አበራ ለማ- "ኢትዮጵያ አቀፉ" ደራሲ
-----
አፈንዲ ሙተቂ
-----
እነሆ ዛሬ ደግሞ ስለአንጋፋው ደራሲና ጋዜጠኛ በአጭሩ ልንናገር ነው። ስለብዕር ገበሬው አበራ ለማ ልናወጋ ተሰናድተናል። ጋሽ Abera Lemma (አበራ ለማ) ማን ነው?
-----
ሰውዬው ብዙ ሰው ነው። የረጅም ልብ-ወለድ ደራሲ ነው። የአጭር ልብ ወለዶች ጸሐፊም ነው። የኖቬላ ቀማሪ ነው። ግሩም ሐያሲ እና የመጻሕፍት ገምጋሚ ነው። ምርጥ አርታኢ ነው። ገጣሚ ነው። የሙዚቃ ድርሰቶች ጸሐፊም ነው። ጋዜጠኛ ነው። የጉዞ ማስታወሻዎች አጠናቃሪ ነው። የደራሲያን ማህበር ዋና ጸሐፊ ሆኖ ብዙዎች ወደ ድርሰቱ ዓለም እንዲቀላቀሉ የረዳቸው ቀና ሰው ነው። ብዙ፣ ብዙ፣ ብዙ፣ መገለጫዎች ያሉት የብዕር አውራ ነው። በዚህ ዘመን በሕይወት ካሉት ዋና እና አንጋፋ ደራሲዎቻችንም አንዱ ነው።
-----
ደራሲ አበራ ለማ በእርግጥ ከዩኒቨርሲቲ ተመርቆ ስራ የጀመረው ጋዜጠኝነት ሙያ ነበር። ብዙ ሰዎችም ጋዜጠኝነቱን ሲያደንቁለት እሰማለሁ፣ አነባለሁ። በጋዜጠኝነቱ የተደረጉለትን ቃለ-መጠይቆችም አንብቤአለሁ። በኔ በኩል ግን "አበራ ለማ" የሚለው ስም በደራሲነቱ ይገዝፍብኛል። የዚህ ምክንያት በቅድሚያ እርሱን ያወቅኩት በደራሲነቱ ስለነበረ ነው።
ከደራሲ አበራ ለማ ጽሑፎች ጋር የተዋወቅኩት በ1970ዎቹ እና በ1980ዎቹ መጀመሪያ ላይ ይታተሙ በነበሩት "የካቲት"ን የመሳሰሉ መጽሔቶችና በአዲስ ዘመንና የዛሬዪቱ ኢትዮጵያ ጋዜጦች አማካኝነት ነበር። እንደማስታውሰው መጀመሪያ ያነበብኩለት "ሞገደኛው ነውጤ" የተሰኘውንና ዛሬም ድረስ ብዙዎች በትዝታ የሚያወሱለትን አጭር ቧልታዊ ልብ-ወለድ (Short satiric story) ነው።
ከጥቂት ዓመታት በኋላም "የማለዳ ስንቅ" የተሰኘ መጽሐፉን አነበብኩለት (የግጥምና የአጫጭር ልበ-ወለዶች መጽሐፍ ነው)። በኋላ ላይ (በ1985 ገደማ) የመጻሕፍት ወዳጅ የሆነው አብዛኛው ኢትዮጵያዊ ከሚያስታውሰው "መቆያ" የተሰኘ መጽሐፉ ጋር እኔም መቆያዬን አበጀሁ። ሁለቱም አሪፍ ኪታቦች ነበሩ።
ታዲያ እኔ በቅድሚያ ያነበብኩለት "የማለዳ ስንቅ" የተሰኘ መጽሐፉ ለጋሽ አበራ የመጀመሪያ ድርሰቱ ይመስለኝ ነበር። በ2006 በአካል ስንገናኝ ግን መጻሕፍቱ መታተም የጀመሩት በ1960ዎቹ ማብቂያ ገደማ እንደሆነ ነግሮኝ በተከታታይ ያሳተማቸውን መጻሕፍት አወጋኝ (ከነገረኝ የመጻሕፍቱ ርእሶች መካከል "ሽበት" የተሰኘውን አስታውሳለሁ)።
በዚህም አንድ ነገር ተገነዘብኩ። የኖርዌይ ዜጋ የሆነው Reidulf Molvaer (ሬዶልፍ ሞልቫየር) "Black Lions" በተሰኘው ተወዳጅ መጽሐፉ ውስጥ የአበራ ለማን የብዕር ውሎ ከሌሎች ደራሲዎቻችን ጋር በማቀናጀት የተረከበት ምክንያት በድርሰት አዝመራዎቻቸው በአማርኛ ስነ-ጽሑፍ ዕድገት ላይ የራሳቸውን ተጽዕኖ ማሳረፍ ከቻሉ አንጋፋዎቻችን አንዱ ስለነበረ መሆኑን ተረድቻለሁ።
አበራ ለማ በቅርብ ጊዜ ከከተባቸው መጻሕፍት መካከል "ቅንጣት"ን አንብቤአለሁ። "ጥሎ ማለፍ" የተሰኘውን መጽሐፍ ግን ለማንበብ ከገዛሁት በኋላ አንዱ ልጅ ወስዶብኝ በዚያው ጠፍቶአል። ወደፊት እናነበዋለን። አብሽር!!
-------
እዚህ ዘንድ "ከአበራ ለማ መጻሕፍት እና መጣጥፎች ምኑን ታዘብክለት?" ትሉኝ ይሆናል። ይህ ጥሩ ጥያቄ ነው።
አበራ ለማ ከሌሎች በርካታ ደራሲዎች የሚለየው "ኢትዮጵያ አቀፍ" በመሆኑ ነው። እንደርሱ በድርሰቶቻቸው ኢትዮጵያን በሙሉ ለማሳየትና ለመዳሰስ የሞከሩት ጥቂት ደራሲዎች ብቻ ናቸው።
አዎን! ከኢትዮጵያ ልብ-ወለዶች መካከል ከ85 % በላይ የሚሆኑት አዲስ አበባ ውስጥ ተጀምረው አዲስ አበባ ውስጥ ነው የሚያልቁት። ከነ እነርሱ መካከል የድሮዎቹ በደጃች ውቤ ሰፈር ካለው የወይዘሮ አሰገደች አላምረው ዳንስ ቤት ይጀምሩና፣ ሲኒማ አምፔር፣ ፒያሳ ቲ ሩም፣ ባንኮ ዲ ሮማ፣ እያሉ እዚያው ዙሪያ ይሽከረከራሉ። በዘመናችን ከሚታዩት ልብ-ወለድ ድርሰቶች መካከልም ብዙዎቹ ከቦሌ ጀምረው፣ ቴሌ መድሃኒአለም ወርደው፣ ሀያ ሁለት ማዞሪያ እና ሲ ኤም ሲ ደርሰው ያበቃሉ። መቼታቸው በጣም ጠባብ ነው።
ጋሽ አበራ እና ጥቂቶች ግን እንደዚህ ዓይነት ግንጥል አካሄድ አይጓዙም። አዲስ አበባን እና ሰዎቿን እያሳዩን ሌላውንም የኢትዮጵያ ክፍል ያዳርሳሉ። በዚህ መሃል በግሩም ቋንቋ እየተከሽኑ ለአንባቢያን የሚቀርቡት የባህል፣ የታሪክ፣ የቋንቋ፣ የኪነ-ህንጻ፣ የሙዚቃ፣ የስነ-ቃል፣ የማህበራዊ ህይወት፣ የመልክዐ ምድር፣ የስነ-ጥበብ (fine art) ሀብቶቻችን ተደራሲው ሳይለፋ ሀገሩን እና ሕዝቡን በትክክል እንዲያውቅ እና እንዲረዳ የሚያደርጉ የህይወት ፀጋዎች ናቸው።
በዚህም ምክንያት ነው አበራ ለማን "ኢትዮጵያ አቀፉ" ደራሲ ብዬ የጠራሁት (ምናልባት በethnograpy. ጥናት ላይ ስለተሰማራሁ የኔ taste ከሌላው ተለይቶ ይሆናል። ቢሆንም የጻፍኩት ነገር እውነት ነው)።
ደራሲው አበራ ለማ በአንድ ወቅት ስለድርሰቶቹ መቼት ሲናገር "እኔ የሰላሌ ልጅ ነኝ። በሁለት ታላላቅ ሕዝቦቻችን መካከል ነው ያደግኩት። በዚያ ላይ ሰላሌ ከታላላቅ አርበኞች እስከ ታላላቅ አርቲስቶች ያፈራ ምድር ነው። የመልክዓ ምድሩ ተፈጥሮና ልምላሜው ሌላ ነው። የኔም የድርሰት መኖ ከሰላሌ ይጀምርና ወደ ሌላው የኢትዮጵያ ክፍል ይዘልቃል" ብሎ ነበር (ቃል በቃል አልጠቀስኩትም። ሐሳቡ ግን እንደዚህ ነበር)። በእውነትም ጋሽ አበራን ስናውቀው እንደዚህ ነበር።
-------
ጋሽ አበራ ለማ ብዙ የሚነገር ቁም-ነገር ያለው የድርሰት አባታችን ነው። ፈጣሪ ዕድሜና ጤና ሰጥቶት ሌሎች የጽሑፍ በረከቶቹን እንድንቋደስ ያድርገን። አሚን!!
------
አፈንዲ ሙተቂ
ተማም! ሰላም!

5 months ago