Logo
EBC
ለዋንጫ የሚሆን በቂ ነዳጅ አለን፡- የቬንገርን ሪከርድ ለመስበር የሚጫወተው ሚኬል አርቴታ
********************

በ35ኛ ሳምንት የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ የሊጉ መሪ አርሰናል በለንደን ደርቢ ዛሬ በሜዳው ከፉልሀም ይጫወታል፡፡ ከሁለት የሊጉ ተከታታይ ሽንፈት በኋላ ባለፈው ሳምንት ኒውካስትልን በማሸነፍ ወደ ድል የተመለሰው የሰሜን ለንደኑ ክለብ ወደ ዋንጫው ለመቅረብ በሚያደርገው ጨዋታ ከፉልሀም ከባድ ፈተና ይጠብቀዋል፡፡

ጨዋታው ምሽት 1 ሰዓት ከ 30 ላይ በኤምሬትስ የሚደረግ ሲሆን አርሰናል በሜዳው ከፉልሀም ባደረጋቸው ያለፉት 32 ጨዋታዎች አልተሸነፈም፡፡ 25 ጨዋታዎችን ሲያሸንፍ በሰባቱ አቻ ተለያይቷል፡፡ በአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ ከ20 ዓመት በኋላ ለፍጻሜ ለመድረስ ከአትሌቲኮ ማድሪድ አንድ የ90 ደቂቃ ፍልሚያ ብቻ የሚቀረው አርሰናል ዛሬ በሜዳው የሚያደርገውን ጨዋታ ካሸነፍ የማንችስተር ሲቲ ሁለት ተስተካካይ ጨዋታዎች እንደተጠበቁ ሆነው የነጥብ ልዩነቱን ወደ ስድስት ከፍ የሚያደርግ ይሆናል።

ከወሳኙ ጨዋታ በፊት ሚኬልል አርቴታ በሰጠው ሃሳብ አርሰናል ለዋንጫ የሚያበቃው ነዳጅ (አቅም) አለው ብሏል፡፡ ስፔናዊው አሰልጣኝ “ሊጉ ሊጠናቀቅ አራት ጨዋታዎች ሲቀሩት መገኘት ያለብን ደረጃ ላይ ተገኝተናል ለሁሉም ፈተና ዝግጁ ነን በውድድር ዓመቱ ሁሉ ስናደርግ የነበረውን የማሸነፍ ፍላጎት ይዘን እስከ መጨረሻው እንጓዘለን” ብሏል፡፡ ደጋፊዎች በእያንዳንዱ እንቅስቃሴ ላይ ለተጫዋቾች የሚያሳዩት አዎንታዊ ድጋፍ ውጤቱን ይበልጥ የተሻለ እንደሚያደርገውም ገልጿል፡፡

በሌላ በኩል፣ ሚኬል አርቴታ የዛሬውን ጨዋታ ካሸነፈ በአንድ የውድድር ዓመት አርሰን ቬንገር ካስመዘገቡት የድል ብዛት በላይ በማሸነፍ በክለቡ አዲስ ታሪክ ይጽፋል። ፈረንሳዊው አሰልጣኝ አርሰን ቬንገር በ2001/02 የውድድር ዓመት በ60 ጨዋታዎች 39 ድሎችን ያስመዘገቡ ሲሆን፤ አርቴታ በበኩሉ በዘንድሮው የውድድር ዓመት እስካሁን ባደረጋቸው 57 ጨዋታዎች 39ኙን በማሸነፍ የአንጋፋውን ሰው ታሪክ ተጋርቷል። በመሆኑም ዛሬ ፉልሃምን ማሸነፍ የሚችል ከሆነ የቬንገርን የቆየ ክብረ ወሰን በማሻሻል በክለቡ ታሪክ በአንድ የውድድር ዓመት ብዙ ጨዋታዎችን ያሸነፈ የመጀመሪያው አሰልጣኝ ሆኖ ስሙን በደመቀ ሁኔታ ይጽፋል።

የፉልሀሙ አሰልጣኝ ማርኮ ሲልቫ እንዲህ አይነት ጨዋታዎችን ማድረግ ያስደስተኛል በመሆኑም ለዋንጫ ከሚፋለመው አርሰናል የምንጫወተው ሦስት ነጥብ ለማግኝት ነው ብለዋል፡፡ በጨዋታው ካይ ሀቨርዝ እና ዩሪየን ቲምበር በጉዳት ከስብስቡ ወጭ ሲሆኑ ማርቲን ኦዴጋርድ ለጨዋታው እንደሚደርስ ሚኬል አርቴታ ተናግሯል፡፡

በሌላ ጨዋታ በሊጉ ለመቆየት እየታገለ የሚገኘው ዌስትሀም ዩናይትድ 11 ሰዓት ላይ ከሜዳው ወጭ ከብሬንትፎርድ ይጫወታል፡፡ በ36 ነጥብ 17ኛ ደረጃ ላይ የሚገኘው ዌስትሀም ከባለፉት ስድስት የሊግ ጨዋታዎች የተሸነፈው በአንዱ ብቻ ሲሆን 18ኛ ደረጃ ላይ የሚገኘው ቶተንሀም እንዳይደርስበት የሚፋለም ይሆናል፡፡

ኒውካስትል ዩናይትድ ከብራይተን እና ከሊጉ መሰናበቱን ያረጋገጠመው ዎልቭስ ከሰንደርላንድ በተመሳሳይ 11 ሰዓት የሚደረጉ ጨዋታዎች ናቸው፡፡

በአንተነህ ሲሳይ
#ethiopiabroadcastingcorporation #epl #arsenal #fulham

5 months ago

No replys yet!

Be the first to share what you think — your comment will appear here.