Logo
YenetaTube
ግልጽነት የጎደለው የነዳጅ ቁጠባ መመሪያ፤ ለማደያ ባለቤቶች የፈለጉትን እንዲያደርጉ 'ፍቃድ' ሰጥቷል ተባለ

የነዳጅና ኢነርጂ ባለሥልጣን ያወጣው የነዳጅ ቁጠባና የቅድሚያ አሰጣጥ መመሪያ፣ ግልጽነት የጎደለውና ለብልሹ አሰራር በር የሚከፍት መሆኑን የዘርፉ ባለሙያዎችና ተጠቃሚዎች ገለጹ።

መንግስት በመካከለኛው ምስራቅ ካለው ቀውስ ጋር ተያይዞ የነዳጅ አቅርቦት እጥረት እንዳይከሰት በሚል "ለሕዝብ ትራንስፖርትና ለልማት ፕሮጀክቶች ቅድሚያ ይሰጥ" የሚል መመሪያ ቢያወጣም፣ አተገባበሩ ግን በማደያዎች ዘንድ ለግል ጥቅምና ለተጠቃሚዎች እንግልት መዳረጊያ እየሆነ መጥቷል።

ጉዳዩን በቅርበት የሚከታተሉ የዘርፉ ባለሞያዎች ለካፒታል እንደሚሉት፣ መመሪያው በዝርዝር አፈጻጸም ያልተደገፈና "የተሸፋፈነ" በመሆኑ ለማደያ ባለቤቶች እንደፈለጉ እንዲያደርጉ ያልተገደበ ስልጣን ሰጥቷቸዋል።

በማደያዎች ዘንድ ለግል ተሽከርካሪ ባለቤቶች "ዞር በል" ወይም "ነዳጅ የለም" ለማለት እንደ ዋነኛ ሰበብ እየቀረበ ይገኛል።

ይህም ተሽከርካሪዎች ለሰዓታት ተሰልፈው ነዳጅ እንዳያገኙ ከማድረጉ ባለፈ፣ "ተጨማሪ ብር ከከፈልክ ትቀዳለህ" የሚሉ የሙስና ጥያቄዎች እንዲበራከቱ ምክንያት ሆኗል።

"ነዳጅ ጨምሮብናል፣ አሁን ደግሞ ማግኘት እንኳን አልቻልንም" የሚሉ የግል ተሽከርካሪ ባለቤቶች፣ መመሪያው ወጥ በሆነ መልኩ የማይተገበርና ለአድልዎ የተጋለጠ መሆኑን ይገልጻሉ።

በተመሳሳይ መልኩ አሽከርካሪዎች "የነዳጅ ምርቶችን ለማግኘት አስቸጋሪ እየሆነባቸው እንደሚገኝ" በመግለፅ ቅሬታ እያቀረቡ ሲሆን፣ በዚህም ምክንያት ከተፈቀደው ታሪፍ በላይ ጭማሪ እያደረጉ እንደሚገኙ ካፒታል ለመረዳት ችሏል። ይህም በትራንስፖርት ተጠቃሚው ማህበረሰብ ላይ ተጨማሪ የኢኮኖሚ ጫና ፈጥሯል።

ባለሙያዎች እንደሚመክሩት፣ መንግስት እንዲህ አይነት መመሪያዎችን ሲያወጣ ግልጽ የሆነ የክትትልና የቁጥጥር ስርአት አብሮ መዘርጋት ይኖርበታል። አለበለዚያ መመሪያው አቅርቦትን ከማስተካከል ይልቅ፣ ለብልሹ አሰራርና ለህገ-ወጥ ግብይት 'ህጋዊ ሽፋን' መስጠቱን ይቀጥላል ሲሉ አስጠንቅቀዋል።

Via Capital

3 months ago

No replys yet!

Be the first to share what you think — your comment will appear here.