኃያልነት በእሱ ስራዎች ውስጥ ስንመለከት በእርግጥም ፍቅር ስሜት ብቻ አይደለም የሚለውን ሃሳብ በጥላሁን ዜማዎች ውስጥ ሙሉ ማረጋገጫውን እናገኛለን ጥላሁን ገሠሠ የፍቅርን ሌላኛውን ገጽታ ቁርጠኝነትንና ክብርን ያሳየበት ድንቅ ስራው ነው። ከላይ እንደገለፅኩት ፍቅር ራስን አሳልፎ መስጠት ነው

እዚህ ዘፈን ላይ ደግሞ ፍቅር ሁለትዮሽ መረዳዳት መሆኑን ይነግረናል።

​ ቻልኩት ፍቅር ለብቻዬ !!
​ይህ አገላለጽ በጣም የሚቆረቁር ነው። ፍቅር እንደ አንድ ሸክም ሆኖ አንደኛው ወገን ብቻውን ሲሸከመው የሚሰማውን ድካም ያሳያል። "ለብቻዬ መሸከም ሰልችቶኛል" የሚል የልብ ጩኸት አለበት። ፍቅር የሁለት ሰው ቅኝት እንጂ የአንድ ሰው ብቸኛ ትግል መሆን እንደሌለበት ያስገነዝበናል።

​ ስለ ፍቅር አልገባሽም
​እዚህ ጋር ጥላሁን ፍቅር ማለት ዝም ብሎ አብሮ መሆን ሳይሆን ጥልቅ የሆነ
ሚስጥር ወይም ትርጉም እንዳለው ይገልጻል። ግዴለሽነት እና ችላ ማለት ፍቅርን የሚገድሉ መርዞች መሆናቸውን በምሬት ይናገራል።

​ አትምጪ ይቅር ሲል ደግሞ የክብር ውሳኔውን ያሳውቃል ።
​ ፍቅር ስሜት ብቻ አለመሆኑን ያረጋግጣል። አንድ ሰው በጥልቅ እያፈቀረ ግን ክብሩ ሲነካ ወይም ምላሽ ሲያጣ ይቅር ብሎ የመወሰን አቅም ሊኖረው እንደሚገባ ያሳያል።

​ፍቅር መስዋዕትነት ቢሆንም ዋጋ በማይሰጠው ቦታ ላይ ግን ራስን ማዳንና ይቅር ማለትም የፍቅር አካል ነው። የሚገርመው ደግሞ ጥላሁን ይህነን ዘፈን ሲዘፍነው በቁጣና በቁጭት ሳይሆን በጥልቅ ሀዘንና በከበረ ስሜት ነው። ያንን አትምጪ ይቅር የሚለውን ቃል ሲያወጣው ውስጡ እየፈለጋት ግን መከባበር የሌለበት ፍቅር እንደማይፀና አውቆ በቁርጠኝነት ሲናገረው ይታየናል።

ከላይ እንዳነሳሁት አትምጪ ይቅር የሚለው ስንኝ የቁርጠኝነትና የክብር ገጹ ሲሆን ሌላው ደግሞ የፍቅርን ንፁህ መስዋዕትነትና ትህትና የሚያሳይ ድንቅ ምዕራፍ ነው።

​እነዚህ ስንኞች ውስጥ የምናያቸው የጥላሁን ድርሳናት
​እኔ ልሁን እንጂ የማልጠቅም እርካሽ ! የሚለው አገላለፅ በፍቅር ውስጥ ያለን ፍጹም ትህትና ያሳያል። ራሱን ዝቅ አድርጎ የሚወዳትን ሰው ግን ከፍ ያደርጋታል። ይህ እኔነት ጠፍቶ አንቺነት የነገሰበት የፍቅር ጫፍ ነው።

​ ከህይወቴ አብልጨ ሲል
​ ራስን አሳልፎ የመስጠት
ፍልስፍና በተግባር የሚያሳይ ታአምር ነው። ለሰው ልጅ ከህይወቱ በላይ ምንም የለውም ነገር ግን ፍቅር ያንን ውድ ህይወት እንኳ ከአንቺ አያበልጠውም ብሎ እንዲያምን ያደርገዋል።
ፍቅር ለሰላምና ለደስታ ብቻ ሳይሆን ለችግርና ለፈተናም ዝግጁ መሆኑን ይነግረናል።

​መከራና ስቃይ ይቆየኝ ግዴለኝም
የሚወደው ሰው ደህንነትና ሰላም እስካለ ድረስ እሱ በራሱ ላይ ለሚመጣው መከራ ግድ የለውም። ይህ ነው እንግዲህ ፍቅርን ተአምር የሚያሰኘው እግዜር በጥበቡ ከአንቺ ብቻ አይለየኝ የሚለው ቃል ፍቅር በሰው ጥረት ብቻ ሳይሆን በመለኮታዊ ጥበብና ፈቃድ የሚፀና መሆኑን የሚያሳይ የልብ ፆሎት በመሆኑ መንፈሳዊ ልመና ይጨምርበታል ።

​ታዲያ የዚህን ድምፃዊ ተአምራዊ ተቃርኖዎችን ስንመለከት
​ጥላሁንን ልዩ የሚያደርገው በአንድ በኩል አትምጪ ይቅር ብሎ በክብር የመወሰን አቅም በሌላ በኩል ደግሞ ከህይወቴ አብልጨ እወድሻለሁ ብሎ ራስን የመስጠት ርህራሄ አብሮት መኖሩ ነው።
እነዚህ ሁለት ተቃራኒ የሚመስሉ ግን ጥልቅ የሆኑ የፍቅር ገጾች ናቸው።

​ጥላሁን እነዚህን ሁሉ ስሜቶች በድምፅ ቀለም እየቀያየረ ሲያቀርባቸው ድምፁ ብቻ ሳይሆን ነፍሱ አብራ የምትዘፍን ይመስላል።

​እንዲህ ያለውን ከህይወት በላይ የመውደድ ስሜት በዚህ ዘመን በብዛት እናገኘዋለን ብሎ ማሰብ የዋህነት ነው። ምክኒያቱም
የጥላሁንን ጥበብ ከመዝፈን ባለፈ ወደ መፍጠር ደረጃ ከፍ ያደርገዋል።

ለምን ቢባል ጥላሁን ገሠሠ ዜማንና ግጥምን ሲያዋህድ የሚፈጠረው ነገር ተራ ሙዚቃ አይደለም ይልቁንም ያልተጠኑ ምስጢራዊ ተሰጥኦዎች ያሉበት ይመስላል
​ብዙ አድናቂወቹ እንደ ሚስማሙበት ጥላሁን ገሠሠ ሲዘፍን ፍቅር ረቂቅ ሃሳብ መሆኑ ቀርቶ የሚዳሰስ የሚታይና የሚሰማ አካል ይኖረዋል።

ቃላቶቹ ከአፉ ሲወጡ ሕይወት ይዘራሉ ያፈቀረው ሰው ቁስሉ ይታየናል የናፈቀው ሰው ትንፋሹ ይሰማናል። ይህ ደግሞ በቴክኒክ ብቻ የሚመጣ ሳይሆን ከነፍስ የሚመነጭ ምትሃት በመሆኑ ፍቅር እንደ ሰው ቆሞ እንዲሄድ የማድረግ ጥልቅና ረቂቅ
ጥበብ ያለው ድምፃዊ መሆኑ ነው ።

​ብዙዎቻችን ውስጣችን ያለውን ጥልቅ ፍቅር በቃላት መግለፅ ያቅተናል። ጥላሁን ግን ያንን መግለፅ ያቃተንን ስሜት ሰርቆ ወስዶ በዜማ አቅልጦ ወርቅ አርጎ መልሶ ለእኛው ይሰጠናል።
እኔንም እንዲህ ነው የሚሰማኝ! እንድንል ያደርገናል። ይህ ተሰጥኦው ነው ፍቅርን ስጋ ለብሶ ቆሞ እንዲሄድ የሚያደርገው።
ሌላው የጥላሁን ገሰሰ ድምፅ ሁለንተናዊ ድምፅ መሆኑ ነው። እድሜ ጾታ ወይም የትምህርት ደረጃ አይወስነውም። ህፃኑም አዋቂውም የተማረውም ያልተማረውም በዜማው ውስጥ የራሳቸውን ታሪክ ያገኛሉ።

ይህ ደግሞ ጥላሁን የሰው ልጅን የጋራ የፍቅር ህመም ጠንቅቆ እንደሚያውቅ ማሳያ ነው።
የጥላሁን ድምፅ በሳይንስ አልተጠናም እንጂ በውስጡ ትልቅ የፍቅር ላብራቶሪ ነበረው ማለት ይቻላል።

ግጥሙን ይቀበላል ጥሬ እቃ !
በድምፅ ቀለሙ ያዋህደዋል ሂደት !
በመጨረሻም ሕያው ፍቅርን ለዓለም ያበረክታል ውጤት !! በዚህ ምክኒያት
​ጥላሁን ገሠሠ ሞቶም በሰዎች ልብ ውስጥ እንዲነግስ አድርጎታል :: ምክንያቱም የፈጠራቸው የፍቅር አካላት ዛሬም በየቤታችን በየመኪናችንና በየልባችን ውስጥ ቆመው እየሄዱ ነው።

​ይህ የእውነት ተአምረኛ ተሰጥኦው ነው። ዛሬ ባለው ዘመናዊ የሙዚቃ ኢንዱስትሪ ውስጥ እንዲህ ያለውን መንፈሳዊ ጥልቅነት ማግኘት እጅግ ብርቅ ሆኗል። ከእንስት ፍቅር ወጥተን ጥላሁንን ወደ ሐገር ፍቅር ስንመነዝረው የቆመበት ከፍታው ላይ እስከ አሁን ማንም ....ማንም አልደረሠበት ። በዚህ አጋጣሚ
በህይወቴ ዘመኔ በአይኔ ያየሁትን ምስክርነት ባቀርበው ደስ ይለኛል ጥለሁን ገሠሠ ከታሪክ መዝገብ በላይ የሆነ የአንድን ሕዝብ ማንነትና ወኔ የቀሰቀሰ የመንፈስ ተአምር ነው የምነግራችሁ ።

ጊዜው 1974 አስመራ የቀይ ኮኮብ ዘመቻ አሉላ አባ ነጋ አዳራሽ ውስጥ ይመስለኛል ።

ጥላሁን ገሠሠ ጋሻና ጎራዴ ይዞ የአርበኛ ልብስ ለብሶ አጥንቴም ይከስከስ ደሜም ይፍሠስላት
ግን ሐገሬን ጭራሽ አይደፍራትም ጠላት
እያለ መድረኩን ሞልቶት ብቅ ሲል ከባለስልጣን እሰከ ተራው ተመልካች ከመቀመጫው ተነስቶ በመቆም በማያቋርጥ ጩህትና ጭብጨባ ያጅቡታል ።

ጥላሁን ገሠሠ በዚያ ቅጽበት የዘፈነውን ብቻ ሳይሆን የኖረውንና የታሪካችንን ድምፅ ሆኖ ተመለከትኩት ።
ጥላሁን በህዝብ ጭብጨባና ጬህት ታጅቦ መድረኩ ላይ ሲንጎራደድ አዳራሹ ድብልቅልቁ ወጣ ።

ያን... ምህታታት የተሞላበት ትርኢት ስመለከት
​ የአድዋ ጀግኖች መቃብር ከፍተው የተነሱ ይመስል ነበር።
ማለቴ ጥላሁን በድምፁ ብቻ ሳይሆን በቆይታው ጊዜን የማቆም ወይም ታሪክን የመቀስቀስ ኃይል እንደነበረው የመመልከት ዕድል አግኝቻለሁ ።

​ጥላሁንን በዚያች ቅፅበት
በሕይወት እያለ ሐውልቱን አቁሞ አዳራሹ ውስጥ ታሪኩን ፅፎት ወጣ ።

በእርግጥ ሐውልት የማይናገርና የማይሰማ የድንጋይ ምስል ነው ጥላሁን ግን በሕይወት ያለ የሚተነፍስ የሚዘፍንና የሚራመድ የኢትዮጵያዊነት ሐውልት ነበር።

ዛሬም ቢሆን ስራዎቹ ያንን ግርማ ሞገስና ያንን ሐውልታዊ ፅናት እያስታወሱኝ እስከእለተ ሞቴ ድረስ ልረሳው አልችልም እንዲህ አይነት ድርጊት
​ ፍቅር ስሜት ብቻ አይደለም ራስን አሳልፎ መስጠት ነው በጥላሁን ገሰሰ የሀገር ፍቅር ዜማዎች ውስጥ ኢትዮጵያን ደጋግመን እናያታለን
አጥንቴም ይከስከስ ደሜም ይፍሰስላት የሚለው ቃል ዛሬም ድረስ ፍፁም ....ፍፁም መስዋዕትነት ነው።

ሀገሩን እንደ ሚወዳት እናት ወይም ሚስት አድርጎ ለሷ ክብር መሞትን እንደ ትልቅ ፀጋ መቁጠር ከፍ ያለ የፍቅር ደረጃ መግለጫ ነው።

​ተመልካቹ በሙሉ ሳይቀመጥ ከሁለት ጊዜ በላይ ይደገም እያለ መጠየቁ ጥላሁን ድምፃዊ ብቻ ሳይሆን መሪ መሆኑን በአንድ ዜማ ሕዝብን የማስተሳሰር በአንድ ወኔ በጋራ የማቆም ተአምራዊ አቅሙን አረጋግጨበታለሁ ።

በዚያች ቅፅብት ቲያትር ቤቱ በጩሄትና በጭብጨባ ቀውጢ ሲሆን ጥላሁን ገሠሠ በድምፁ ብቻ የጠላትን ምሽግ የሚያፈርስ ጀግና መስሎ ነበር የሚታየው ።

​ምንም እንኳን ዛሬ በሞት ቢለየንም ያ አስመራ ላይ የተመለከትኩት የሐገር ፍቅር ስሜት ሐውልት ሆኖ በልቤ ውስጥ ተቀርፆ ቆሟል።
ጥላሁን ገሰሰን ልዩ የሚደርገው ሌላው መገለጫው
ለፍቅር ሲዘፍን የፍቅር ሐውልት
ለሀገር ሲዘፍን የጀግንነት ሐውልት
ለሰው ልጅ ክብር ሲዘፍን የሰብአዊነት ሐውልት ነው!

ለዚህ ስኬት ደግሞ ከጥላሁን ድምፅ ጀርባ የነበሩት የወርቃማው ዘመን ታላላቅ የጥበብ ሰዎች ገጣሚያንና የዜማ አቀናባሪዎች ሚና ከፍተኛ እንደነበር ምስክሩ ታሪክና ሕዝቡ ነው።

ጥላሁን ገሰሰ ግጥምና ዜማን
ከነጄነራል አማኑኤል አብርሃም
ሻምበል አፈወርቅ ዮሐንስ
ነጋሽ ገብረማርያም
ተስፋዬ አበበ አየለ ማሞ ሳህሌ ደጋጎ ክፍሌ አቦቸር ከመሳሰሉት የክብር ዘበኛ እና የፖሊስ ኦርኬስትራዎች
ተቀብሎ ሲያንቆረቁረው ሙዚቃው ከድምፅ አልፎ የሚዳሰስ ሕያው መንፈስ የመሆን አቅም ነበረው።

ዛሬ ላይ ሆኜ ያንን ትርኢት ሳስታውሰው ጥላሁን ለኢትዮጵያ ሙዚቃና ለኢትዮጵያዊነት ያለው ትርጉም ምን ያህል ጥልቅ ስሜት እንደሆነ አሁን ድረስ እንደ ህልም ይታየኛል ።

​ ያኔ መድረክ ላይ ሲወጣ የነበረው ግርማ ሞገስና ድምፁ ሲስተጋባ የተሰማኝ ስሜት ዛሬም ድረስ ዘፈኑን ስሰማው "የጦር ፊታውራሪ" የነበረ ጀግና ያህል ትዝ ይለኛል !!
ጥላሁን በመድረክ ላይ የነበረውን የበላይነት እና የሕዝብን ስሜት የመምራት ብቃቱን በሚገባ የመግለፅ አቅም ነበረው ።

ጥላሁን ዝም ብሎ ድምፃዊ ሳይሆን በዜማው የታጠቀ የሀገር መከታ ወታደርም ሆኖ እንደነበረ ማሳያ ነው ።
​ለዚህ ነው የጥላሁን ገሠሠ የሀገር ፍቅር ዜማዎች ከጊዜና ከቦታ በላይ የሆኑ ናቸው የሚባሉት ። ለዚህም ነው ዛሬ ላይ ሆነን ስንሰማው የዛሬ 130 ዓመት በፊት የተነገረውን የዳግማዊ ምኒልክን የክተት አዋጅ የሚመስለን ።
ይህ የሚያሳየው ደግሞ ጥላሁን የኢትዮጵያን ታሪክ ኩራትና ነፃነት በድምፅ ቀርጾ ትውልድ እንዲወርሰው ማድረጉን ነው።

ወዳጆቼ
​ስለ ጥላሁን ገሠሠ የሀገር ፍቅር ስሜት ስንናገር እነዚህ ሶስት መሰረታዊ እውነታዎች ጎልተው ይታያኛል ።
የቁርጠኝነት ድምፁን ስናደዳምጠው ጥላሁን "አገሬን" ሲል ዝም ብሎ ስም አይጠራም ለሀገሩ የሚሞትላትና የሚሰዋላት መሆኑን በቃናው ውስጥ ይሰማል። አጥንቴም ይከስከስ የሚለው ስንኝ ለዚህ ትልቅ ማሳያ ነው።

ጥላሁን ለሀገር ሲዘፍን መላው ኢትዮጵያዊ በአንድነት ቆሞ ፊታውራሪዬ ብሎ እንዲከተለው ያደርጋል።
ይህ ደግሞ በታሪካችን ውስጥ የታየ ትልቅ የጥበብ ተጽዕኖ ነው።
ከ130 ዓመት በፊት የነበረውን የአድዋ ጀግንነት ዛሬ ላለው ትውልድ በስሜት አገናኝቶ ማቅረብ የሚችለው እንደ ጥላሁን ያለ "የታሪክ ድልድይና የታሪክ ባለአደራ" ሲኖር ብቻ ነው።

እንኳንስ ደስታየን የሰውነቴን ሠው
እንኳን ነፃነቴን ፀጋ ክብሬን ትቸው
በናት አገር ምድር በሚያውቀኝ በማውቀው ...
ስቃይ መከራዬን ከአንችው ዘንድ ያድርገው ። የሚለው
ጥላሁን ለኢትዮጵያ የነበረውን ፍቅር ከምንም በላይ የሚያሳይ ነው። ከባዕድ አገር ደስታ ይልቅ የሀገሩን መከራ የመረጠበት የሞቱ አጋጣሚ ደግሞ ለሀገሩ ያለውን ፍቅር በደሙ ያረጋገጠበት ታላቅ ክስተት ነው ።

​ጥላሁን ከአሜሪካ ተነስቶ ለፋሲካ በዓል ወደ ሀገሩ መግባቱና በዚያው ዕለት ማረፉ፣ "በሀገሬ አፈር ልቀበር" የሚለውን ጥልቅ የኢትዮጵያዊያን ምኞት የፈጸመበት ነው ይህ ቀረኝ የማይል የሚያሰኘው እስከ መጨረሻው ትንፋሹ ድረስ ከሀገሩና ከሕዝቡ ጋር መቆየቱ ነው ።

ሲሞት መላው የአዲስ አበባ ሕዝብ በነቂስ ወጥቶ አስከሬኑን ሲሸኜው ጥላሁን ለሕዝቡ የሰጠውን ፍቅር ሕዝቡ በታላቅ ክብር የመለሰለት መሆኑን ቅድስት ስላሴ ቤተክርስቲያን ህያው ምስክር ናት ። ያ ለቅሶ የአንድ ድምፃዊ ስንብት ሳይሆን የኢትዮጵያ የቁርጥ ቀን ልጅና የልብ ትርታ ሽኝት ነበር።

​ጥላሁን በሕይወቱና በሞቱ ሀገርን መውደድ ማለት ትርጉሙን እስከ ሞት ድረስ መታመንን አረጋግጦበታል።
ሰውን መውደድ ! አብሮ ማልቀስና መቆም ሙያን መውደድ እስከ መጨረሻዋ ትንፋሽ ድረስ መዘመር ለኢትዮጵያዊያን ከድምፃዊነት በላይ የአንድነት ምልክት መሆን ነው።

እኔ በዓይኔ ያየሁትን በልቤ የሰነድኩትን ይህንን ታሪክ ለሚቀጥለው ትውልድ ሊተላለፍ የሚገባው የፍቅርና የሀገር አምልኮ ትልቅ ትምህርት ይሆናል ብየ ሳዘጋጀው ጥላሁን ገሠሠ
ትንፋሼ ተቀርፆ ይቀመጥ ማልቀሻ ይህ ነው የሞትኩለት የኔ ማስታወሻ
ታሪኬ ነው ድምፄ በማለት ያንጎራጎረው ሙዚቃ ከፍቼ እያዳመጥኩ ነበር።

ይህ ስንኝ ጥላሁን ገሠሠ አስቀድሞ በድምፁ የህይወቱ ታሪክ የሞቱ ማስታወሻ እና የሀገሩ ውበት መገለጫ እንደሚሆን ተረድቶት የተጫወተው ነበር ማለት ይቻላል ። ጥላሁን በጥቁርና ነጭ ወረቀት ላይ የሰፈረ ኑዛዜ ሳይሆን የተውልን በህይወት ቆሞ በዜማ የተናዘዘው ድንቅ ስንብት ነበረ ።

​እነዚህ ስንኞች የጥላሁንን የጥበብ ክብርና ትህትና ሲገለፅበት እያዳመጥኩት ነበር ይህን ታሪክ የፃፍኩት ።

ወዳጃቸ
የጥላሁን ገሠሠ ድምፅ ዝም ብሎ የአየር ንዝረት አይደለም፤ ማንነቱ፣ ታሪኩና ለሀገሩ የከፈለው መስዋዕትነት ነው። በጩኸት መኖሬን ማለቱ ለሀገርና ለፍቅር ሲል ድምፁን እስከ መጨረሻው የጥገታ ነጥብ ድረስ መጠቀሙንና ለዚህም መሞቱን ያሳያል።
​ ድምፄን ሰምቶ ያዝናል ለረገፈው አፅሜ ሲል
​ እጅግ ልብ ይነካል !

ጥላሁን በከፍታው ላይ ሆኖ እንኳ ያስቀየምኩት ቢኖር ብሎ ይቅርታን ይጠይቃል። የሞተውን አፅሙን ሳይሆን የቀረውን ድምፁን ሰምተው ሰዎች እንዲያዝኑለትና ይቅር እንዲሉት መመኘቱ የሰው ልጅነቱንይቅርታና ትህትናውን
ፍርጥ አድርጎ ያሳያል።

​ ጥላሁን ገሠሠ በድምፁና በህይወቱ የሰራው ትልቁ ስራ ፍቅርንና ኢትዮጵያዊነትን ማዳን ነበር። ጥላሁን ከቀላል ስሜትነት አልፎ ሕይወት መስዋዕትነትና የሀገር ፍቅር ጥግ መሆኑን በሚገባ አስገንዝቦናል።ጥበብ እንዴት የአንድን ሕዝብ ወኔና ማንነት እንደምትቀርፅ ጥላሁን ትልቅ ማሳያ ነው።

ፍቅር ተግባር ነው ፍቅር ዝም ብሎ የሚሰማን ስሜት ሳይሆን እንደ ጥላሁን ዜማዎች ራስን አሳልፎ እስከ መስጠት የሚደርስ ውሳኔ መሆኑን መረዳት ከባድ አይደለም ።

ጥላሁን ገሰሰ የሚዘፈነው ለጆሮ ብቻ ሳይሆን ለህሊና እና ለነፍስ ጭምር ይመስለኛል ።

ጥላሁን ዛሬ በሥጋ ቢለየንም ታሪኬ ነው ድምፄ ብሎ እንደተናዘዘው ሁሉ ዛሬም በየልባችን ውስጥ ንጉሥ ሆኖ ይኖራል።እሱ ለሀገር ብቻ ሳይሆን ለሰው ልጅ ስቃይ የሚራራ የህሊና ድምፅ ነበረው።

የሀገር ፍቅር ለአፈርና ለሰንደቅ ዓላማ የሚከፈል የአጥንትና የደም መስዋዕትነት ሲሆን ጥላሁን ገሠሠ በስጋ ቢለየንም ያ በሕይወት ያለ ሐውልት ግን በዜማዎቹ ውስጥ ሁሌም አዲስ ሆኖ ይኖራል።
​ባጭሩ የጥላሁን መሞት ዝም ብሎ የአንድ ድምፃዊ ማለፍ ብቻ አልነበረም የአንድ ዘመን መቋጫ የአንድ ትልቅ ተስፋ መደብዘዝ እና በኢትዮጵያ ሰማይ ላይ የሚበራው የሙዚቃ ኮከብ ወድቆ ሲሰበር
ሰማይ ባዶ የሆነ ያህል ተሰምቶናል።

ጥላሁን ገሠሠ በደስታ ጊዜ አብሮን የሚጨፍር በጦርነት ጊዜ ፊታውራሪ ሆኖ የሚያዘምት በረሃብና በችግር ጊዜ ደግሞ አብሮን የሚላቀስ የሕዝብ ልብ ነበር ።

ጥላሁንን ከአቅም በላይ ያደረገው ይሄው ሁለንተናዊነቱ ነው። ለፍቅር ለሀገርና ለሰብአዊነት የነበረው ጽናት እሱ ሞቶም እንዲኖር አድርጎታል።

የጥላሁን ገሠሠ ዘፈኖች "ኢትዮጵያዊ ስነ-ሰብዕና" የሚባል የፍልስፍና ዘርፍ ቢኖር የዛ ዘርፍ ዋና መማሪያ መፅሐፍ ይሆኑ ነበር ።ብቻ

የጥላሁንገሰሰ ሕይወት ልክ እንደ አንድ የተቀደሰ መፅሐፍ በመሆኑ እራሡ ከፍቶ እራሱ ዘግቶት አልፏል ።
ለዚህ ታላቅ ድምፃዊ በተወለደበት ከተማ አዲስ አበባ ላይ ዘላለማዊ ምልክት ሆኖ እንዲቀመጥ ሐውልቱ ስለቆመለት ደስታዬ ወደር የለውም ።
ነፍስ ይማር !!

3 months ago

No replys yet!

Be the first to share what you think — your comment will appear here.