Logo
Getu Temesgen
የብሔራዊ ምርጫ ቦርድና እና የፌድሬሽን ምክር ቤት ስልጣን (ከሀገር አቀፍ ምርጫ አንጻር ያላቸው ፋይዳ)

ጠበቃና የህግ አማካሪ ፋንታሁን ደለለው
0929101037/0983337690

መግቢያ #ethiopia | ለዚህ ጽሁፍ መነሻ የሆነኝ የፌድሬሽን ምክር ቤትን እና የብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ስልጣን መለየቱ አስፈላጊ ሆኖ በመገኘቱ ማንም የመንግስት አካል ፣ ዜጋ ሆነ ይህንን የምርጫ ማስፈጸም ስራ የሚሰራ አካላት ባለሙያዎች እንደ ተሰጣቸው የህግ ስልጣን ልክ ብቻ እንጂ ከስልጣናቸው በማለፍ የብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ስልጣን ውስጥ በመግባት ምርጫው በህገመንግስቱ ከተቀመጠው አላማና ሀሳብ ውጭ እንዳይሆን ይልቁንም ምርጫው ነጻ፣ሚስጥራዊነቱን የተጠበቀ፣ሁሉአቀፍ፣የእኩልነት መርህ የጠበቀ እንዲሆን የሚመለከተው የመንግስት አካል በሙሉ በመራጮችና በተመራጮች ዘንድ ተጽእኖ፣ማስፈራራትና ዛቻ እንዳይደርስባቸው የውድድር ሜዳው ለሁሉም እኩል እና የተመቻቸ እንዲሆን አስፈላጊውን ሊያደርጉ ይጠበቅባቸዋል። ምርጫ የዲሞክራሲያዊ በተለይም የገዢው መንግስት ሰላም ወዳድነት መገለጫ ነው።

ስለሆነም መንግስት ሁሉም አካላት ራሱንም ጨምሮ ለምርጫው መሟላት አስፈላጊውን እንዲያደርግ የሚጠበቅበት ሆኖ የምርጫ ቦርድም ገለልተኛ ሆኖ በኢትዮጵያ የሀገሪቱ ግዛት በሙሉ ምርጫው የምርጫ መርሆችና ህጎችን በጠበቀ መልኩ ሊያከናውን ይገባል። ሆኖም ሁሉም የመንግስትም አካላትም ሆነ ተፎካካሪ ፓርቲዎች ምርጫ ቦርድን ጨምሮ በተለይም የፌድሬሽን ምክር ቤት ስልጣናቸውን በአግባቡ በመለየት ምርጫው የተሳካ እንዲሆን አስፈላጊውን ማድረግ ይጠበቅባቸዋል።

1. የህዝብ ተወካዮችን ወንበር በምርጫ ማግኘት የሚቻለው ምንን መሠረት በማድረግ ነው?

በሀገር አቀፍ ደረጃ በየአምስት አመቱ የሚደረገው ምርጫ በኢፊድሪ ህገመንግስት አንቀጽ 54/1/ መሠረት ነጻ፣ሁለአቀፍ፣ቀጥተኛ፣ትክክለኛ በሆነና ድምጽ በሚስጥር መሆን እንዳለበት የሚደነግግ ሲሆን እነዚህ የምርጫ መርሆች ሲሆኑ ማንም አካል ሊያከብራቸው የሚገባቸው ናቸው።

በዚህ አንቀጽ ንኡስ አንቀጽ ሁለት ላይ ያለውን ስንመለከት የምርጫ ተወዳዳሪዎች በተመደበላቸው የምርጫ ጣቢያ መሠረት የሚወዳደሩ ሲሆን የምርጫ ጣቢያውም አጠቃላይ በሀገር አቀፍ ደረጃ ያለው ቁጥር የህዝብ ተወካዮች ያለው ቁጥር ሲሆን በህገመንግስቱ አንቀጽ 54/3/ ላይ እንደተቀመጠው 550 የማይበለጥ ነው።

ይህ ምርጫ ጣቢያ በሀገር አቀፍ ደረጃ ተመድቦ ምርጫው የሚካሄደው በዋናነት የህዝብ ብዛትን ከአሰፋፈሩ አንጻር መሠረት ባደረገ መልኩ እንጂ ብሔር ፣ብሔረሰብን ማንነትን ምክንያት በማድረግ አይደለም። ይሁን እንጂ ከአሰፋፈራቸው እና ብሔር ብሔረሰባቸው እጅግ አናሳ የሆኑ በምክር ቤቱ ድምጽ እንዳያጡ ሲባል ብቻ እስከ 20 ወንበር ድረስ ይፈቀድላቸዋል።

ይህ እንዴት ሊሆን ይችላል የሚለውን ጉዳይ በተመለከተ እነዚህ ህዝቦች ውክልና እንዳያጡና በህገመንግስቱ እና በሌሎች ህጎች የተቀመጡትን መብቶች እንዳያጡ እንዴት ውክልና በምክር ቤት እንደሚያገኙ በዝርዝር በህግ እንደሚወሰን በዚህ ድንጋጌ ተቀምጧል።

ይህንን ህግ ለማውጣት ስልጣን የተሰጠው አካል እንደሚታወቀው ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሲሆን ይህን አስመልክቶ መመሪያን የማውጣት ስልጣን ለፌድሬሽን ምክር ቤት ወይም ለምርጫ ቦርድ ሊሰጥ የሚችል ሲሆን ነገር በስልጣናቸው ልክ ከፋፍሎ በአዋጁ ቢሰጥ በጣም የተሻለ ይሆናል።

በአጠቃላይ የዚህ ክፍል ዋናው መሠረታዊ አላማ የምርጫ ጣቢያ ምደባ አስተዳደር ምን መሠረት ያደረገ ነው የሚል ሲሆን ከላይ እንዳስቀመጥነው በህዝብ ብዛትና አሰፋፈር እንጂ የብሔር ብሔረሰብ ማንነት ጉዳይ እንዳልሆን መገንዘብ ያለብን ሲሆን አናሳ ብሔረሰቦች ብቻ ውክልና እንዳያጡ በበምክር ቤቱ መቀመጫ እንዲያገኙ እስከ 20 ወንበር ድረስ የሚመቻችላቸው መሆኑን በህገመንግስቱ አንቀጽ 54 መሠረት መረዳት የሚቻል ነው።

2. የምርጫ ቦርድ

ምርጫ ቦርድ ምርጫዎችን ለማከናወን የምርጫ ጣቢያዎችን ማመቻቸትና ማደላደል የሚጠበቅበት ሲሆን ይህም እንደ ህዝብ አሰፋፈሩ ፣ቁጥር በዚያ አከባቢ ያለው ህዝብ የምርጫ ፍላጎት በመረዳት የምርጫ ጣቢያዎችን አግባብ ባለው መልኩ ማመቻቸት ነው። በሀገራችን በህዝብ ተወካዮች ወይም በፓርላማ የሚገኙ መቀመጫዎች በኢፊድሪ ህገመንግስት አንቀጽ 54/3/ መሠረት የተወካዮች መቀመጫ ቁጥር 550 መሆናቸው ይታወቃል።

በእነዚህ መቀመጫዎች ልክ የምርጫ ጣቢያዎች ቁጥር ወይም ብዛት ይኖራሉ። ይህ የማንነት መብት መጠበቂያ ወይም የድንበር መለያ ጉዳይ አይደለም። ነገር ግን በዚህ አከባቢ ያለው ህዝብ ከቁጥሩ አሰፋፈሩ ፣ የፖለቲካ ምህዳር ውጤት ከማስከተሉ አንጻር የምርጫ ጣቢያ የሚያስፈልግ መሆኑ ሲታመንበት የምርጫ ጣቢያ ይቋቋማል።

3. የምርጫ ቦርድ ከማንም የመንግስት አካል ነጻ በመሆን ራሱ ገለልተኛ ሆኖ በአዋጆቹ በደንብ እና ራሱ በሚያወጣው መሠረት በፍርድ ቤት እስከ አልተከለሰ ድረስ ወጥና ተጨባጭ በሆነ መንገድ ሊጓዝ ይገባል። የምርጫ ቦርድ የክልሎችን ድንበር የመወሰን ስልጣን የለውም። ማንም ብሔር፣ብሔረሰብ ወደ የትኛውም ክልል በፌድሬሽን ምክር ቤት ተካለለ ቢባል ገባ ወይም ወጣ ቢባል ማንም የፖለቲካ ፓርቲ ተፎካካሪ ድርጅት በየትኛውም ክልል ሄዶ የመወዳደር መብት አለው። በዚህን ጊዜ የሚመርጠው በዚያ ቦታ የሰፈረው ዜጋ እንጂ ህዝብ እንጂ የፌድሬሽን ምክር ቤት ወይም ሌላ የመንግሥት አካል አይደለም።

ምርጫ ሚስጥራዊ፣ነጻ፣የእኩልነት መርህ የተከተለ፣ሁሉአቀፍ ነው እስከተባለ ድረስ ይህንን በማስከበር ረገድ የምርጫ ቦርድ እና መንግስት ታዛቢ አካላት ሌሎችም አስፈላጊውን ድጋፍ ሊያደርጉ ይገባል እንጂ የድንበር ማካለል፣ክልሎችን በአዲስነት የመወሰን ተግባር ከምርጫ አላማ ጋር ሊያያዝ አይገባም። አለበለዚያ ጥያቄ ሊሆን የሚችለው የክልል አስተዳደር ተጽእኖ በምርጫ ሂደት ላይ የሚከሰት ነው ብሎ ካልታመነበት በቀር ተወዳዳሪ ፓርቲ የድርጅቱን መግለጫ በማሳወቅ የትም ቦታ መወዳደር ይችላል።

ነገር ግን ሌላ ጥያቄ ሊሆን የሚችለው ለክልል ምክር ቤት ለመወዳደር እንዴት ሊሆን ይችላል በሚለው ሊነሳ የሚችል ሲሆን በዚህም ቢሆን የትኛውም ተፎካካሪ ፓርቲ በየትኛውም ክልል የመወዳደር እና የምክር ቤት ወንበር የማግኘት መብት የክልል መንግስት የመመስረት መብት ስላለው ከዚህ አንጻር በመረዳት አቅም ፈጥሮ መወዳደር ነው እንጂ የድንበር ማካለል የብሔረሰብ ከክልሎች መደመር ወይም መቀነስ ጋር በማያያዝ የምርጫ አካሄድ ስረአት እና አላማን ልናያይዝ አያስፈልግም።

4. የፌድሬሽን ምክር ቤት አካራካሪ ሆኖ የተገኘው ስልጣን
የፌድሬሽን ምክር ቤት የክልል ድንበር ማካለል ስራዎች ሊሰራ ይችላል ይህ ስልጣኑ ነው። ነገር ግን የምርጫ ጣቢያ የመወሰን፣የማደላደል ስራዎችን ሊሰራ አይችልም። ይህን ማድረግ በህገ መንግስቱ አንቀጽ 62 መሠረት ከተቀመጠው ወጭ ስለሚሆንበት ስልጣኑን አላግባብ መጠቀምና የምርጫ ቦርድ ስልጣን ነጻ ምርጫ ላይ ተጽእኖ ማሳደር ነው። ይህ ደግሞ በህገመንግስቱ አንቀጸሸ 38 ላይ የተቀመጠውን ነጻ ምርጫ በሚለው ላይ ተጽእኖ ማሳደር ስለሚሆን ኢ ህገመንግስታዊ ነው።

ይሁን እንጂ ምርጫ ቦርድ በተሰጠው ስልጣን መሠረት ሀገራዊ ምርጫዎችን ለማድረግ ያመቸው ዘንድ የፌድሬሽን ምክር ቤት ስልጣኑን መሠረት ለምርጫዎች አመቺ ሁኔታን ከመፍጠር አንጻር የሚያመቻቸው ጉዳይ ውሳኔ የህግ መንግስት ትርጉም ካለ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ይህንን ለማጥራት ወይም ለማጣራት የህገ መንግስት ማብራርያ እና መሠል ቀድመው ሊፈጸሙ የሚችሉ ጥያቄዎችን ከመጠየቅ የሚከለክለው ነገር የለም።

5. ምርጫ ቦርድ መጠቀም ያለበት የህግ ሀይል ምንድ ነው?

ምርጫ ቦርድ ዜጎች በየትኛውም የሀገሪቱ ከፍሎች ቢሆኑ ቋሚ መኖሪያቸው እስከ ሆነ ድረስ ማንም ተፎካካሪ የፖለቲካ ድርጅት ለመመረጥ ሲቀርብ አይቶ መርምሮ የምርጫ መርሆችን ህጎችን በጠበቀ መልኩ ማንም ዜጋ እንዲመርጥ ወጥ፣ተቀባይነት ያለው መመርያ የማውጣት ስልጣን እስካለው ድረስ በዚህ መሠረት አዋጭ ግልጽ ዝርዝር መመሪያ በማውጣት ተግባራዊ ሊያደርግ ያስፈልጋል።

6. መደምደምያ

በድንበር ማካለል ወይም በብሔር ብሔረሰብ ማንነት ጥያቄ ተከትሎ በሚከሰት የፌድሬሽን ምክር ቤት ውሳኔ እና አሰራር ምክንያት ሳይሆን በህዝብ ብዛትና አሰፋፈርን መሠረት በማድረግ የምርጫ ቦርድ በሚያስተዳድረው የምርጫ ክልሎች አማካኝነት ተፎካካሪ ፓርቲዎች በሚያደርጉት የምርጫ ተቀባይነት በምክር ቤት አብላጫ ድምጽ በመያዝ መንግስት የሚመሰርቱበት ነው።

ማጣቀሻዎች
1. የኢፊድሪ ህገመንግስት፤ አዋጅ ቁጥር 1/1987
2. የፌዴሬሽን ምክር ቤት ለማቋቋም የወጣ አዋጅ ቁጥር 1262/2013
3. የምርጫ ቦርድ ለማቋቋም የወጣ አዋጅ ቁጥር 1133/11
4. የየኢትዮጵያ የምርጫ፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባና
የምርጫ ሥነምግባር አዋጅ…1162/11
https://t.me/Fantahunlawye...
https://www.facebook.com

3 months ago

No replys yet!

Be the first to share what you think — your comment will appear here.