Logo
FIDEL POST NEWS
የደም ትስስርና የነፍስ ጩኸት፡ ከዐድዋ ተራሮች እስከ ጋርቬይ

​ዐድዋ አንድ ሺ ጊዜ ቢነገር አንድ ሺ መልዕክት ያለው ድል ነው።ዓለም በአሥራ ዘጠነኛው ክፍለ ዘመን ማብቂያ ላይ ለጥቁር ሕዝቦች አስከፊ ነበረች። አፍሪካ በበርሊን የካርታ ጠረጴዛ ላይ እንደ ታረደ በሬ በቅርጫ ተከፋፍላ፣ ልጆቿ በገዛ ምድራቸው ባዕድ ሆነው ነበር።

በባሕር ማዶ፣ በአሜሪካና በካሪቢያን ደሴቶች፣ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ጥቁሮች ከማንነታቸው ተላቀው፣ ስማቸው ተፍቆ፣ እንደ ቁስ ተቆጥረው በነጮች እርሻ ውስጥ በባርነት አለንጋ ይገረፉ ነበር። ጥቁር መሆን የውርደት፣ የዝቅተኝነትና የሽንፈት ምልክት ተደርጎ የታተመበት ያ ዘመን፣ ለብዙዎች ተስፋ የሞተበት ድቅድቅ ጨለማ ነበር።

​ነገር ግን፣ በዚህ ሁሉ ስቃይና እንባ መካከል፣ ከአፍሪካ ቀንድ አንዲት ብርሃን ብልጭ አለች። ያቺ ብርሃን ከኢትዮጵያ ምድር የተገኘች "አድዋ" ትባላለች።

​በዛ ዘመን የኢትዮጵያ ተራሮች በጭስና በደም ተሸፍነዋል። ንጉሠ ነገሥቱ ዳግማዊ ምኒልክና እቴጌ ጣይቱ፣ ገበሬውን፣ ቄሱን፣ ሸማኔውንና አርሶ አደሩን አስተባብረው ዘመናዊ መሣሪያ የታጠቀውን የጣሊያን ጦር ፊት ለፊት ተጋጠሙት። ያ ዛረም ድረስ ምናከብረው የድል ቀን ለነጭ ገዢዎች የውርደት፣ ለጥቁር ሕዝቦች ግን የትንሳኤ ቀን ነበር።

​ድሉ ሲበሰር "ጥቁር ሰው ነጭን ማሸነፍ ይችላል!" የሚለው ዜና በባርነት ቀንበር ስር ላሉት ወንድሞቻችን የነፃነት ወንጌል ሆነ። ይህ ዜና ጃማይካ ደሴት ላይ ወደሚገኘውና ገና በልጅነቱ የዘሩን መገፋት እያየ ወደሚያለቅሰው ወጣቱ ማርከስ ጋርቬይ ደረሰ።

​ማርከስ ጋርቬይ በጃማይካ ሲያድግ፣ በዙሪያው የሚያየው ድህነትን፣ ንቀትንና የጥቁርነትን ስብራት ነበር። ነገር ግን ስለ አድዋ ሲሰማ፣ በውስጡ አንድ ታላቅ እሳት ነደደ። ጋርቬይ ኢትዮጵያን በአካል አይቷት አያውቅም፤ ነገር ግን በልቡ ውስጥ ኢትዮጵያ "የእናት ምድር" ምልክት፣ የክብር ተራራ፣ የነፃነት መቅደስ ሆና ተቀረጸች።

​ጋርቬይ "Universal Negro Improvement Association" (UNIA) የተባለውን ማኅበር ሲመሠርት፣ በቢሊዮን ለሚቆጠሩ ጥቁር ሕዝቦች የነገራቸው አንድ ትልቅ እውነት ነበር፦ "እናንተ አገር የሌላችሁ ተቅበዝባዦች አይደላችሁም፤ እናንተ አድዋ ላይ ታሪክ የሠሩ የጀግኖች ወንድሞች ናችሁ!" እያለ ይጮኽ ነበር። ጋርቬይ ለጥቁር ሕዝቦች የሰጠው ሰንደቅ ዓላማ መነሻው የአድዋው የኢትዮጵያ ባንዲራ ነበር። ቀዩ—ስለ ነፃነት የፈሰሰውን ደም፣ ጥቁሩ—የሕዝቡን ክብር፣ አረንጓዴው ደግሞ የአፍሪካን ተስፋ ይወክሉ ነበር።

​የጋርቬይ ሕይወት በመከራ የተሞላ ነበር። በዘረኞች እየታደነ፣ በገዛ ወንድሞቹ እየተከዳ፣ በእስር ቤት እየማቀቀ እንኳን፣ ከአንደበቱ የማይጠፋው ቃል "ኢትዮጵያ" የሚል ነበር። ጋርቬይ በሃርለም ጎዳናዎች ላይ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ጥቁሮችን ሰብስቦ ሲያሰልፍ "ወደ አፍሪካ ተመልከቱ" እያለ ሲቀሰቅስ፣ በዓይነ ሕሊናው የሚታየው የምኒልክ ጎራዴና የኢትዮጵያ ሉዓላዊነት ነበር።

​ጋርቬይ እንዲህ ይል ነበር፦ "እግዚአብሔር ሆይ! ጥቁር ሕዝቦች በራሳቸው መርከብ ወደ እናት ምድራቸው ተመልሰው፣ እንደ አድዋ ጀግኖች በነፃነት የሚኖሩበትን ቀን አሳየኝ!" እርሱ ለዚህ ራዕይ ሲል ክብሩን፣ ገንዘቡንና ጤናውን መሥዋዕት አደረገ።

በወቅቱ የነበሩት ኃያላን መንግሥታት "ይህ ሰው ጥቁሮችን እያነቃ ነው" ብለው ፈሩት። በሐሰት ወንጀል ከሰሱት፣ አሰሩት፣ መጨረሻም ከአሜሪካ አባረሩት።

​ ​በ1930 ዓ.ም ንጉሥ ተፈሪ መኮንን "ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ" ተብለው ሲነግሡ፣ በካሪቢያን የሚገኙ የጋርቬይ ተከታዮች በደስታ አበዱ ። ጋርቬይ ቀድሞ "ጥቁር ንጉሥ በአፍሪካ ይነግሣል" ብሎ ተንብዮ ስለነበር፣ የንጉሡ መክሊት ለጋርቬይ ተከታዮች መሲሐዊ ትርጉም ነበረው።

​ነገር ግን ታሪኩ እዚህ ላይ አሳዛኝ መልክ ይይዛል። በ1935 ዓ.ም ፋሺስት ጣሊያን በአድዋ የተሸነፈችውን ሽንፈት ለመበቀል በድጋሚ ኢትዮጵያን ስትወርር፣ ጋርቬይ በለንደን ስደት ላይ ነበር። ኢትዮጵያ ስትወረርና ንጉሡ ወደ ስደት ሲመጡ፣ ጋርቬይ ልቡ በሐዘን ተሰበረ። "እንዴት አባቶቻችን አድዋ ላይ ያስከበሩትን ክብር እናጣለን?" ብሎ ምርር ብሎ አለቀሰ። በወቅቱ ከንጉሡ ጋር የነበረው መጠነኛ የሐሳብ ልዩነትና የኢትዮጵያ በጣሊያን እጅ መውደቅ፣ ጋርቬይን ለከፍተኛ ሕመም ዳረገው።

​ማርከስ ጋርቬይ በ1940 ዓ.ም በለንደን በብቸኝነት ሲያልፍ፣ የመጨረሻ ቃላቱ ስለ ጥቁር ሕዝብ አንድነትና ስለ አፍሪካ ነፃነት ነበሩ። የሚገርመውና ልብን የሚሰብረው፣ ጋርቬይ ሕይወቱን ሙሉ የዘመረላት፣ ስለ ክብሯ የታገለላትና መላ ሕይወቱን የሰጠላትን ኢትዮጵያን አንድም ቀን በአካል ሳይረግጣት መሞቱ ነው።

​እርሱ ለጥቁር ሕዝቦች "ሥር" የሰጠ፣ ከአድዋ ተራሮች የተነሳውን የነፃነት እሳት ወደ ዓለም ያሰራጨ ታላቅ ነፍስ ነበር። እርሱ ሲሞት የነበረው ብቸኝነትና ድህነት፣ ለጥቁር ሕዝብ የከፈለው መሥዋዕትነት ትልቅነት ማረጋገጫ ነው።

​ዛሬ የአፍሪካ ህብረት አዲስ አበባ ላይ ሲቆም፣ አድዋ የፓን አፍሪካኒዝም ማዕከል ስትሆን፣ የማርከስ ጋርቬይ መንፈስ በዚያ ደጃፍ ላይ ቆሞ ይታያል።

ጋርቬይ በአካል ባይመጣም፣ በሚሊዮን የሚቆጠሩ የጃማይካና የዲያስፖራ ጥቁሮች ዛሬም "ኢትዮጵያ" እያሉ ይዘምራሉ።

​አድዋ ላይ የፈሰሰው የኢትዮጵያውያን ደም፣ በካሪቢያንና በአሜሪካ ለነበሩት ባሮች የነፍስ ምግብ ሆኗቸዋል። ጋርቬይ ደግሞ ያንን ደም ወደ ርዕዮተ ዓለም ቀይሮ፣ ጥቁር ሕዝብ በራሱ እንዲተማመን አድርጓል።

​አድዋ እና ጋርቬይ የአንድ ታሪክ ሁለት አካላት ናቸው። አድዋ—ሥጋዊና ሞራላዊ ነፃነትን ሲሰጠን፣ ጋርቬይ—መንፈሳዊና አእምሯዊ ነፃነትን ሰጥቶናል። ዛሬም ድረስ በጃማይካ የሚገኙ ራስተፋሪያውያን ወደ ኢትዮጵያ (ሻሸመኔ) ሲመጡ፣ "ወደ አገራችን ተመለስን" የሚሉት ለዚህ ነው።

​የአድዋ ድል ባይኖር ጋርቬይ የሚሰብከው ክብር አይኖርም ነበር። ጋርቬይ ባይኖር ደግሞ የአድዋ ድል በኢትዮጵያ ተራሮች መካከል ብቻ ተቀብሮ በቀረ ነበር።

ዛሬ ላይ ሆነን ስናስበው፣ ጋርቬይ ማለት በአድዋ የተነሳው የነፃነት ብርሃን በዓለም ዙሪያ እንዲበራ ያደረገ ታላቅ የመብራት ማማ ነው።

​ይህ ታሪክ የሚያስተምረን አንድ ትልቅ እውነት አለ፦ የአፍሪካውያንና የጥቁር ሕዝቦች ትስስር በውቅያኖስ የማይገደብ፣ በባርነት የማይበጠስና በጊዜ የማይደበዝዝ የደም ትስስር መሆኑን ነው። ጋርቬይ በለንደን ስደት ላይ ሆኖ የፈሰሰው እንባ፣ ዛሬ በአፍሪካ አንድነት ውስጥ ፍሬ አፍርቷል።

​እኛ የአድዋ ልጆች፣ የማርከስ ጋርቬይ ራዕይ አደራዎች ነን። እርሱ ያላያትን ኢትዮጵያ እኛ ይዘናታል፤ እርሱ የናፈቃትን ነፃነት እኛ እየኖርንባት ነው። ይህን ታላቅ ክብር መጠበቅና ለቀጣዩ ትውልድ ማስተላለፍ የታሪክ ግዴታችን ነው።

​ክብር ለአድዋ ጀግኖች! ዝንተዓለም መታሰቢያነት ለአፍሪካ ኩራት ለማርከስ ጋርቬይ!
5 months ago

No replys yet!

Be the first to share what you think — your comment will appear here.