Logo
FastMereja
ሀገር አቀፍ የስፔሻል ኦሊምፒክ ውድድር ሊካሄድ ነው

​#fastmereja | 11ኛው የዓለም የዳውን ሲንድሮም ቀን በኢትዮጵያ “ብቸኝነትን በአንድነት እንመክት” በሚል መሪ ቃል ከመጋቢት 4 እስከ 6 ቀን 2018 ዓ.ም በተለያዩ ስፖርታዊ ውድድሮች እንደሚከበር ተገለጸ።

​ስፔሻል ኦሊምፒክስ ኢትዮጵያ ከ“ፍቅር የኢትዮጵያ የአእምሮ ዕድገት ውስንነት ብሔራዊ ማኅበር” ጋር በመተባበር የሚያዘጋጁት ይህ ሀገር አቀፍ ጨዋታ በኢትዮጵያ ስፖርት አካዳሚ ለሦስት ቀናት ይካሄዳል።

​ዝግጅቱ ሁሉንም የኦሊምፒክ ስፖርት ዓይነቶች የሚያካትት ሲሆን፣ ውድድሩም የአእምሮ ዕድገት ውስንነት ያለባቸውን ተወዳዳሪዎች ባማከለ ልዩ የስፖርት ሕግ መሠረት የሚከናወን ይሆናል።

​የኢትዮጵያ ስፔሻል ኦሊምፒክ ኮሚቴ በባህልና ስፖርት ሚኒስቴር ዕውቅና አግኝቶ ከተደራጀበት ጊዜ ጀምሮ፣ የአእምሮ ዕድገት ውስንነት ያለባቸው ዜጎች በስፖርት ተሳታፊና ተጠቃሚ እንዲሆኑ ከሀገር ውስጥና ከዓለም አቀፍ አጋሮች ጋር እየሠራ ይገኛል።

​የፍቅር ኢትዮጵያ ማህበር የአእምሮ ዕድገት ውስንነት ያለባቸውን ልጆች አስተምሮና አሰልጥኖ በማኅበሩ ውስጥ የሥራ ቅጥር እንዲያገኙ በማድረግ ጭምር አርአያነት ያለው ሥራ እያከናወነ ይገኛል።

​በአሁኑ ወቅት በአፍሪካና በኢትዮጵያ የአእምሮ ዕድገት ውስንነት ያለባቸው ወገኖች ላይ የሚደርሰው መገለልና መድልዎ ከፍተኛ በመሆኑ፣ እንዲህ ያሉ ስፖርታዊ መድረኮች ግንዛቤን ለመፍጠርና ብቸኝነትን ለመቀነስ ትልቅ ፋይዳ አላቸው።
#ኹነት

5 months ago

No replys yet!

Be the first to share what you think — your comment will appear here.