Logo
FIDEL POST NEWS
ከሽመና መጋዝ ወደ ዓለም አቀፍ ዝና፡ሁላችንም የምንማርበት የሱዙኪ አስደናቂ ጉዞ

እስቲ በዕዕምሯቹ አንዲትን ደሀ ሴት አስቡ ።ያቺ ሴት ደግሞ ​በሃያኛው ክፍለ ዘመን መጀመሪያ በጃፓን በምትገኘው የሃማማትሱ የባህር ዳርቻ መንደር ውስጥ የነበረች ብላቹ አስቡ ።ያቺ እናት በእጅ በሚሰራ የሽመና መሣሪያ ጥጥ ስታደራጅ ቀኑ ይጨልምባታል። ልጇ የሚቺዮ ሱዙኪ የእናቱን መከራና የቆሰሉ እጆቿን እያየ ልቡ በሐዘን ይነካል።

ይህን የልጅነት ፍቅርና ርኅራኄ ነው እንግዲህ ዛሬ የምናውቀው የሱዙኪ ኩባንያ መሠረት የሆነው። የሚቺዮ የመጀመሪያው ህልም እናቱን ከድካም የሚያሳርፍ መሣሪያ መፍጠር እንጂ መኪና ማምረት አልነበረም፤ ይህ በንጹህ ልብ የተጀመረ ጥረት ግን የቴክኖሎጂ አብዮት ለመፍጠር በቂ ነበር።
​ሚቺዮ በፈረንጆቹ 1909 ዓ.ም በ22 ዓመቱ የራሱን "ሱዙኪ የሽመና ፋብሪካ" ሲመሰርት ጃፓን ከእርሻ ወደ ኢንዱስትሪ የምትሸጋገርበት ወቅት ነበር።

እርሱ የሠራቸው የሽመና መሣሪያዎች ከሌሎቹ በበለጠ ፍጥነትና ጥራት ስለነበራቸው በሽመናው ኢንዱስትሪ ውስጥ ትልቅ ዝናን አተረፉ፤ ስራውም እየሰፋ በመሄዱ በ1920ዎቹ ማሽኖቹ ወደ ውጭ ሀገራት መላክ ተጀመረ። የዚህ ሰው ስኬት ሚስጥር ግን ትርፍ ማግኘት ብቻ ሳይሆን የሰዎችን የዕለት ተዕለት ችግር መረዳትና መፍትሄ መስጠት መሆኑ ለቀጣዩ ትልቅ ለውጥ በር ከፋች ሆነ።

​ሁለተኛው የዓለም ጦርነት ሲያበቃ የጃፓን ኢኮኖሚና የጨርቃጨርቅ ገበያ ክፉኛ ተመታ፤ በዚህ አስቸጋሪ ወቅት ግለኛ አስተሳሰብ ያለው ሰው አልነበረምና ሚቺዮ ፋብሪካውን ለመዝጋት አልፈለገም ይልቁንም ህዝቡ ምን ይፈልጋል? የሚለውን አሰበ።

ጦርነቱ ያደቀቃት ጃፓን ውስጥ ሰዎች ለመንቀሳቀስ ብስክሌት ብቻ ነበር ያላቸው፤ እናም ሚቺዮ ለተራው ህዝብ ተመጣጣኝና ጉልበት የማይጠይቅ የትራንስፖርት አማራጭ ለማቅረብ ወሰነ። ይህ ውሳኔ የኩባንያውን አቅጣጫ ከሽመና ወደ ሞተር ዘርፍ የቀየረ የታሪክ ምዕራፍ ሆነ።

​በፈረንጆቹ 1952 "Power Free" የተሰኘችውን የመጀመሪያዋን 36cc አነስተኛ ሞተር ለገበያ አቀረበ፤ ይህች ሞተር በብስክሌት ላይ የምትገጠም ሆና በፔዳል ወይም በሞተር እንድትሰራ ተደርጋ የተነደፈች ብልህ ፈጠራ ነበረች። ይህ ስኬት ኩባንያው በ1954 "Diamond Free" የተባለችውን ጠንካራ ሞተር እንዲያመርትና ስሙን ወደ "ሱዙኪ ሞተር ኩባንያ" እንዲቀይር አደረገው፤ የሚቺዮ ህልም አሁን ከእጅ ስራ ወጥቶ በመንገዶች ላይ መፍሰስ ጀመረ።

​የሱዙኪ ትልቁ ድፍረት የታየው በ1955 "Suzulight" የተባለችውን የመጀመሪያዋን አነስተኛ መኪና ሲያመርት ነው፤ መኪናዋ በወቅቱ በአውሮፓ እንኳን ብርቅ የነበሩ እንደ ፊት ለፊት ጎታችያሉ ቴክኖሎጂዎችን አካታ ነበር።

ይህች መኪና ለጃፓን ህዝብ የተስፋ ምልክት ሆና አገለገለች፤ ሱዙኪም በዓለም ዙሪያ "አነስተኛና ቀልጣፋ" መኪኖችን በማምረት ረገድ ተወዳዳሪ የሌለው መሆኑን ለመጀመሪያ ጊዜ አስመሰከረ።

​እያደገ የመጣው ኩባንያ በ1960ዎቹ እና 70ዎቹ ውስጥ ወደ ሞተር ሳይክሎች እና አነስተኛ የጭነት ተሽከርካሪዎች ዘርፍ ተስፋፋ፤ የሱዙኪ ሞተር ሳይክሎች በውድድር መድረኮች ላይ ድልን መቀዳጀት ሲጀምሩ፣ እንደ "Alto" ያሉ መኪኖች ደግሞ የቤት እመቤቶችና ተራ ሰራተኞች ተመራጭ ሆኑ። የኩባንያው ፍልስፍና "ቀላል፣ ብልህ እና ለሰው ልጅ ቅርብ" በሚሉ እሴቶች ላይ በመገንባቱ በዓለም አቀፍ ደረጃ ተቀባይነቱ በከፍተኛ ፍጥነት ጨመረ።

​ሱዙኪ በዓለም አቀፍ ገበያ ውስጥ ትልቅ ስር የሰደደው በ1982 ዓ.ም ከህንድ "Maruti Udyog" ጋር ባደረገው አጋርነት ነው፤ ይህ ጥምረት የህንድን የመኪና ገበያ ከመቀየር ባለፈ በሚሊዮኖች ለሚቆጠሩ ሰዎች የመኪና ባለቤት የመሆን ህልምን እውን አደረገ። በፓኪስታን እና በሌሎች ታዳጊ ሀገራትም ሱዙኪ የታማኝነትና የኢኮኖሚ ምልክት በመሆን በየቤቱ ስሙ የሚጠራ ተወዳጅ የምርት ስም መሆን ቻለ።

​በ1990ዎቹ ኩባንያው ስሙን ወደ "ሱዙኪ ሞተር ኮርፖሬሽን" በመቀየር ዓለም አቀፋዊነቱን አጠናከረ፤ እንደ "Swift"፣ "Jimny" እና "Vitara" ያሉ ዝነኛ ሞዴሎችን በማፍራት የዘመኑን ወጣትና ቤተሰብ ፍላጎት ማርካት ቻለ።

እነዚህ መኪኖች በጠንካራነታቸውና በነዳጅ ቆጣቢነታቸው የታወቁ ሲሆኑ፣ ሱዙኪ በአነስተኛ መኪኖች ዘርፍ ያለውን የበላይነት ለዓለም በድጋሚ ያሳየባቸው ውጤቶች ነበሩ።
​የኩባንያው መሪ መፈክር "By Your Side" (ከጎንዎ ነን) የሚል ሲሆን፣ ይህ ዝም ብሎ የንግድ ማስታወቂያ ሳይሆን የቆየው የሚቺዮ ሱዙኪ መንፈስ መገለጫ ነው፤ ይህም ማለት የደንበኞችን የዕለት ተዕለት ኑሮ መረዳትና ለኑሯቸው የሚመጥን መፍትሄ ማቅረብ ማለት ነው።

ዛሬ ሱዙኪ በከተማ መኪኖች፣ በሞተር ሳይክሎች ብቻ ሳይሆን በባህር ላይ ሞተሮችም ጭምር በዓለም ዙሪያ ካሉ ማህበረሰቦች ጋር በቅርበት የተቆራኘ ነው።

​የሚቺዮ ሱዙኪ ታላቅነት ያለው ከመሬት ተነስቶ ቢሊዮን ዶላር የሚያንቀሳቅስ ኩባንያ በመገንባቱ ላይ ብቻ አይደለም፤ ይልቁንም ለእናቱ ካለው ፍቅር ተነስቶ ለሰው ልጅ ሁሉ የሚጠቅም ስራ መስራቱ ላይ ነው። የእሱ ታሪክ እንደሚያስተምረን ትልቅ ለውጥ የሚመጣው ከትልቅ ካፒታል ሳይሆን የሰዎችን ችግር ለመቅረፍ ካለ ቅን ፍላጎትና ያላሰለሰ ጥረት ነው፤ ይህም ዛሬ ለደረሰበት ዓለም አቀፍ አቅኚነት ዋነኛው ነዳጅ ነበር።

​በአሁኑ ሰዓት ሱዙኪ ወደ ኤሌክትሪክ መኪኖችና ወደ ተለያዩ ዘመናዊ ቴክኖሎጂዎች እየተሸጋገረ ቢሆንም፣ አሁንም መሠረታዊ ማንነቱን ግን አልለቀቀም። የአካባቢ ጥበቃን ያገናዘቡ እና አነስተኛ የካርቦን ልቀት ያላቸውን ተሽከርካሪዎች በማምረት የወደፊቱን የትራንስፖርት ዓለም እየመራ ይገኛል፤ ይህ ደግሞ የሚቺዮን የፈጠራ መንፈስ ከአዲሱ ዘመን ጋር የማስማማት ጥበብ ውጤት ነው።

​የሱዙኪ ጉዞ ከጃፓን የባህር ዳርቻ መንደር ተነስቶ በዓለም አውራ ጎዳናዎች ላይ የነገሰ ታሪክ ነው፤ ይህ ታሪክ ትጋት፣ ርኅራኄና ጽናት ካለ የማይታለፍ መሰናክል እንደሌለ ያረጋግጣል። የዚያ ታናሽ የገበሬ ልጅ ህልም ዛሬም በቢሊዮኖች ልብ ውስጥና በየመንገዱ በሚሽከረከሩት የሱዙኪ መኪኖች ውስጥ ህያው ሆኖ ይቀጥላል።

ሱዙኪ ከቴክኖሎጂ በላይ የሰው ልጅ የጽናት ውጤት ነው።
3 months ago

No replys yet!

Be the first to share what you think — your comment will appear here.