Logo
Getu Temesgen
የወንጀል ምስክሮችና ጠቋሚዎች የሕግ ጥበቃ
በኢትዮጵያ ህግ ማእቀፍ

ጠበቃና የህግ አማካሪ ፋንታሁን ደለለው
0929101037,0983337690

መግቢያ #ethiopia | በኢትዮጵያ ወንጀልን እና ሙስናን ለሚያጋልጡ ጠቋሚዎች ማንነትን መደበቅ፣ ምስጢራዊነትን መጠበቅ እና ከበቀል እርምጃ የመከላከል ህጋዊ ጥበቃ ይደረጋል። ይህ ጥበቃ በተለይም ሙስናን የሚዘግቡ ወገኖች ላይ የሚደርስን ተጽዕኖ ለመቀነስ እና ጠቋሚዎች ያለስጋት መረጃ እንዲሰጡ ለማበረታታት ያለመ ነው።

የተለያዩ የአለማችን ሀገራት ለወንጀል ጠቋሚዎችና ምስክሮች ጥበቃ የሚያደርጉ ሲሆን ይህን የሚያደርጉትም ከባድ እና የተደራጁ ወንጀሎችን በሚመለከት ለሚቀርቡ ጠቋሚዎችና ምስክሮች ነው፡፡ ሀገራችንም ይህንኑ በመረዳት የወንጀል ምስክሮችና ጠቋሚዎች ጥበቃ አዋጅ ቁጥር 699/2003 አውጥታ በህግ በተመለከቱ ወንጀሎች ላይ ምስክሮችና ጠቋሚዎች ለሆኑ ሰዎች ጥበቃ ለማድረግ ጥረት በማድረግ ላይ ትገኛለች፡፡ በዚህ ፅሁፍ የምስክር እና ጠቋሚዎችን ጥበቃ ምንነትና የጥበቃ ስምምነት፣ የጥበቃ እርምጃ ዓይነቶችን እና ጥበቃ የሚደረግባቸውን ወንጀሎች በአጭሩ እንዳስሳለን፡፡

1. የጠቋሚዎችና ምስክሮች ጥበቃ ምንነት እና የጥበቃ ስምምነት

የጠቋሚዎችና ምስክሮች ጥበቃ ማለት አንድን ወንጀል በተመለከተ የሚያውቀውን ለፍርድ ቤት ወይም ለፖሊስ ለመግለፅ የተስማማ ጠቋሚ ወይም ምስክር ቃሉን ወይም መረጃውን በመስጠቱ ምክንያት በራሱ ወይም በቤተሰቡ ላይ ከሚቃጣበት ጉዳት የሚጠበቅበት በህግ የተዘረጋ ሥርአት ነው፡፡ ይህም በጥበቃ ስምምነት መሰረት የሚፈፀም ሲሆን ስምምነቱ በጥበቃ ተጠቃሚው እና በፍትህ ሚኒስቴር መካከል የሚደረግ ነው፡፡ በአዋጁ አንቀፅ 2(2) መሰረት የጥበቃ ተጠቃሚ ከሚኒስቴሩ ጋር የጥበቃ ስምምነት የተፈራረመ ጠቋሚ ወይም የምስክር ወይም የጠቋሚ ወይም የምስክር ቤተሰብ አባል ነው፡፡ የጥበቃ ተጠቃሚው አካለ መጠን ያላደረሰ ወይም በፍርድ የተከለከለ ሰው ከሆነ የጥበቃ ስምምነቱ ከወላጆቹ ወይም ከአሳዳሪው ጋር የሚፈረም ሲሆን ነገር ግን የጥበቃ ተጠቃሚው አካለ መጠን ከደረሰ ወይም የህግ ችሎታውን መልሶ ካገኘ በኋላ ጥበቃው የሚቀጥል ከሆነ ስምምነቱን የጥበቃ ተጠቃሚው ራሱ መፈረም እንዳለበት በአዋጁ አንቀፅ 8(3) ተደንግጎ ይገኛል፡፡

2. የጥበቃ ተጠቃሚው የሆነው አካለ መጠን ያላደረሰ ልጅ ሲሆን

መረጃ ወይም ምስክርነት የሚሰጠው በወላጁ ወይም በአሳዳሪው ላይ ሲሆን፣ ወላጅ ወይም አሳዳሪ የሌለው ሲሆን፣ አስፈላጊው ጥረት ተደርጎ ወላጁን ወይም አሳዳሪውን ማግኘት ያልተቻለ እንደሆነ፣ ወላጁ ወይም አሳዳሪው በቂ ባልሆነ ምክንያት ፈቃዱን ሳይሰጥ ሲቀር ወይም በማናቸውም ምክንያት ፈቃዱን መስጠት ሳይችል ሲቀር ሚኒስቴሩ ከልጁ ጋር ልዩ የጥበቃ ስምምነት ሊፈራረም እንደሚችል ከአዋጁ አንቀፅ 9(1) መረዳት ይቻላል፡፡ ሆኖም አካለ መጠን ካላደረሰ ልጅ ጋር የተደረገ ልዩ የጥበቃ ስምምነት ከተፈረመበት ዕለት ጀምሮ ባሉት አስር ቀናት ውስጥ ለፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ቀርቦ መጽደቅ አለበት፡፡ ፍርድ ቤቱም አካለ መጠን ያላደረሰው ልጅ ጥቅምና ደህንነት ይበልጥ ሊረጋገጥ የሚችልበትን ሁኔታ ግምት ውስጥ በማስገባት የጥበቃ ስምምነቱን መሻር፣ ማጽደቅ ወይም ማሻሻል እንደሚችል በአዋጁ አንቀጽ 9(4) ስር ተደንግጎ ይገኛል፡፡

3. ዋና ዋና የጥበቃ አይነቶች

3.1 ማንነትን መደበቅ፦ የጠቋሚው ማንነት በምርመራ እና ክስ ሂደት ውስጥ በምስጢር እንዲያዝ ይደረጋል።

3.2 ከበቀል ጥበቃ፦ ጠቋሚዎች በስራ ቦታቸው ወይም በሌላ ቦታ ላይ ለጠቆሙት ጥቆማ በቀል እንዳይደርስባቸው ህጉ ይከለክላል።

3.3 የደህንነት ከለላ፦ የወንጀል ድርጊቶችን በመጠቆማቸው ህይወታቸው ወይም ንብረታቸው አደጋ ላይ ሊወድቅ በሚችልበት ጊዜ ጥበቃ ይደረግላቸዋል።

3.4 ህጋዊ ጥበቃ (Immunities): ጠቋሚዎች ከሰጡት መረጃ ጋር በተያያዘ ከፍትሐብሔር ወይም የወንጀል ተጠያቂነት ጥበቃ ሊደረግላቸው ይችላል። እነዚህ ዋና ዋናዎቹ ሲሆኑ በዝርዝር ሌሎቹንም ጨምሮ ከዚህ በታች ባለው ክፍል የጥበቃ አይነት እና ጥበቃ ለሚያስፈልጋቸው አካላት የሚወሰድላቸው የህግ ጥበቃ አፈጻጸም እንመለከታለን።

4. የጥበቃ ዓይነቶች እና አፈጻጸም

ለወንጀል ጠቋሚዎችና ምስክሮች የሚደረጉ የጥበቃ እና የጥንቃቄ እርምጃዎች በአዋጁ አንቀጽ 4 ስር ተዘርዝረው ይገኛሉ፡፡ የጥበቃ እና የጥንቃቄ እርምጃዎች እንደ ሁኔታው በተናጠል ወይም በጣምራ ለጥበቃ ተጠቃሚ ተፈጻሚ የሚደረጉ ሲሆን ይህም ፡-

 የአካልና ንብረት ደህንነት ጥበቃ

 የመኖሪያ ስፍራ መቀየርን ጨምሮ ደህንነቱ የተጠበቀ የመኖሪያ ቦታ መስጠት

 ማንነትንና ባለንብረትነትን መደበቅ

 ማንነትን መቀየር

 ለራስ መጠበቂያ የነፍስ ወከፍ መሳሪያ መስጠት

 መረጃ በተሰጠበት የወንጀል ድርጊት ያለመከሰስ

 መረጃ በሚሰጥበት የወንጀል ጉዳይ ላይ የመጨረሻ ውሳኔ ከመሰጠቱ በፊትም ሆነ በኋላ ተከሳሽ በጥበቃ ተጠቃሚው መኖሪያ ወይም የሥራ ቦታ ወይም ትምህርት ቤት አካባቢ እንዳይደርስ ማገድ

 የፍርድ ሂደት ተጀምሮ ምስክርነት እስከሚሰጥ ድረስ የምስክር ማንነት እንዳይገለጽ ማድረግ

 ምስክርነት በዝግ ችሎት እንዲሰጥ ማድረግ

 ምስክርነት በአካል ሳይታይ ከመጋረጃ በስተጀርባ ሆኖ ወይም ማንነትን በመሸፈን እንዲሰጥ ማድረግ

 ማስረጃ በኤሌክትሮኒክስ ወይም በሌላ የተለየ ዘዴ እንዲቀርብ ማድረግ

 በሚስጥር መያዝ ያለበት ካልሆነ በስተቀር ለጠቋሚ ጥቆማ ባቀረበበት ጉዳይ ላይ ወቅታዊ መረጃና ምክር መስጠት

 እንዲመሰክር ለተጠራ ምስክር የጉዞና የውሎ አበል መስጠት

 የጥበቃ እርምጃው የመኖሪያ ስፍራን ለውጥ ካስከተለ የጓዝ ማንሻ ወጪን መሸፈን

 በበቀል የተወሰደ አስተዳደራዊ እርምጃ እንዲታገድ ወይም እንዲሻር ማድረግ ወይም ተመጣጣኝ የሆነ የማካካሻ እርምጃ መውሰድ

 በበቀል እርምጃ ለደረሰ ጉዳት የህክምና አገልግሎት በመንግሥት ሆስፒታል በነጻ መስጠት

 በጥበቃ እርምጃው ምክንያት ለደረሰ የገቢ ማጣት ወይም በበቀል እርምጃ ለደረሰ የመሥራት ችሎታ ማጣት የመሠረታዊ ፍላጎት ማሟያ ወጪን መሸፈን

 በጥበቃ ሥር እያለ ለደረሰ ሞት የቀብር ማስፈጸሚያ ወጪ መሸፈንና ለቤተሰብ የገንዘብ ድጋፍ ማድረግ

 የጥበቃ ተጠቃሚው የሥራና የትምህርት ዕድል እንዲያገኝ መርዳት

 ለምስክሩ ወይም ለጠቋሚው የምክር አገልግሎት መስጠት ወይም እንዲያገኝ ማድረግን የሚያካትት ነው፡፡

5. ለምስክር ወይም ጠቋሚዎች ጥበቃ የሚደረግባቸው ወንጀሎች የትኞቹ ናቸው?

ለምስክሮች ወይም ለጠቋሚዎች ጥበቃ የሚደረገው በህጉ ለተመለከቱት ወንጀሎች ሲሆን በወንጀል ምስክሮችና ጠቋሚዎች ጥበቃ አዋጅ ቁጥር 699/2003 አንቀጽ 3 መሰረት የጥበቃ እና የጥንቃቄ እርምጃዎች ማግኘት የሚቻለው የፅኑ እስራት መነሻው ምንም ይሁን ምን ጣራው ግን 10 (አስር አመት) እና ከዚያ በላይ በሆነ ፅኑ እስራት ወይም በሞት ሊያስቀጣ በሚችል ወንጀል ምስክርነት ወይም ጥቆማን የተመለከተ ሆኖ

 የወንጀል ድርጊቱ ያለምስክሩ ወይም ያለጠቋሚው ምስክርነት ወይም ጥቆማ በሌላ ማናቸውም መንገድ ሊረጋገጥ ወይም ሊደረስበት የማይችል ሲሆን እና

 በምስክሩ፣ በጠቋሚው ወይም በቤተሰቡ ህይወት፣ አካላዊ ደህንነ፣ ነፃነት ወይም ንብረት ላይ ከባድ አደጋ ያደርሳል ተብሎ ሲታመን እንደሆነ ከአዋጁ አንቀፅ 3(1) መረዳት ይቻላል፡፡
ለአብነትም በኢትዮጵያ የሽብር ወንጀልን ለመከላከል እና ለመቆጣጠር የወጣው አዋጅ ቁጥር 1176/2012 አንቀፅ 16 እና በሰው የመነገድ እና ሰውን በህገ ወጥ መንገድ ድንበር የማሻገር ወንጀልን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የወጣው አዋጅ ቁጥር 1178/2012 አንቀፅ 25 የወንጀል ምስክሮችና ጠቋሚዎች በአዋጅ ቁጥር 699/2003 መሰረት ለወንጀል ምስክሮችና ጠቋሚዎች ስለሚደረግ ጥበቃ ደንግገው ይገኛሉ፡፡
ነገር ግን አዋጁ ይህንን መስፈርት ቢያስቀምጥም የፍትህ ሚኒስቴሩ የጥበቃ ተጠቃሚ ላልሆኑ ለማንኛቸውም ምስክሮችና ጠቋሚዎችም በዚህ አዋጅ አንቀጽ 4 ስር ከተቀመጡ አንዳንድ ጥበቃዎችን እንደአስፈላጊነቱ ሊያደርግ ይችላል፡፡

ይህም

 በሚስጥር መያዝ ያለበት ካልሆነ በስተቀር ለጠቋሚ ጥቆማ ባቀረበበት ጉዳይ ላይ ወቅታዊ መረጃና ምክር መስጠት

 እንዲመሰክር ለተጠራ ምስክር የጉዞና የውሎ አበል መስጠት

 በበቀል የተወሰደ አስተዳደራዊ እርምጃ እንዲታገድ ወይም እንዲሻር ማድረግ ወይም ተመጣጣኝ የሆነ የማካካሻ እርምጃ መውሰድ

 በበቀል እርምጃ ለደረሰ ጉዳት የህክምና አገልግሎት በመንግሥት ሆስፒታል በነጻ መስጠት

 ለምስክሩ ወይም ለጠቋሚው የምክር አገልግሎት መስጠት ወይም እንዲያገኝ ማድረግን የሚያካትት ነው፡፡

6. የጹሁፉ ቁልፍ የህግ ማጠቃለያ

የዚህ ጽሁፍ መነሻ የአዋጅ ቁጥር 699/2003 ስለ ወንጀል ጠቋሚዎችና ምስክሮች የሚደረግ የህግ ጥበቃ ሲሆን ከላይ በቀረበው አግባብ የህግ ግንዛቤ መስጠት በተለይም ረቂቅና ከበድ ወንጀሎችን በህዝብና በሀገር ላይ ከባድ ጉዳትን የሚያስከትሉትን ወንጀሎች እንዲጋለጡ ምስክሮችም የህግ ጥበቃ ኖሮዋቸው የበኩላቸውን ድርሻ እንዲወጡ መንግስት አስፈላጊውን ጥበቃ በዚህ አዋጅ መሠረት ማድረጉ ለህበረተሰቡና ለሀገር ሰላም የሚበጅ ሲሆን በተቃራኒው እንደዚህ አይነት ሰወች በመጠቆማቸው ወይም በመመስከራቸው ምክንያት የአደጋ ወይም የወንጀል ሰለባ ቢሆኑ ለሌላውም ዜጋ በዚህ ልክ ትብብር ለመስጠት የሚፈራ በመሆኑ ፍትህ ተደብቃ የምትቀርበት ሁኔታ ይፈጠራል።ስለሆነም ለከባድ ወንጀል ጠቋሚዎች እና ለምስክሮች መንግስት አስፈላጊውን የህግ ጥበቃ ሊያደርግና ከዚህ አንጻር ለማህበረሰቡ አስፈላጊውን የህግ ግንዛቤ ሊሰጥ ያስፈልጋል።

https://t.me/Fantahunlawye...
https://www.facebook.com/s...

ማጣቀሻዎች/References/
1. የወንጀል ምስክሮችና ጠቋሚዎች ጥበቃ አዋጅ ቁጥር 699/2003
2. የኢፊድሪ ወንጀል ህግ 1996
3. የወንጀለኛ መቅጫ ህግ ስነስረአት
4. የኢፊድሪ ወንጀል ስነስረአት እና የማስረጃ ህግ

5. የፍትህ ሚኒስቴርን የማህበራዊ ሚዲያ ትስስር የፌስቡክ ገጽ

2 months ago

No replys yet!

Be the first to share what you think — your comment will appear here.