Logo
YenetaTube
በርበሬን ከቀለም ጋር በመቀላቀል ሲያሰራጩ የነበሩ ተያዘ

በሀላባ ዞን ቁሊቶ ከተማ አስተዳደር ክትትልን መሰረት በማድረግ በተሰራ የተቀናጀ ኦፕሬሽን በሁለት ወፍጮ ቤቶች ላይ ለህዝብ ጤና አደገኛ የሆነ የበርበሬ ምርት በቁጥጥር ስር ውሏል። ከብሄራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት እንዲሁም የጉምሩክ ኮሚሽን ሀዋሳ ቅርንጫፍ የክትትል ቡድን በደረሰዉ መረጃ መነሻ በማድረግ ወፍጮ ቤቶቹ በህገ ወጥ መልኩ አዘጋጅተዉ ለገበያ ሊያቀርቡ የነበሩ የበርበሬ ምርት ተይዟል።

በዚህም 68 ኩንታል ከባዕድ ነገር ጋር ተቀቅሎ የተፈጨ በርበሬ፣ የታሸገ 1ሺህ 300 ፍሬ ባለ 500 ግራም እና 250 ግራም ከባዕድ ነገር ጋር ተቀላቅሎ የታሸገ የበርበሬ ምርት፣ 16 ኩንታል ለመፍጨት የተዘጋጀ ከደረጃ በታች የሆነ (ፎሼ) በርበሬ በቁጥጥር ስር መዋሉን የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ፖሊስ የሚዲያ ክፍል ኃላፊ ም/ኮማንደር ታጁ ነጋሽ ለብስራት ሬዲዮ ተናግረዋል።የበርበሬ ምርቱ ምንነታቸዉ ባልታወቁና የበርበሬዉን ቀለም በሚቀይሩ ኬሚካሎች ጋር የተደባለቀ ሲሆን ለዚሁ ስራ እንዲዉል የተዘጋጀ 200 ግራም ምንነቱ ያልታወቀ እና ለምግብ ማቅለሚያነት የሚያገለግል ኬሚካል እና አገልግሎት ላይ ዉሎ ያለቀ ፌስታል በአግዝቢት ተይዟል።

ይህን የመሰሉ ተግባራት የህብረተሰቡን ጤና አደጋ ላይ የሚጥሉ በመሆናቸዉ ድርጊቱ ሲፈጸምባቸዉ የነበሩ ሁለት የወፍጮ ቤቶች ሙሉ በሙሉ የታሸጉ ሲሆን ይህንን ህገወጥ ተግባር ሲያካሄዱ የነበሩ ተጠርጣሪ ግለሰቦችም በህግ ቁጥጥር ስር ዉለዉ ምርመራ እየተደረገባቸዉ ይገኛል።የተያዙት ምርቶች ናሙና ለብሄራዊ ላቦራቶሪ የተላከ ሲሆን ዉጤቱን መነሻ በማድረግ በቀጣይ ህጋዊ እና አስተዳደራዊ እርምጃዎች የሚወሰዱ ይሆናል::

የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ጤናና ጤና ነክ አገልግሎቶች እና ግብዓቶች ጥራት ቁጥጥር ባለስልጣን ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር በመቀናጀት የቁጥጥር ስራዉን አጠናክሮ እንደሚቀጥል በመግለጽ ህብረተሰቡ መሰል ህገወጥ ተግባራት ላይ በመሰማራት የህብረተሰቡን ጤና አደጋ ላይ ሊጥሉ የሚችሉ አጠራጣሪ ጉዳዮችን በሚመለከትበት ወቅት አቅራቢያቸዉ ለሚገኝ የጤና ተቆጣጣሪ አካል ጥቆማ እንደሰጡ ጥሪ ማቅረቡን ም/ኮማንደር ታጁ ነጋሽ ጨምረው ለብስራት ሬዲዮ ተናግረዋል።

Via_ዳጉ_ጆርናል

6 months ago

No replys yet!

Be the first to share what you think — your comment will appear here.