Logo
FIDEL POST NEWS
በሂርና ከተማ በጅብ ላይ ጉዳት ያደረሰው ግለሰብ  የህክምና ወጪውን እንዲሸፍን ተደረገ

በምስራቅ ሀረርጌ ዞን ሂርና ከተማ አስተዳደር  ሀዬታ ቀበሌ ውስጥ ከጫካ የወጣ ጅብ በሰው ተመቶ ጉዳት የደረሰበት መሆኑን የፖሊስ ፅ/ቤት አስታውቋል።ጉዳት የደረሰበት  ጅብ የህክምና እርዳታ አግኝቶ ወደጫካው መመለሱ ተገልጿል።

የሂርና ከተማ መደሀዮታ ቀበሌ ማህበረሰብ አቀፍ ፖሊስ አገልግሎት ፅ/ቤት ሃላፊ  ኢንስፔክተር ሬድዋን ኢብራሂም ለብስራት ሬዲዮ እንደገለጹት ጅቡ ከጫካ የወጣው ጥር 30 ቀን 2018 ዓ.ም  ምሽት ሶስት ሰዓት  ላይ ሲሆን  አንድ ግለሰብ ቤት አካባቢ ሲጮህ የቤቱ ባለቤት ጅቡን ለማባረር በወረወረው ድንጋይ ጅቡ በሁለት እግሮቹ ላይ ጉዳት እንደደረሰበት ተገልጿል ።

ጅቡ ጉዳት ሲደርስበት በአካባቢው ፖሊስ እና  ባህላዊ ፍርድቤት ግቢ ገብቶ ጥቅልል ብሎ በመተኛት የደረሰበትን ጉዳት በጩኸት ሲገልጽ እንደነበረ ተጠቁሟል ።የጅቡን ጩኸት የተመለከቱ የፖሊስ አባላትም ግቢያቸው የገባውን የጫካ ጅብ ከማባረር እና ከመጉዳት ይልቅ ምግብ እና  ውሃ  በመስጠት አሳድረውታል። 

በነጋታውም ለጅቡ የሚያስፈልገውን በመስጠት ጉዳቱን እንዲታከም የዱር እንስሳት ጥበቃ ባለሞያ እና ሀኪም አፈላልገው በማሳከም ለሶስት ቀናት ካሳከሙት በኋላ የካቲት 4 ቀን 2018 ዓ.ም ወደ መጣበት ጫካ በሰላም ሸኝተውታል።

ፖሊስ ከጫካ የወጣውን ጅብ ላይ ጉዳት ያደረሰውን ግለሰብ ተከታትሎ በመያዝ የህክምናውን ወጭ እንዲሸፍን ያደረጉ ሲሆን የሶስት ቀን የምግብ ወጭውንም ፖሊሶች ስጋ በመግዛት አገግሞ ወደ ጫካው እንዲመለስ ማድረጋቸውን  ኢንስፔክተር ሬድዋን ኢብራሄም ጨምረው ለብስራት ሬዲዮ ተናግረዋል ።

በኤደን ሽመልስ
#ዳጉ_ጆርናል
6 months ago

No replys yet!

Be the first to share what you think — your comment will appear here.