Logo
FIDEL POST NEWS
በሀዋሳ ከተማ የ6 ወር ነፍሰጡር የትዳር አጋሩን በአሰቃቂ ሁኔታ የገደለው ግለሰብ በእድሜ ልክ እስራት ተቀጣ

‎         
‎ተከሳሹ ዩኤ ወይንም ዮሐንስ ቃቃዎ የተባለ ሲሆን በሀዋሳ ከተማ አስተዳደር ቱላ ክፍለ ከተማ ሀዌላ ወንዶ ቀበሌ ልዩ ስፍራው ካፋሪ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ታህሳስ 8 ቀን 2018 ዓ/ም  ከቀኑ 11:00 ሰዓት ገደማ የ6 ወር ነፍሰጡር የሆነችውን የትዳር አጋሩ አበበች ዲጋሳን  በዕለታዊ ግጭት በተነሳ ፀብ ጭካኔ በተሞላ መልኩ ህይቷን እንድታጣ ማድረጉን የሀዋሳ ከተማ አስተዳደር  ፖሊስ መምሪያ አዛዥ ረ/ኮሚሽነር ግርማ ማቴዎስ ለብስራት ሬድዮ ተናግረዋል ።

‎እንደ ኃላፊው ገለፃ ግለሰቡ ጭካኔ በተሞላበት መልኩ የሰውነት ክፍሏን በስለት ቆራርጦ ከገደላት በኋላ አስክሬኗን ገደል ውስጥ መጨመሩን ተናግረዋል። ፖሊስ ተከሳሹ የፈፀመውን ወንጀል በሰውና በሰነድ ማስረጃ ካጣራ በኋላ  ለሀዋሳ ከተማ አስተዳደር ከፍተኛ ዓቃቤ ህግ መዝገቡን አስተላልፏል።

‎የምርመራ መዝገቡ የደረሰው የሀዋሳ ከተማ አስተዳደር ከፍተኛ ዓቃቤ ህግ የኢ/ፌ/ዴ/ሪ የወንጀል ህግ አንቀፅ 539(1-ሀ)ስር የተመለከተውን በመተላለፍ በፈፀመው ከባድ የሰው ግድያ ወንጀል ክስ በመመሰረት ለሀዋሳ ከተማ ከፍተኛ ፍ/ቤት አቅርቧል።

‎የሀዋሳ ከተማ ከፍተኛ ፍ/ቤትም የቀረበለትን መዝገብ ከተመለከተ በኋላ የተከሳሹን ጥፋትኝነት በማረጋጥ  የካቲት 25 ቀን 2018 ዓ/ም በዋለው የወንጀል ችሎት ተከሳሽ ዮሐንስ ቃቃዎ ያስተምራል ሌሎችን ያስጠነቅቃል በማለት በእድሜ ልክ ፅኑ እስራት እንዲቀጣ ውሳኔ ማሳለፉን ረዳት ኮሚሽነር ግርማ ማቴዎስ ለብስራት ሬድዮ ጨምረው ተናግረዋል ።

በሰብል አበበ
#ዳጉ_ጆርናል
5 months ago

No replys yet!

Be the first to share what you think — your comment will appear here.