Logo
Getu Temesgen
'ሌላ እውነት የለኝም' በቨርጂኒያ ተመረቀ
#ethiopia | የአርቲስት ሜሮን ጌትነት ‘ሌላ እውነት የለኝም’ የግጥም መድበል እጅግ ባማረና የሚገባውን ክብር ባገኘ መልኩ እዚህ ቨርጂኒያ ውስጥ ተመርቋል። ግጥሞቿ በሞያ አጋሮቿ ተነበዋል፣ ሙያዊ ዳሰሳም ተደርጎባቸዋል። የሜሪ ግጥሞች በስሜት ማዕበል ሲያወዛውዙን፣ ሲያስደምሙን፣ ሲያስለቅሱን፣ ሲያስቁን፣ ሲመስጡን አመሹ። ነገሮችን የምታይበት መነጽር አዲስ፣ የምትገልጽበት መንገድ ደግሞ የነፍሳችንን አስኳል የሚነካ ሃይል ያለው አለው።

ላይ ላዩን የሚጋልቡ ሳይሆን ሁለንተንችንን የሚነዝሩ፣ ውስጥ ድረስ ዘልቀው የሚሰሙና ጥያቄ የሚያጭሩ ሃሳቦች ግዘፍ ነስተው፣ ነፍስ ዘርተው ግጥሞቿ ውስጥ ይተነፍሳሉ፤ ይናገራሉ። ጥልቅ፣ መሰረታዊ፣ እናም ደግሞ ልዩ ትርጉም ያላቸው ሃሳብ፣ ምልከታና ሙግቶች ‘ሌላ እውነት የለኝም’ ውስጥ ሞልተዋል። ያልታዩ፣ ያልተስተዋሉና ያልታሰቡ የህይወት አቅጣጫወች በሜሪ ግጥሞች ውስጥ ፍንትው ብለው ተገለጠዋል። እናም ሁላችንም ወደ ውስጥ እንድናይ፣ ከራሳችን ጋ እንወዛገብ ዘንድ በር ይከፍታሉ። ይህን ሁሉ የሚያደርጉት ደግሞ በማያልቀው የሜሪ የቋንቋ ውበት፣ የአጻጻፍ ብቃት እና የፈጠራ ክህሎት ታጅበው፣ ጉዞው በማያልቅበት የምናቧ ጥልቀትና ስፋት ተቃኝተው ነው።

ሜሮን እንደ ሁልጊዜው ሁለገብ ከያኒነቷን ግጥሞቿን እየተወነች አሳየችን።ግጥም መጻፍ ብቻ ሳይሆን ማንበብም ጥርት ያለ ጥበብ መሆኑን አስመሰከረች። ግጥምና ጃዝ ዳግም ተጣመሩ። መድረኩ በትወና፣ በሙዚቃ እና በግጥም ደምቆ አመሸ። ግጥሞቿን አምጣ ወልዳ፣ አሳድጋ፣ አሳትማ፣ አስመርቃ ለወግ ለማዕረግ አበቃች። በምሽቱ ስራውቿን በማቅረብ፣ የራሳቸውን የኪነጥበብ ውጤቶችን በማቋደስ፣ የመጽሐፉን ዳሰሳ በማድረግ ለዝግጅቱ ግብዓት የሆኑት የሞያ አጋሮቿ የድግሱ ድምቀቶች ነበሩ። ለታይታና ደረስ ብሎ ለመመልስ ሳይሆን፣ ሙሉ ዝግጅቱን በሙሉ ልብ ለመቋደስ የታደመው የDMV ነዋሪም ለሜሪና ለስራወቿ አፍቃሪና አክባሪ መሆኑን በተግባር አሳይቶ ምሽቱን ምሉዕ አድርጎታል። ለዝግጅቱ መሳካት ሽር ጉድ ሲሉ የነበሩ አስተባባሪወችና ሁል ጊዜም እንዲህ ያሉ ዝግጅቶችን በመደገፍ የሚታወቁ አጋር ድርጅቶች ከሜሮን ጎን በመቆም የማህበራዊ ሃላፊነታቸውን ተወጥተዋል።

የሜሮን ስብዕና፣ ብቃት፣ ለሞያው ያላት መሰጠት እጅግ ይገርማል፣ ያስደምማል፣ ያስደስታል፣ ያኮራል። ሜሪ ሁሌ ጻፊ። እንኳን ደስ አለሽ።

Via Abebe Feleke
Photo Credit: Eagle Photography Nathnael Damtew

Meron Ghetnet Hiwot Tadesse followers #addisababa #ethiopia #dmv

5 months ago

No replys yet!

Be the first to share what you think — your comment will appear here.