Logo
FastMereja
የኢትዮጵያ ጥራት ሽልማት ድርጅት አዲስ የምዘና ሞዴል ይፋ አደረገ፤ 73 ተቋማት ለውድድር ቀርበዋል

​#fastmereja I የኢትዮጵያ ጥራት ሽልማት ድርጅት ተቋማትን የሚመዝንበትን የልህቀት ሞዴል (Self Assessment Manual) ከዓለም አቀፍ ነባራዊ ሁኔታዎች እና ከሰው ሠራሽ አስተውሎት (AI) እድገት ጋር በማጣጣም ማሻሻሉን አስታወቀ። በ13ኛው ዙር አገር አቀፍ የጥራት ሽልማት ውድድር ላይ ለመሳተፍም የኢትዮጵያ አየር መንገድ እና ኮካ ኮላን ጨምሮ 73 ድርጅቶች መመዝገባቸው ተገልጿል።

​የድርጅቱ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ቴዎድሮስ መብራት ዛሬ ሐሙስ መጋቢት 24 ቀን 2018 ዓ.ም በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ እንደገለጹት፣ ተቋሙ ለ13ኛው ዙር ውድድር የሚጠቀምበት ማንዋል በከፍተኛ ሁኔታ ተሻሽሏል። ይህ ማሻሻያ የተደረገው አሁናዊ የልህቀት ጽንሰ-ሐሳቦችን ለማካተት፣ ከአገሪቱ ብሔራዊ ፖሊሲ ጋር ለማጣጣም እና በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚታወቁትን የEFQM እና የማልኮም ባልድሪጅ የ2025 የክለሳ መስፈርቶችን መነሻ በማድረግ መሆኑ ታውቋል።

​በተለይም የቴክኖሎጂ ሽግግርን ከግምት ውስጥ በማስገባት፣ በሰው ሠራሽ አስተውሎት (AI) እና በልህቀት ሞዴሉ መካከል ያለውን ትስስር የሚቃኙ አዳዲስ የአሠራር ሥርዓቶችና ስታንዳርዶች በማንዋሉ ውስጥ ተካተዋል።

​በዘንድሮው ውድድር ላይ ለመሳተፍ ከተመዘገቡት 73 ድርጅቶች መካከል 38ቱ በማኑፋክቸሪንግ፣ 12ቱ በአገልግሎት፣ 9ኙ በጤና፣ 9ኙ በፐብሊክ ሰርቪስ እንዲሁም 5ቱ በኮንስትራክሽን ዘርፍ የተሰማሩ ናቸው።

ቀደም ባለው 12ኛው ዙር የልህቀት ዋንጫ አሸናፊ የነበሩት የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ፣ የሃይንከን ኢትዮጵያ ፋብሪካዎችና የሚድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ በድጋሚ የቀረቡ ሲሆን፤ እንደ ኢስት አፍሪካ ቦትሊንግ (ኮካ ኮላ)፣ የቅዱስ ጴጥሮስ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል እና የኢትዮጵያ ማሪታይም ባለሥልጣን ያሉ ተቋማት ደግሞ በዘንድሮው ውድድር አዲስ ተመዝጋቢ ሆነዋል።

​መጋቢት 24 ቀን 2018 ዓ.ም

2 months ago

No replys yet!

Be the first to share what you think — your comment will appear here.