Logo
YenetaTube
በጋሞ ዞን በተከሰተ ግጭት 15 ሰዎች ተገደሉ

በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ጋሞ ዞን አርባ ምንጭ ዙሪያ ወረዳ በተቀሰቀሰ ግጭት 15 ሰዎች መገደላቸውን ነዋሪዎችና አካባቢውን የወከሉ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል ገለጹ፡፡ ነዋሪዎቹና የምክር ቤት አባሉ እንዳሉት ሰዎቹ የተገደሉት ከትናንት በስቲያ እሑድ እና ትናንት ሰኞ በወረዳው ዛይሴ ወዘቃ እና ዛይሴ ደንብሌ በተባሉ ቀበሌያት በተቀሰቀሰ ግጭት ነው ፡፡
አንድ ለደኅንነታቸው ሲሉ ስማቸው እንዳይጠቀስ የጠየቁ የዛይሴ ደንብሌ ቀበሌ ነዋሪ ግጭቱ ከትናንት በስቲያ አሑድ 10 ሰዓት ላይ ተከስቶ እስከ ትናንት ሰኞ ቀትር ድረስ መቀጠሉን ለዶቼ ቬለ ተናግረዋል፡፡ በፖሊስ አጀብ ተሽከርካሪ ተጭነው በቀበሌው በማለፍ ላይ የነበሩ የጋሞ ዞን የፀጥታ አባላት «ድንጋይ ተወርውሮብናል» በሚል የወረወረውን ሰው ለመያዝ ወደ መንደሮች መግባታቸውን የጠቀሱት እኝሁ የቀበሌው ነዋሪ «የፀጥታ አባላቱ በየቤቱ መግባት መጀመራቸውን ተከትሎ ነው ግጭቱ የተነሳው። የፀጥታ አባላቱ በመንደሩ ላይ በከፈቱት ተኩስ ወላጅ አባታችንን ጨምሮ የአምስት ሰዎች ሕይወት አልፏል» ብለዋል፡፡

የዛይሴ የምርጫ ክልልን በመወከል የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል አቶ አብረሃም አሞሼ የፀጥታ አባላቱ በቀበሌያቱ ከፈቱት ባሉት ተኩስ በዛይሴ ወዘቃ ቀበሌ ሰባት እና በዛይሴ ደንብሌ ቀበሌ ደግሞ ስምንት ሰዎች መገደላቸውን ተናግረዋል።
ዶይቸ ቬለ ተከስቷል የተባለውን ግጭት አስመልክቶ ምላሽ ለማግኘት የጋሞ ዞን አስተዳደርንም ሆነ የዞኑን ፖሊስ መምሪያ ኃላፊዎች ለማነጋገር ያደረገው ጥረት አልተሳካም፡፡ ይሁን እንጂ ከቀናት በፊት በተካሄደው የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል 5ተኛ ዓመት 6ተኛ መደበኛ ጉባዔ ላይ የሥራ ሪፖርት ያቀረቡት የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ጥላሁን ከበደ፤ የክልሉን የፀጥታ ጉዳይ በሪፖርታቸው ጠቅሰዋል። ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን በስም ባልጠቀሷቸው ነገር ግን በአንዳንድ የክልሉ አካባቢዎች ባሏቸው ሥፍራዎች ላይ ከአደረጃጀት ጥያቄ፣ ከማንነት፣ ከሃይማኖት ጽንፈኛነት እና ከመሬት ወረራ ጋር በተያያዘ ግጭቶች መከሰታቸውን ተናግረዋል፡፡

በግጭቶቹ በሰውና በንብረት ላይ ጉዳት መድረሱን የጠቀሱት ርዕሰ መስተዳድሩ «የተወሰኑ ግጭቶች በዕርቅ እንዲፈቱ ተደርጓል። በተፈጠረው ግጭት ምክንያት ተዘርፈው የነበሩ ንብረቶችም ለባለቤቶቹ የመመለስ ሥራዎች የተከናወኑ ሲሆን ግጭት ጨማቂዎችም ለሕግ እንዲቀርቡ ተደርጓል» ብለዋል።

DW Amharic

4 months ago

No replys yet!

Be the first to share what you think — your comment will appear here.