Logo
SeledaPost
በአክሱም ከተማ ለሰላት በተሰባሰቡ ምዕመናን ላይ ጥቃት መፈጸሙ ተነገረ

አክሱም —በትግራይ ክልል አክሱም ከተማ ዛሬ አርብ (ሚያዝያ 2 ቀን 2018 ዓ.ም) ለጁመዐ ሰላት በተሰባሰቡ ምዕመናን ላይ በከተማዋ የፀጥታ ኃላፊ በተመራ ቡድን ጥቃት መፈጸሙን የዓይን እማኞች እና የአካባቢው ነዋሪዎች ገለጹ። በደረሰው ጥቃት በርካታ ሰዎች የአካል ጉዳት የደረሰባቸው ሲሆን፣ በሃይማኖታዊ ቁሳቁሶች ላይም ውድመት መድረሱ ተሰምቷል።

እንደ ነዋሪዎች መረጃ ከሆነ፣ ግጭቱ የተቀሰቀሰው ከጁመዐ ሰላት በፊት እንደአባዋ ተብሎ በሚጠራው ስፍራ ምዕመናን ለሰላት ዝግጅት እያደረጉ በነበሩበት ወቅት ነው።

የከተማዋ የፀጥታ ኃላፊ አቶ ቴዎድሮስ በየነ መሩት የተባለው ቡድን ለሰላት አገልግሎት የሚውሉ ሸራዎችን እና የድምጽ ማጉያዎችን በኃይል ነጥቆ መውሰዱ የውጥረቱ መነሻ ሆኗል።

ከሶላት መጠናቀቅ በኋላ ምዕመናን ድርጊቱን በመቃወም ድምጻቸውን ማሰማታቸውን ተከትሎ፣ በፀጥታ ኃይሎች እና በተደራጁ ወጣቶች ጥቃት መሰንዘሩ ተገልጿል።

በጥቃቱ ዙሪያ የሚከተሉት ዋና ዋና ነጥቦች ተዘግበዋል፦

1. ጥቃት አድራሾቹ ምዕመናን ተከራይተው የሚጠቀሙበትን መስጂድ ሰብረው በመግባት በውስጡ የነበሩ ቅዱስ ቁርኣኖችን ቀደዋል ተብሏል።

2. በመስጂዱ ኢማሞች እና በምዕመናን ላይ በዱላና በድንጋይ በተፈጸመ ድብደባ በርካቶች ቆስለዋል። ስድስት ሰዎች የመጀመሪያ ደረጃ ሕክምና አግኝተው ሲወጡ፣ የሁለቱ ጉዳት ግን ከፍተኛ በመሆኑ በቅድስት ማርያም ሆስፒታል ክትትል እየተደረገላቸው ይገኛል

3. ከጥቃቱ በኋላ በከተማዋ በተደረገ የመኖሪያ ቤት አሰሳ በርካታ ሰዎች ተይዘው መታሰራቸው ተነግሯል።

መቀመጫውን በመቀሌ ያደረገው የትግራይ ክልል እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት ጉዳዩን ለሚመለከታቸው የመንግስት አካላት ማሳወቁን የጠቀሱት ምንጮች፣ ከሰዓት በኋላ ከአጎራባች ከተሞች ተጨማሪ የፀጥታ ኃይል ወደ አክሱም መግባቱን ጠቁመዋል።

በአክሱም ከተማ ከዚህ ቀደምም መሰል የሃይማኖት ነፃነት ጥያቄዎች ሲነሱ የቆዩ ሲሆን፣ በተለይም ባለፈው ዓመት ሙስሊም ሴት ተማሪዎች በትምህርት ቤቶች ውስጥ በደረሰባቸው የሒጃብ ክልከላ ምክንያት ከትምህርት ገበታቸው መፈናቀላቸው ይታወሳል።

እስከ አሁን ድረስ ከትግራይ ክልል የፀጥታ ቢሮም ሆነ ከከተማዋ አስተዳደር ስለደረሰው ጥቃት የተሰጠ ይፋዊ መግለጫ የለም።

Via Minber TV/ ሚንበር ቲቪ

seledadotio
seledadotio
4 months ago

No replys yet!

Be the first to share what you think — your comment will appear here.