Logo
Getu Temesgen
♦️የኢትዮጵያ ሻምፒዮና ዳግም ውልደት

♦️አትሌቲክሱ ከማንዋል ወደ ዲጂታል መሸጋገሩን ያበሠረው ሻምፒዮና

♦️ልዩ ምስጋና የሚገባቸው ሁሉም የፌዴሬሽኑ ባለሙያዎች እና የአትሌቲክስ ዳኞች

👉1057 አትሌቶች ለሜዳልያ የተናነቁበት 55ኛው
ሻምፒዮና

#ethiopia | 36 ክለቦችና ተቋማት፣ 9 ክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች፣621 ወንዶች፣ 436 ሴቶች በድምሩ 1057 አትሌቶች ለሜዳልያ የተናነቁበት 55ኛው የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ሻምፒዮና ተመልካቾችን ቁጭ ብድግ አድርጎ፣አዳዲስ ሪከርዶች ተሠባብረውበት፣ በተለይ በአጭር ርቀት የነገ የርቀቱ ንጉሶች ሊሆኑ ይችላሉ ተብለው የተገመቱ ተስፋዎች በብዛት ታይተውበት፣በዘመናዊ የውጤት መመዝገቢያ መሣሪያ(Time Tronics) ታጅቦና ዘምኖ በልዩ ድምቀት ተጠናቋል።

👉የሻምፒዮናው አጠቃላይ የአሸናፊነትን ዘውድ

የደፋው ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ

በውድድሩ ለመሸናነፍና ለሜዳልያ ከሚደረገው ትንንቅ ባለፈ ለተተኪ አትሌቶች የውድድር እድል የመፍጠር፣የነገ ብቁና ውጤታማ አትሌቶችን ማፍራት ዋነኛ አላማው አድርጎ በተካሄደው ሻምፒዮና ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የሻምፒዮናው አጠቃላይ የአሸናፊነትን ዘውድ ደፍቶ፣መቻል እና ኢትዮ ኤሌክትሪክ እንደየቅደም ተከተላቸው ሁለተኛና ሶስተኛ ደረጃን በመያዝ ተጠናቋል።

👉 ዳግም የተወለደው ዕድሜ ጠገቡ ሻምፒዮና

ከመክፈቻው እስከ መዝጊያው የነበረው ድባብ፣ሪከርዶች መሠባበራቸው፣በታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ ከ54 ዓመታት በኃላ በ Time Tronix መሳሪያ ታግዞና ዘምኖ የተጠናቀቀውን የኢትዮጵያ ሻምፒዮና ልብ ብሎ ለተመለከተው ዕድሜ ጠገቡ ሻምፒዮና ዳግም ተወልዷል ቢባል ቃሉ ግነት የለውም።

ከምንም በላይ ዘመኑን የዋጀ፣ከማንዋል ወደ ዲጂታል መሸጋገሩን ያበሠረ ታይም ትሮኒክስን በሻምፒዮናው መጠቀሙ ለአትሌቲክሱ ትንሳኤ፣ለአትሌቱ ደግሞ ከፍተኛ ደስታን ከማጎናፀፋቸው ሌላ በሁለቱም ፆታ በቦትስዋና ጋብሮኒ ለሚደረገው የአለም አትሌቲክስ ሪሌሚኒማ ለማሟላት ወደ ሌላ ሀገር የሚደረግ ስደትን፣የገንዘብ ብክነትንና ድካምን ያስወገደ ከመሆኑም በላይ በቀጣይ ፌዴሬሽኑ እያሠበ ላለው የብ/ቡድን ምስረታም አመላካችም ሆኖም ታይቷል።

👉የማይካደው የኮማንደር አትሌት ስለሺ ስህን የላቀ ሚና

ከ54 ዓመታት በኃላ የደመቀ ሻምፒዮና እንዲታይ የበርካቶች ጥረት እንዳለ መካድ ባይቻልም በተለይ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት የኮማንደር አትሌት ስለሺ ስህን ሚና ግን የላቀውን ቦታ ይይዛል።

ፕሬዝዳንቱ ኮማንደር አትሌት ስለሺ ስህን ሰባቱንም ቀን በአካል በመገኘት፣አስፈላጊውን መመሪያና አቅጣጫ በመስጠት፣በተለይ ከፍተኛ ወጪ ወጥቶበት ተጥሎ የነበረው ታይም ትሮኒክስ ከወደቀበት ተነስቶ አዋራው ተራግፎ ዳግም እንዲጠገን፣4 ባለሙያዎችን(2 ከቤልጅየም 1ከናይጄሪያ፣1 ዛምቢያ) በማስመጣት ለአገልግሎት እንዲውልና የውድድሩ ድምቀት እንዲሆን በሀገሪቱ የሚገኙ የስፖርት ሳይንስ ሙሁራንና ባለሙያዎችን በማሠባሠብ ብቁ የሠው ኃይል ለማፍራትና በሀገር አቅም ለመጠቀም ከውጪ በመጡ ባለሙያዎች ስልጠና በመስጠት በቀጣይ ውድድሮች በራሳችን ባለሙያዎች የሚመራበት ዕድል እንዲፈጠር ፕሬዝዳንቱ በቃላት የማይገለፅ ሚና መጫወታቸው ነው የተሠማው፤

ይሄ ብቻም አይደለም አራቱ የታይም ትሮኒክስ ባለሙያዎችም በቆይታቸው ተደስተው እንዲሄዱ፣በመንከባከብ፣የሽኝት እራት ፕሮግራም በማዘጋጀት፣በግላቸው ለውድድር የሚሆን ዶላር በማውጣትና ወጪዎቹን በመሸፈንና፣ከአለም አትሌቲክስ ጋር ፌዴሬሽኑ መልካም ግንኙነት እንዲኖረውም ከፍተኛ ስራ ሠርቷል፤ ስለዚህም ፕሬዝዳንት ኮማንደር አትሌት ስለሺ ስህን
ምስጋና የሚያንሠው ካልሆነ የሚበዛበት አይሆንም።

ውድድሩን በማስተባበር፣ቴክኖሎጂው እንዲተገበር በማድረግ በኩል የውድድሩ ዳይሬክተር አቶ ጊዜ አድነው እንዲሁም የአጭር ርቀት ውድድሮች ብ/ቡድን በመመስረት ጥሩ ስራ ሠርቷል፤የፅ/ቤት ኃላፊው አመንሲሳ ከበደ(ዶ/ር) በቦትስዋና የሚደረገው ውድድር ላይ ሚኒማ ለማሟላት ከዚህ በፊት ናይጄሪያ ድረስ ብዙ ወጪ ይወጣ የነበረውን የሚያስቀር አሠራር በመዘርጋታቸው የውድድሩን ከፍታ በመጨመራቸው እና ተስፋ ሰጪ መንገድ በማሳየታቸው ሁለቱ ምስጋና ይገባቸዋል ።

👉ሊመሠገኑ የሚገባቸው ባለሙያዎች

ከላይ ከተጠቀሱት በተጨማሪ ላለፉት 7 ቀናት የተካሄደው ሻምፒዮና እጅግ አድካሚና ፈታኝ ቢሆንም ፌዴሬሽኑ ውስጥ ያሉ የውድድር ባለሙያዎች፣አጠቃላይ የፌዴሬሽኑ ሙያተኞችና እና የአትሌቲክስ ዳኞችም ከጠዋቱ 12:00 ጀምሮ እስከ ማታ ድረስ በመስራት የውድድሩ ቅመሞች ሆነው በስኬት እንዲጠናቀቅ በማድረጋቸው ሁሉም የምስጋናው ፀበል ሊደርሳቸው ይገባል።

👉 ከ60 በላይ ጋዜጠኞች መታደማቸው ሌላኛው
የውድድሩ ሪከርድ

ቀደም ሲል ለአንድና ሁለት ሚዲያዎችና ጋዜጠኞች ብቻ በሩ ተከፍቶ ለሌሎች በመከርቸሙ ወደ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ደጃፍ ደርሠው የማያውቁትን ስመ-ጥር እና አንጋፋዎቹን ጨምሮ ከ60 በላይ ጋዜጠኞች ሻምፒዮናውን መታደማቸው ሌላኛው የፌዴሬሽኑ ስኬት ሲሆን የኮሚኒኬሽን(የህዝብ ግንኙነት)ከፍተኛ ባለሙያው መሀሪ ነጋሽ ሁሉም ጋዜጠኞች የቤታቸው ያህል እንዲሠማቸው፣አመለካከታቸው እንዲቀየር በማድረግ በኩል አኩሪ ስራ አከናውኗል ።

በተጨማሪም ወጣት መሀሪ ነጋሽ በፌዴሬሽኑ የማህበራዊ ትስስር ገፆች ፈጣን፣ቀልጣፋ ፣ተደራሽና ትኩስ መረጃ በማድረስ ቤተሠባዊነቱ ተጠናክሮ እንዲቀጥል የዘየደው ዘዴና የዘረጋው መስመር በመላው አለም ቀጥታ ስርጭት በማስተባበር እና ከውጭ የመጡት እንግዶችን አስፈላጊውን ድጋፍ በማድረግ በጎ ተግባር አከናውኗል ።

በተጨማሪም ውድድሩ ካለፋት ዓመታት በጣም በተሻለ የብራንዲንግ ስራ በመስራት ውድድሩ በውጪ አገር የሚካሄድ እስኪ መስል ድረስ ደረጃውን ከፍ በማድረግ የስፖርት ቤተሰቡን አስደምመዋል።
በዶክተር አያሌው የተመራው የህክምና ክፍልም ሳምንቱን ሙሉ ተቀናጅቶ በመስራትና ለተጎዱ አትሌቶች ተሎ በመድረስ ካለፈው ዓመት የተሻለ ስራ ሲሠራ ተስተውሏል።

በመዝጊያው መርሀ ግብር ላይ ሁሉም የፌዴሬሽኑ የስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባላት በሚባል ደረጃ ባልተለመደ መልኩ በአካል ተገኝተው መከታተላቸው እና እየተዘዋወሩ አትሌቶችን ማበረታታቸው የሚደነቅ አዲስ ጅምርም ሆኖ ታይቷል።
👉ማጠቃለያ:-ይታሠብበት
👉ሻምፒዮናው የደመቀ ቢሆንም እንከን
አልባ አልነበረም ማለት አይቻልም

በእርግጥ ውድድሩ ያማረና የደመቀ፣በተመልካችና በፉክክር የታጀበ፣በታይም ትሮኒክስ የታገዘ ሆኖ በድምቀት የተጠናቀቀ እንደሆነ ባይካድም እንከን አልባ አልነበረም ማለት ግን አይቻልም፤በዚህ በኩል በተለይ በታይም ትሮኒክስ አጠቃቀምና አተገባበር ዙሪያ ይስተዋሉ የነበሩ ክፍተቶች አትሌቶች ለውድድር ተዘጋጅተው ትራክ ላይ 20 እና 25 ደቂቃ የሚቆሙበት ክፍተት የሚጋነን ባይሆንም የውድድሩ ሠባራ ጎን ነበር፤

ይህ ትንሽ የሚመስል ስህተት በ One day meeting (ኮንትኔንታል ቱር)ላይ ክፍተት እንዳይፈጥር ከወዲሁ ስራ ሊሠራበትና ሊታሠብበት እንደሚገባ እየጠቆምን ባህልና ስፖርት ሚኒስቴር ትራክ ከማዘጋጀት ጀምሮ ሶስት ሚኒስትሮች በመክፈቻው ዕለት በመገኘት ከቀን ጀምሮ እሰከማታ ከፌዴሬሽኑና ከውድድሩ ጎን በመቆም አትሌቶችን ማበረታታቸው ያስመሠግናቸዋል።

✍️✍️በጋዜጠኛ ይስሀቅ በላይ(ሀትሪክ ስፖርት ኦፊሺያል)

ፎቶ ክሬዲት: የኢ.አ.ፌ ይፋዊ የፌስቡክ ገጽ

4 months ago

No replys yet!

Be the first to share what you think — your comment will appear here.