Logo
YenetaTube
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ኢትዮጵያ ወደ ቀይ ባሕር መውጫ መንገድ ለመፈለግ የምታደርገውን ጥረት ቱርክ እንድትደግፍ ጠየቁ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ጥያቄውን ያቀረቡት የቱርኩ ፕሬዚዳንት ራሲፕ ታይፕ ኤርዶኻን ለአንድ ቀን ጉብኝት ትናንት ማክሰኞ ወደ አዲስ አበባ በተጓዙበት ወቅት ነው።
ፕሬዝዳንት ኤርዶኻን በአዲስ አበባ በነበራቸው ቆይታ በዚሁ ጉዳይ ላይ ከጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ ጋር መምከራቸው ተገልጿል። ፕሬዝደንት ኤርዶኻን በበኩላቸው ባደረጉት ንግግር ሀገራቸው ኢትዮጵያ በምትገኝበት ክፍለ ዓለም «አዲስ ግጭቶች እና አዲስ ህመም እንዲጨምር እንደማትፈልግ» ገልጸዋል። ኤርዶኻን «የአፍሪካ ቀንድ የውጭ ኃይሎች መፋለሚያ» መሆን እንደሌለበትም በጋራ መግለጫ ንግግራቸው አሳስበዋል። የቱርኩ ፕሬዝደን የኢትዮጵያ ጉብኝታቸው «ለአካባቢው ሰላምና መረጋጋት አስተዋፅኦ እንደሚያበረክት» ተናግረዋል።

ሁለቱ መሪዎች በቆይታቸው በአፍሪቃው ቀንድ ሽብርተኝነትን ለመዋጋት የተስማሙ ሲሆን በኃይል ዘርፍም ለመተባበር የመግባቢያ ሰነድ መፈራረማቸው ተገልጿል። ኢትዮጵያ የባሕር በር ለማግኘት በሚል ከሶማሊላንድ ጋር የመግባቢያ ሰነድ መፈራረሟን ተከትሎ ከሶማሊያ ጋር የተፈጠረውን ውጥረት ቱርክ በጎርጎሪዮሳዊው 2024 ታኅሣስ ወር አሸማግላ ማርገቧ ይታወሳል። በሶማሊያ እና ኢትዮጵያ መካከል የተደረሰው ስምምነትም አዲስ አበባ አስተማማኝ የባሕር በርን በሶማሊያ በኩል የመጠቀምን እድል የሚያመቻች እንደሚሆን በወቅቱ ተገልጿል። በዚህ ጉዳይ ላይ የሚደረገው ውይይት እንደቀጠለ ነው።
ቱርክ በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያ ውስጥ በተለይ በአምራች እና ግንባታ ዘርፎች ላይ በመሰማራት ቀዳሚ ከሆኑ አራት የውጭ ሃገራት ተርታ ትሰለፋለች። ከኢኮኖሚ ትብብሩ ባለፈ አንካራ በአፍሪካ ቀንድ ያላትን ዲፕሎማሲያዊ ሚና በማስፋፋትም ስሟ ይነሳል።

ቱርክ በኢትዮጵያ እና በሶማሊያ መካከል ተፈጥሮ የነበረውን እሰጥ አገባ ከማለዘብ ባሻገር በአባይ ወንዝ እና የባሕር በርን በተመለከቱ ቁልፍ ጉዳዮች ለአዲስ አበባ ድጋፏን ስትቸር ቆይታለች።

DW Amharic

4 months ago

No replys yet!

Be the first to share what you think — your comment will appear here.