Logo
FIDEL POST NEWS
" ‎ይህ አይነቱ የወንጀል ድርጊት በአከባቢው ሲፈፀም የመጀመሪያ ነው። የሞት ፍርድ ውሳኔም የመጀመሪያ ነው " - አቶ ነጋልኝ ዓለሙ

በቡርጂ ዞን በውርስ ምክንያት 3 የቤተሰባቸውን አባላትን በጥይት ደብድበው የገደሉ ተከሳሾች በሞት እንዲቀጡ ተወሰነ።

‎ይህ በአከባቢው የመጀመሪያው የሞት ፍርድ ውሳኔ እንደሆነ ተገልጿል።

የወንጀል ድርጊቱ የተፈጸመው ‎ነሐሴ 16/2017 ዓ/ም ከምሽቱ 2:00 ሰዓት ገደማ በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ሶያማ ዙሪያ ወረዳ ገራ ቀበሌ መሆኑን በዞን ፍትህ መምሪያ የልዩ ልዩ ወንጀሎች ዘርፍ አስተባባሪ አቶ ነጋልኝ ዓለሙ ለቲክቫህ ኢትዮጵያ ገልጸዋል።

በዚሁ ቀበሌ አቶ ዋቶ ወርቁ የተባሉ አዛውንት ዕድሜያቸው እየገፋ መምጣቱን ተከትሎ በአከባቢው ባህል መሰረት ልጆቻቸውን ጠርተው የመሬት ውርስ ክፍፍል ማድረግ ይጀምራሉ።

ይህ እየሆነ ባለበት በሂደቱ ተቃርኖ የነበራቸው የአዛውንቱ የመጀመሪያ ልጅ እና የልጅ ልጃቸው ሁለቱም የክላሽ ኮቭ መሳሪያ በመታጠቅ በቤተሰብ አባላቱ ላይ ተኩስ መክፈታቸውን አቶ ነጋልኝ ለቲክቫህ ኢትዮጵያ ተናግረዋል።

‎በጥቃቱ አዛውንቱ አቶ ዋቶ ወርቁን እና ሁለት ልጆቻቸው ወዲያውኑ ሲሞቱ ሁለት የቤተሰብ አባላት ደግሞ ከባድ ጉዳት ደርሶባቸው ወደ አርባምንጭ ሪፌራል ሆስፒታል መላካቸውን ገልፀዋል።

‎ፖሊስም ግለሰቦቹን ከነመሳሪያቸው ኤግዚቢትነት በመያዝ ምርመራ ማድረግ ይጀምራል። መዝገቡንም አደራጅቶ ለዞኑ ዐቃቤ ሕግ ያቀርባል።

‎ዐቃቤ ሕግ መዝገቡን በማደራጀት በሁለቱ ተከሳሾች ላይ በዋና ወንጀል አድራጊነት ፦
• በሶስት የግድያ ወንጀል ክስ በወንጀል ህጉ አንቀጽ 539/1/ሀ መሠረት በከባድ የሰዉ ነብስ ማጥፋት ወንጀል
• ሁለት በህይወት በተረፉ የግል ተበዳዮች ወንጀል ሁለት ክስ በወንጀል ህግ አንቀጽ 27 እና 539/1/ሀ መሠረት ክስ ማቅረቡን አቶ ነጋልኝ አስረድተዋል።

‎ተከሳሾች ፍርድ ቤት ቀርበው የወንጀል ድርጊቱን ስለመፈፀማቸው ተጠይቀው " አልፈፀምንም " በማለት ክደዉ ተከራክረዋል።

አቃቤ ህግ በሰዉና በሰነድ ማስረጃ አምስቱንም ክስ በሚገባ ያስረዳ ሲሆን ተከሳሾች የቀረበባቸዉን ክስ መከላከል ባለመቻላቸው የቡርጂ ዞን ከፍተኛ ፍ/ቤት ተከሳሾችን በቀረበባቸው ክሶች ጥፋተኛ ናቸው ብሏል።

የፈፀሙት ወንጀል ጭካኔ የተሞላበትና አስነዋሪ መሆኑ ፤ በአከባቢው ከዚህ ቀደም ተደርጎ የማይታወቅ ፤ ከሁለት በላይ የሆነ የቤተሰብ አባላት ላይ በአንድ ጊዜ የተፈፀመ ግድያ መሆኑን ከግምት ውስጥ ገብቷል።

ፍርድ ቤቱ ሁለቱም ተከሳሾች በሞት እንዲቀጡ ውሳኔ አስተላልፏል።

‎ይህ አይነቱ የወንጀል ድርጊት በአከባቢው ሲፈፀም የመጀመሪያ ነው ያሉት አቶ ነጋልኝ የሞት ፍርድ ውሳኔም በዞኑ የመጀመሪያ ነው ሲሉ ገልፀዋል።

ቲክቫህ ኢትዮጵያ
ሀዋሳ
መጋቢት 18 ቀን 2018 ዓ/ም

tikvahethiopia
4 months ago

No replys yet!

Be the first to share what you think — your comment will appear here.