Logo
EBC
ኢራን የዓለም ዋንጫ ጨዋታዎቿን በአሜሪካ ታደርጋለች - ፊፋ
****************

ኢራን የ2026ቱን የዓለም ዋንጫ ጨዋታዎቿን በአሜሪካ እንደምታከናውን የዓለም አቀፉ የእግር ኳስ ፌዴሬሽኖች ማኅበር (ፊፋ) ፕሬዚዳንት ጂያኒ ኢንፋንቲኖ በድጋሚ አረጋገጡ።

ኢንፋንቲኖ ይህንን ያስታወቁት በቫንኩቨር፣ ካናዳ መካሄድ የጀመረውን የፊፋ ጉባኤን በንግግር በከፈቱበት ወቅት ነው።

በመካከለኛው ምሥራቅ የተቀሰቀሰውን ጦርነት ተከትሎ ኢራን በካናዳ፣ ሜክሲኮ እና አሜሪካ አስተናጋጅነት በሚካሄደው የ2026ቱ የዓለም ዋንጫ ስለመሳተፏ ጥርጣሬ ላይ ወድቆ ነበር።

ይሁን እንጂ ኢንፋንቲኖ ለጉባኤው በሰጡት መግለጫ፣ "በመጀመሪያ ላረጋግጥላችሁ የምፈልገው ኢራን በ2026ቱ የፊፋ ዓለም ዋንጫ ላይ በእርግጠኝነት ትሳተፋለች፤ ጨዋታዎቿንም በአሜሪካ ታደርጋለች" ብለዋል።

የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ከፊፋው ፕሬዚዳንት መግለጫ በኋላ ስለሁኔታው ተጠይቀው በሰጡት መልስ፣ “አዎ መጫወት ይችላሉ” ሲሉ መመለሳቸውን አናዶሉ ዘግቧል።

ቀደም ሲል የኢራን ባለሥልጣናት የምድብ ጨዋታዎቻቸው ከአሜሪካ ወደ ሜክሲኮ እንዲዛወሩ ጠይቀው የነበረ ቢሆንም፣ ጥያቄው በፊፋው ፕሬዚዳንት ጁሊያኒ ኢንፋንቲኖ ውድቅ ተደርጎ ነበር።

ባለፈው ሳምንት ደግሞ የጣሊያን ተወላጅ የሆኑት የአሜሪካ ልዩ መልዕክተኛ ፓውሎ ዛምፖሊ "ከዓለም ዋንጫ ተሳትፎው ኢራን ተቀንሳ ጣሊያን ትተካ" የሚል ሐሳብ አቅርበው የነበረ ቢሆንም፣ የአሜሪካ መንግሥት ከዚህ ሐሳብ ራሱን ማራቁን የዘገበው ደግሞ ቲአርቲ ነው።

የአሜሪካው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማርኮ ሩቢዮም የኢራን እግር ኳስ ተጫዋቾች በአሜሪካ መልካም አቀባበል እንደሚደረግላቸው መግለጻቸው ይታወሳል።
#ebc #worldcup #iran #usa #fifa

5 months ago

No replys yet!

Be the first to share what you think — your comment will appear here.