Logo
Zehabesha
(ዘ-ሐበሻ ሕይወት) ከሔኖክ ዓለማየሁ | (ነገ ይህን ዘገባ በቪድዮ እስከምናቀርበው በጽሁፍ እንዲህ ቀርቧል) | የዘ-ሐበሻ ሳይሆን የኔ አመለካከት ብቻ ነው | በዚህ ዘመን ኢትዮጵያውያን በከፍተኛ የፖለቲካ፣ ማኅበራዊ እና የሥነ-ልቦና ቀውስ ውስጥ ይገኛሉ። ይህን ቀውስ በተመለከተ የማከብራቸው ኡስታዝ ያሲን ኑሩ "ለአዲሱ ትውልድ ተስፋ መስጠት" በሚል ርዕስ ያደረጉትን ንግግር በቪዲዮ በፌስቡክ ሲዘዋወር ተመልክቻለሁ፤ [ይህ ቪድዮ የቴዲ አፍሮ ሙዚቃ ከተለቀቀ በኋላ የተናገሩት እንደሆነ እርግጠኛ አይደለሁም። ግን ብዙዎች ከቴዲ ፎቶና ሙዚቃ ጋር አገናኝተው ስላጋሩት ያን ታሳቢ አድርጌ ሃሳቤን እንዳቀረብኩ ይታወቅልኝ] እንዲሁም የድምፃዊ ቴዲ አፍሮን "ዳስ ጣል ልቤ" የተሰኘ በአንድ ሳምንት ከ100 ሚሊዮን በላይ ሕዝብ በዩቱብ እና ሌሎች መተግበሪያዎች ይስደመጠውን ሰምቻለሁ። ሁለቱም መልዕክቶች ከየራሳቸው አቅጣጫ የሚነግሩን ትልቅ እውነት አላቸው። ነገር ግን ኡስታዝ ያሲን ኑሩን በከፍተኛ አክብሮት እየተመለከትኩ፣ በንግግራቸው ውስጥ የሚገኙ አንዳንድ አቀራረቦችን ከቴዲ አፍሮ አገላለፅና [እኔ እንደተረዳሁት] እና ከተጨባጩ የሀገራችን የፖለቲካ እውነታ ጋር አገናኝቼ መተቸት እና ሚዛናዊ የሆነ ዕይታን ማቅረብ እወዳለሁ።

ኡስታዝ ያሲን ኑሩ በንግግራቸው ላይ በተደጋጋሚ የሚያነሱት አንድ ትልቅ እና ጠቃሚ ነጥብ አለ፤ እሱም "ተስፋ" ነው። ለትውልድ "ሀገር ፈርሳለች፣ ዳስህን ጣል" ብሎ መንገር፣ ማኅበራዊ ሳይንስን፣ የሥነ-ልቦናን መርህ እና የአመራር ጥበብን ካለመረዳት የሚመነጭ እንደሆነ አበክረው ይናገራሉ። ነቢዩ ሙሐመድ (ሰ.ዐ.ወ) "ሰዎችን አብስሩ እንጂ አታስበርግጉ (አታስሩጡ)" እንዳሉት በማስታወስ፣ አንድ መሪ፣ ኃይማኖት አባት ወይም ተጽዕኖ ፈጣሪ ግለሰብ በማንኛውም አስቸጋሪ ጊዜ ውስጥ ቢሆን ለሕዝብ ተስፋን መዝራት እንዳለበት ይሞግታሉ።

እርግጥ ነው የተስፋ ሥነ-ልቦና ማኅበረሰብን ከመፈራረስ ይታደጋል። ዊንስተን ቸርችል በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወቅት ለብሪታንያ ሕዝብ ተስፋ ባይሰጥ ኖሮ ለንደን በናዚ ጀርመን ቦምብ ስትደበደብ ሕዝቡ ይበታተን ነበር። ማርቲን ሉተር ኪንግ "I Have a Dream" (ሕልም አለኝ) ባይል ኖሮ የአሜሪካ የጥቁሮች የሲቪል መብት ትግል ያን ያህል ተስፋ ባላገኘ ነበር። ኡስታዝ ያሲን ይህንን ሃሳብ ሲያነሱ፣ ትውልዱ ከድብርት እና ከማኅበራዊ የተስፋ መቁረጥ እንዲወጣ በማሰብ እንደሆነ ይሰማኛል። ይህ በበጎ ጎኑ ሊደነቅ የሚገባው የአንድ አባት እና የኃይማኖት መምህር የቅንነት ምክር ነው።

ነገር ግን የኡስታዝ ያሲን ኑሩን ንግግር ሙሉ በሙሉ ለመቀበል የሚያዳግተው፣ ተስፋን መዝራት ማለት እውነታን መካድ መሆን ሲጀምር ነው። ቴዲ አፍሮ በ"ዳስ ጣል ልቤ" ሙዚቃው ላይ እንዲህ ይላል፦

"እህ እያሉ ነዶ
ሀገር የሞተበት
የት ያለቅሳል ሄዶ...
አክሱም ላሊበላን በአንድ አለት አጽንቶ
አልራመድ አለ ሀገር ተለያይቶ"

እኔ እንደሚሰማኝ ቴዲ አፍሮ እዚህ ጋር እየተናገረ ያለው ስለ ሥነ-ልቦና ውድቀት ሳይሆን፣ ስለ ፖለቲካዊ እና ማኅበራዊ የህልውና ቀውስ ነው። "ሀገር ፈርሳለች" ሲባል፣ ጂኦግራፊያዊ የሆነው መሬት ተንዶ አለቀ ማለት አይደለም። ይልቁንም፣ ሀገርን ሀገር የሚያሰኙት የሞራል፣ የሕግ፣ የፍትሕ እና የጋራ ደህንነት ምሰሶዎች ተናግተዋል ማለት ነው።

ኡስታዝ ያሲን "ሀገር አልፈረሰችም" ሲሉን፣ እውነታው ግን ዜጎች በገዛ ሀገራቸው ከአንድ ክልል ወደ ሌላ ክልል በነፃነት መንቀሳቀስ ያልቻሉበት፣ ማንነትን መሠረት ያደረጉ ግድያዎች እና መፈናቀሎች የተንሰራፉበት፣ በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ እናቶችና ሕፃናት በየሜዳው የረገፉበት ዘመን ላይ ነን።

ቴዲ አፍሮ...
"ባሳደገኝ ቀዬ ባደኩበት መንደር
ባይተዋር ሰው ሆኜ እንደሌለው ሀገር"
ሲል፣ በአዲስ አበባም፣ በኦሮሚያም፣ በአማራም፣ በጋምቤላም፣ በቤንሺሻንጉል፥ በትግራይም፣ በሐዋሳም፣ በሶማሌ ክልልም በሐረሪም፣ በድሬድዋም ሆነ በሌሎች የሀገሪቱ ክፍሎች ዜጎች ላይ እየደረሰ ያለውን የመገለል እና የመግፋት ሥነ-ልቦና በትክክል ይገልጻል። ይህን እውነታ "ሀገር አልፈረሰችም" በሚል የፖለቲካ ማስታገሻ ለማለፍ መሞከር፣ የታመመን ሰው "ምንም አልሆንክም፣ ዝም ብለህ ተነሳ" እንደማለት ይቆጠራል።

ኡስታዝ ያሲን "ትውልድን አታስበርግጉ፣ ተስፋ ስጡት" ማለታቸው አግባብ ቢሆንም፣ ተስፋ ሊሰጥ የሚችለው እውነታውን በመካድ አይደለም። አንድ ሐኪም ለካንሰር ታማሚ "ምንም የለብህም" አይለውም፤ በሽታውን በግልጽ ነግሮት፣ የሕክምናውን ሂደት ካብራራ በኋላ ነው የሕይወት ተስፋ የሚሰጠው። አሁን የኢትዮጵያ ሕዝብ የሚያስፈልገው "ምንም አልሆንንም" የሚል የሐሰት ማፅናኛ ሳይሆን፣ የችግራችንን ጥልቀት አውቀን፣ በጋራ መፍትሔ የምንፈልግበት (መድሃኒት) መንገድ ነው።

የአሜሪካው ፕሬዝዳንት አብርሃም ሊንከን፣ አሜሪካ በእርስ በርስ ጦርነት ስትታመስ "A house divided against itself cannot stand" (በራሱ ላይ የተከፋፈለ ቤት ሊቆም አይችልም) ብሎ ነበር። ሊንከን ይህን ሲናገር "አሜሪካ ፈርሳለች" እያለ ማርዶ ሳይሆን፣ እውነታውን ለሕዝቡ እያሳየ ነበር። ቴዲ አፍሮም "ምሶሶው ዘመመ ጣሪያውም ያፈሳል" ሲል፣ ሊንከን የተጠቀመውን ዓይነት የእውነታ ነጸብራቅ ነው ያቀረበው። "አስራ ሁለት ሆና፣ አንድ ነብር ፈጃት... ዝምታ ለበግም አልበጃትምና" የሚለው የቴዲ አፍሮ ስንኝ፣ የዝምታን አደጋ፣ የሕግ የለሽነትን መዘዝ፣ እና ያለንበትን አሳዛኝ የሥርዓት ብልሽት ያሳያል።

ኡስታዝ ያሲን በንግግራቸው መጨረሻ ላይ የነቢዩ ሙሐመድን (ሰ.ዐ.ወ) አደራ ያነሳሉ። ነቢዩ "ኢትዮጵያን አትንኩ" ብለው አደራ ማለታቸውን፣ እና ኢትዮጵያ የፍትሕ ሀገር መሆኗን ያስታውሳሉ። ይህ ታሪካዊ እውነት ማንም ኢትዮጵያዊ የሚኮራበት ነው። የነጃሺ ፍትሕ የኢትዮጵያዊነት ማሳያ ነበር።

ነገር ግን ዛሬ ያ የነጃሺ ፍትሕ የት አለ? ዛሬ "ኢትዮጵያን አትንኩ" የሚለውን አደራ ያፈረሰው የውጭ ጠላት ሳይሆን፣ እኛው እርስ በርሳችን ነን። የነቢዩ አደራ የሚጠበቀው "አይዞን፣ ሁሉም ሰላም ነው" በማለት ሳይሆን፣ እውነትን በመናገር፣ ግፍን በማውገዝ እና ለፍትሕ በመቆም ነው።

ቴዲ አፍሮ
"ጀግኖች ሞተውላት፣ በመርዝ ጋዝ ነፍረው
ተንገብግበው በእሳት፣ ዘመን ተገላብጦ
እንዴት አቀርቅሬ፣ ባንዲራዬን ላንሳት" ሲል፣ ቀደምት አባቶች ያቆዩዋት ክብር ዛሬ መዋረዱን ነው የሚያነሳው። ባንዲራችን የፖለቲካ መጠቀሚያ፣ ማንነታችን የጥቃት ኢላማ በሆነበት በዚህ ዘመን፣ "ሀገር ፈርሳለች" ብሎ መገምገም ማኅበራዊ ሳይንስን ካለማወቅ የሚመጣ ሳይሆን፣ መራራውን እውነት ከመቀበል የሚመነጭ ነው።

ጽሁፌን ስቋጭ ኡስታዝ ያሲን ኑሩን ለሰላም፣ ለተስፋ እና ለአንድነት ያላቸውን ቀና አመለካከት አከብራለሁ። ትውልድን በተስፋ ማነጽ አስፈላጊ ነው። ነገር ግን፣ ቴዲ አፍሮ በግጥሙ እንዳስቀመጠው፣ አሁን ያለንበት ሁኔታ "የዳስ" (የሃዘን) ሁኔታ ነው። ሀገራችን በብዙ ፈተናዎች ታጅባለች።

የጀርመኑ ፈላስፋ ፍሬድሪክ ኒቼ "He who has a why to live for can bear almost any how" (ለመኖር የሚያስችል 'ምክንያት' ያለው ሰው፣ የትኛውንም 'እንዴት' መቋቋም ይችላል) ብሎ ነበር። ኢትዮጵያውያን ተስፋ (ምክንያት) ያስፈልገናል። ነገር ግን ያ ተስፋ መገንባት ያለበት በሐሰተኛ ትርክት ላይ ሳይሆን፣ ስህተቶቻችንን አምነን በመቀበል፣ ፍትሕን በማስፈን እና እኩልነትን በተግባር በማረጋገጥ ላይ ነው።

"ዳስ ጣል ልቤ" የሚለው ጩኸት፣ የመጨረሻው የተስፋ መቁረጥ ድምፅ ሳይሆን፣ የማንቂያ ደወል ነው። ሀገር የምትድነው መሪዎቿ እና ተጽዕኖ ፈጣሪዎቿ "ምንም አልሆንንም" ሲሉ ሳይሆን፣ ዜጎቿ "እየታመምን ነው፣ ሕክምና እንፈልጋለን" ብለው እውነቱን ሲያወጡ ነው። ኡስታዝ ያሲንም ሆኑ ቴዲ አፍሮ በየራሳቸው መንገድ ሀገርን ይወዳሉ፤ ነገር ግን በዛሬይቱ ኢትዮጵያ፣ ቴዲ አፍሮ ያወጣው ዘፈን አሁን ካለንበት ተጨባጭ የፖለቲካ እና የማኅበራዊ ቀውስ ጋር ይበልጥ የተቆራኘ ነው።

2 months ago

No replys yet!

Be the first to share what you think — your comment will appear here.