Logo
YenetaTube
በኬንያ አብያተ ክርስቲያናት ብሔራዊ ምክር ቤት ቦታ ላይ 32 ሰዎች በጅምላ ተቀብረው ተገኙ

የኔታ ሚዲያ

በምዕራብ ኬንያ ኬሪቾ በተባለች ከተማ ውስጥ በሚገኝ የጅምላ መቃብር አብዛኞቹ ህጻናት የሆኑ የ32 ሰዎች አስከሬን ተቆፍሮ ወጥቷል። ጉዳዩን በተመለከተ አስደንጋጭ ምርመራዎች ቀጥለዋል።

የአስከሬን ቁፋሮው የተከናወነው ፖሊስ መጀመሪያ ላይ በቦታው ተቀብረዋል ተብለው የታሰቡትን 14 አስከሬኖች ለማውጣት የፍርድ ቤት ትዕዛዝ ካገኘ በኋላ ነው። የመንግስት ፓቶሎጂስት ሪቻርድ ንጆሮጌ ማክሰኞ ምሽት ለጋዜጠኞች እንደተናገሩት በከባድ ዝናብ ለተወሰነ ጊዜ ተቋርጦ በነበረው የሙሉ ቀን ቁፋሮ የተገኘው ነገር በጣም ያልተለመደ እና አስከሬኖቹ በጆንያ ውስጥ ተደርድረው የተገኙ መሆናቸውን ገልጸዋል።

የአስከሬን ምርመራ (Post-mortem) ረቡዕ ዕለት ይጀምራል ተብሎ የሚጠበቅ ሲሆን የሟቾቹን ማንነት በፍጥነት ለመለየትና ለሞታቸው ምክንያት የሆኑ ሁኔታዎችን ለማጣራት ጥሪዎች እየቀረቡ ነው።

ንጆሮጌ እንዳሉት ሰባት አዋቂዎች እና 25 ህጻናት የተገኙ ሲሆን ህጻናቱ ጨቅላዎችና ፅንሶች ናቸው።

በተጨማሪም የተወሰኑ የሰውነት ክፍሎች ተገኝተዋል ፓቶሎጂስቱ አክለውም አንዳንድ አስከሬኖች ከሆስፒታሎች እና ከአስከሬን ማቆያ የመጡ ይመስላሉ ሆኖም ይህ የሚረጋገጠው ከአስከሬን ምርመራ በኋላ እንደሆነ ገልጸዋል።

የአዋቂዎቹ አስከሬን በጣም የፈረሰ (decomposed) ሲሆን የህጻናቱ ግን ያን ያህል አለመሆኑ ግለሰቦቹ በተለያዩ ጊዜያት እንደሞቱ የሚያመለክት መሆኑን ጠቁመዋል።

ማክሰኞ ዕለት ነጭ መከላከያ ልብሶችን ጓንቶችን እና ማስኮችን የለበሱ የፎረንሲክ ቡድኖች ጥብቅ ጥበቃ በሚደረግበት ቦታ ላይ ቁፋሮውን ሲያከናውኑ ውለዋል።

ይህ የአስከሬን ቁፋሮ የተከናወነው በአንድ ጥቆማ ሰጪ አማካኝነት ፖሊስ ምርመራ ከጀመረ በኋላ ነው ሰኞ ዕለት የወንጀል ምርመራ ዳይሬክቶሬት (DCI) እንደገለጸው መጀመሪያ ላይ የተገኙት መረጃዎች እንደሚያሳዩት 13 ባለቤት ያልተገኘላቸው አስከሬኖች ከጎረቤት ኒያሚራ ግዛት ሆስፒታል በይፋ ተለቀው ባለፈው አርብ በኬሪቾ እንዲቀበሩ ተወስደው ነበር።

ይሁን እንጂ ስለተጨማሪዎቹ አስከሬኖች እና ስለ አቀባበሩ ሁኔታ አሁንም ብዙ ጥያቄዎች እየተነሱ ነው አስከሬኖቹ የኬንያ አብያተ ክርስቲያናት ብሔራዊ ምክር ቤት (NCCK) ንብረት በሆነው ቦታ ላይ እንዴት ሊቀበሩ እንደቻሉ ግልጽ አይደለም።

ምክር ቤቱ ግን ከምስጢራዊው ቀብር ጋር ምንም ዓይነት ግንኙነት እንደሌለው አስተባብሏል።

የድርጅቱ ባለስልጣን ለሀገር ውስጥ ጋዜጣ Daily Nation እንደተናገሩት ቀብሩ የተከናወነው ያለእነሱ ፈቃድና እውቅና ነው።

የታሰሩ ተጠርጣሪዎች እና የሰብአዊ መብት ተሟጋቾች ምላሽ
የወንጀል ምርመራ ዳይሬክቶሬት (DCI) ከቀብር ሂደቱ መዛባት በተጨማሪ ሌላ የወንጀል ድርጊት መኖር አለመኖሩን እያጣራ መሆኑን ገልጿል።

ከጉዳዩ ጋር በተያያዘ የኒያሚራ የሕዝብ ጤና መኮንን እና የመቃብር ቦታ ጠባቂ በቁጥጥር ስር የዋሉ ሲሆን ሌሎችም ጥያቄ እየቀረበላቸው ነው።

ቮካል አፍሪካ የተሰኘው የሰብአዊ መብት ተሟጋች ቡድን ግኝቱ የአሳዛኙን ክስተት ትክክለኛ መጠን የሚያሳይ እና አስደንጋጭ ነው ብሎታል።

ቡድኑ አክሎም በአስከሬኖቹ ላይ የታዩት የመቆራረጥ ምልክቶች አስቸኳይ ግልጽ የሆነ ምርመራ እና ብሔራዊ ተጠያቂነትን የሚጠይቅ የጥቃት ደረጃን ያመለክታሉ ብሏል።

የኬንያ የሕግ ማህበር ፕሬዝዳንት ፌዝ ኦዲአምቦ በበኩላቸው የእነዚህ ሰለባዎች ማንነት በተቻለ ፍጥነት መለየት አለበት ሲሉ አሳስበዋል።

3 months ago

No replys yet!

Be the first to share what you think — your comment will appear here.