Logo
Getu Temesgen
የደሃ ሃገር ወጣት I ShowSpeed ን አይኮርጅም !

(የኔ ምልከታ) #ethiopia | አይሾውስፒድ 'Contentless Content' ይዞ ጥድፊያና ሁካታ ወዳድ የዓለም ዜጎችን እያስከተለ ያለ ለጋ ወጣት ነው፡፡ ዓለም የጥድፊያ እና ሁካታ (speed and chaos) መድረክ ናትና ሁካታ ወዳድ ዜጎች ቢኖሯት አይገርምም፡፡ ስፒድም መቶ ቀርቶ ሁለት መቶ ሚሊዮን ተከታይ ቢኖረውም አይደንቅም፡፡ ፍላጎት ባለበት አቅርቦት አትራፊ ነው፡፡

ባልቲሞር ውስጥ በሚገኘው የጥንቱ የቅዱስ ጳውሎስ ቤተክርስቲያን በ1692 ዓ.ም ተጠቅልሎ የተገኘ ዴዜዴራታ የሚባል መመሪያ እንዲህ ይላል፡፡ "በዚህ ዓለም ጥድፊያና ሁካታ ሳትበገር በርጋታ ኑር"

ዴዜዴራታ ካዛሬ 300 ዓመት በፊት የዓለምን ‘የጥድፊያና ሁካታ’ መንደርነት መዝኖ ነው በዚህ ውስጥ ለመኖር እርጋታ በጣም አስፈላጊ መሆኑን የመከረው፡፡ ረጋ ያሉ ብቻ ጥድፊያውንና ይዞት የሚመጣውን ደራሽ በዘዴ ያልፉታል፡፡

ስፒድ [ኮንቴንት ከተባለ] ኮንቴንቱ 'ጥድፊያ እና ሁካታ' ብቻ ናቸው፡፡ 'በክዋኔም፣ በንግግርም “ጥድፊያ”ን በማሳየት ነው ብራንዱን የቀረጸው ፡፡ ያንን ደግሞ ከጩኸት (ሁካታ) ጋር አስተሳስሮታል፡፡ በዚያ ላይ ደግሞ ኢነርጂ (ጉልበት) ጨምሮበታል፡፡ እነዚህ ሶስቱ ሲቀናጁ የርሱን ኮንቴንት ፈጥረዋል፡፡

ስለዚህ መረጋጋት የስፒድ መለያ አይደለም፡፡ ይጮሃል እንጂ አያወራም፣ ይሮጣል እንጂ አይቆምም፡፡ ዘፈቀደ እንጂ የተሰተረ ነገር (setup) አይወድም፡፡ በተረጋጋ ሁኔታ ውስጥ ምንም መስራት አይችልም፡፡ ትክክለኛው የዚህ ዓለም ጥድፊያና ሁካታ መገለጫ ይሄ ልጅ ነው፡፡

ይህ ልጅ በልጅነቱ ወላጆቹ ‘ስፒድ’ የሚል ቅጥያ ስም ያወጡለት አለነገር አይመስለኝም፡፡ በተፈጥሮው Hyperactive የሚባል አይነት ሰው እንደሆነ ያስታውቃል፡፡ ሰውነቱ የሚያመነጨው የሚያስጨንቅ ኢነርጂ አለው፡፡ ያንን ኢነርጂውን በጩኸት እና በጥድፊያ ያወጣዋል፡፡ እሱን የሚያረጋጋውም ይኸው ነው፡፡
ባለሙያ ባልሆንም ጥቂት በማውቃት ሳይንስ ልክ …ስፒድ በግልጽ የሚታይ ADHD የተባለ የትኩረት ማጣት እና መቅበጥበጥ (አለመረጋጋት) የሚያስከትል Disorder እንዳለበት የሚያሳብቁ ምልክቶችን አይቼበታለሁ፡፡ ተረጋግቶ ቁጭ አለ ስትለው ድንገት እንደእንቁራሪት እንጣጥ ይላል፡፡ ስላሴ ቤተክርስቲያን ሲገባ የሆነውንና ያሳየውን ድርጊት ካያችሁት በቂ ነው፡፡ ያንን የተረጋጋ ስፍራ ለሰከንዶች መልመድ ተቸገረ፡፡ ራሱን ለመቆጣጠር ሲሞክር ይታያል፡፡ ውስጡ እምቢ ሲለውና ሲዘል አያችሁት፡፡ ብቻውን ጣቶቹን እየፈተለ በማይሰማ ድምጽ እያነበነበ ነበር፡፡ ከዚያ እንደወጣ የተጠራቀመ ኢነርጂውን እንዴት እንዳወጣውም ታዝባችኋል፡፡

ስፒድ ኮንተንቱን እንዲሰራ የሚመቸው ጫጫታና ጩኸት እንጂ ዝምታና እርጋታ አለመሆኑን ግብጽ ጊዛ ፒራሚዶች ውስጥ ከነበረው ‘ቶታል ሸትዳውን’ ትረዳላችሁ፡፡ የርሱ ተከታዮችም የሚፈልጉት ሁካታ ስለጠፋ ያኔ ቁጥራቸው ዝቅተኛ ነበር፡፡
በዚህ ዘመን የሰለጠነ ሃገር ውስጥ በተለይ በምዕራቡ ስልጣኔ ውስጥ ላለ ዜጋ እርጋታና ቁምነገር ቦታ የላቸውም፡፡ ምክንያቱም ያንን የርጋታ 'ስቴጅ' በትውልድ ቅብብል አልፎት መጥቷል፡፡ የህዝቡ ኑረት ከባህል፣ ወግ እና ልማድ አፈትልኮ ወጥቶ በግል አዳሪነት ላይ ተመስርቷል፡፡ ማህበረሰባዊ ደንብ የሚባል ነገር የለም፡፡ እንደእብድ ውሻ መክለፍለፍን ከምንም በላይ ዋጋ ሰጥቶ ያያል፡፡ አብርሃም ማስሎው የሰው ልጅ ፍላጎቶችን በ5 ደረጃዎች የተነተነበት ‘ማስሎው ቲየሪ’ እንደሚነግረን ከሆነ አብዛኛው በምዕራቡ ስልጣኔ ውስጥ የሚኖረው ዜጋ አሁን ያለበት ደረጃ 4ኛው “እውቅናና ክብርን ለማግኘት” የመፈለግ’ ደረጃ ነው፡፡ ምክንያቱም ከዚህ በፊት ያሉትን ሶስት ደረጃዎች በአብዛኛው አሟልቶ ‘ሳቹሬት’ አድርጓል፡፡ምግብ መጠለያ ሰላም ፍቅር ወዘተ አያሳስቡትም፡፡ ስለዚህ ዛሬ ለእርጋታና ስክነት ቦታ የለውም፡፡

ይኼ የዕድገት ‘ኢቮሉሽን’ ይዞት የመጣ ክስተት ነው፡፡ በዚህ የ GEN Z ዘመን ስክነት አይፈለግም፡፡ ባህሉና ስሪቱ ፍጥነት እና ጥሶ መሄድ ብቻ ነው ፡፡ አለም ዴዜዴራታ በተጻፈበት ዘመን ከተገለጸችበት በከፋ ሁካታና ጥድፊያ ውስጥ ናት፡፡ ስፒድ ይህንን የትውልዱን ይዘት ይዞ ቢመጣ፣ ሚሊዮን ቀርቶ ቢሊዮን ተከታዮችን ቢያፈራም አይደንቅም፡፡

እኔን ብዙዎቻችን ካደግንበት እና ከኖርንበት ባህል እና አስተዳደግ አንጻር አይደለም የአዲሱን ዘመን ጥድፊያ እና ሁካታ እየመንኩ ያለሁት፡፡ “ገና ባልደረስንበት ደረጃ ላይ ስንንጠላጠል ያልረገጥናቸው ደረጃዎች እንዳይክዱን እንጠንቀቅ” ነው እያልኩ ያለሁት፡፡ ማንንም በማይጠቅም የዲጂታል ጩኸት ላይ የተጠለፈውን ትውልድ የምመክረውም ይህንኑ ነው፡፡እንዳለመታደል ደንብና ህግ በሌለባት ሃገር ኢንተርኔት ይዞት የመጣውን ሁሉ ‘አዳፕት’ እንዲያደርግ ክፍቱት የተተወ የወጣት ጭንቅላት ስለስራ ማሰብ እየተሳነው እያየን ነው፡፡

ድሆች ነን፡፡ እንደህዝብም እንደሃገርም ከጩኸትና ሁካታ በፊት ገና ብዙ መስራት ያለብን የቤትስራዎች ይጠብቁናል፡፡ ከላይ በገለጽኩት ምክንያት ስፒድን የሚከተለውን 90 ምናምን ሚሊዮን የሞላለት የሰለጠነ ሃገር ህዝብ አይተን ‘ዘመኑ የሚጠይቀው ይህንን ነው’ ማለትና ያንኑ እዚህ አምጥቶ ‘ባህል’ ለማድረግ መሞከር ልክ አይደለም፡፡ የሰለጠነው ዓለም ዛሬ "ባዶ ቅል እና የሚንሸዋሸው ናስ' ለሚያወጣው ትርጉምየለሽ ድምጽ በጣም ያጋደለው እኛ ዛሬ ያለንበትን ደረጃ ለፍቶበት፣ ፈጥሮበት፣ ሰርቶበትና ተጠቅሞበት አልፎ ነው፡፡

ሰርቶ፣ ፍሬውን አፍርቶ፣ ጎተራ ከትቶ፣ ራሱን ከድካም አላቅቆ፣ ለልጆቹ ቀላል ህይወትን ሰጥቶ ያለፈ የቀደመ ትውልድ ነው ይህን ‘የአይሾው ስፒድ’ ተከታይ የሆነ ሚሊዮን ግሪሳ ወጣት የፈጠረው፡፡ ለብዙ መቶ አመታት በፈጠራ አዕምሮውን አስጨንቆ፣ በጠንካራ ጉልበት ፋግሮ ሃገር ሰርቷል፡፡ ስርዓት ገንብቷል፡፡ ለሚቀጥሉት ብዙ መቶ አመታት እሱና ትውልዱ የሚኖሩበትን ትሩፋት አጠራቅሟል፡፡ በዚህ ሳቢያ ዛሬ ጥያቄው እንደኛ ምግብና ሰላም ሳይሆን ‘መታወቅ’ ብቻ ነው፡፡'አይረቤ ጉዳይ ላይ' ተጠምዶ የምታዩት የልፋቱን ገጽ ስላለፈውና የእረፍቱ ገጽ ላይ ስለደረሰ ነው፡፡ ‘ኢቮሉሽኑ’ እዚህ አድርሶታል፡፡

እናም እንዳትሳሳቱ! የሰለጠነው አለም ህዝብ በጩኸትና ሁካታ ተጠምዶ ስታዩት ስሪቱ ከጅምሩ ይህ ሆኖ አይደለም፡፡ መዝናናትን የቅንጦት አድርጎ እስኪቆጥር ድረስ ላቡ ጠብ እስኪል ሰርቶ፣ ‘ኮንፋይንድ' ብቻውን አውርቶ ነው፡፡ ዛሬ በአደባባይ እንደውሻ መጮህን የሚያደንቀውና የሚያዳንቀው ያንን ደረጃ ስላለፈው ነው፡፡

እኛ ግን ገና ነን፡፡ በአይረቤ የባዶ ቅል ጩኸት ለመመሰጥ ገና ነን፡፡ ገና ምግብ አጥተን እየራበን ነው፡፡ ገና ስራ አጥተን እየደኸየን ነው፡፡ ገና ትምህርት አጥተን እየደነቆርን ነው፡፡ ገና ሰላም አጥተን እየተዋከብን ነው፡፡ ገና ገና ገና ብዙ ገናዎች አሉን፡፡ ያለንበት ደረጃ ሁሉን ትተን ለመዝናናትና ለመንዘፍዘፍ የሚያበቃን አይደለም፡፡

ስለዚህ ስፒድን ምሳሌ እያደረጋችሁ “ዘመኑ የቁምነገር አይደለም ፣ የትምህርት አይደለም፣ የስራ አይደለም፣ የልፋት አይደለም፣ የአቋራጭ 'ኮንተንት አልባነት ዘመን ነው “ የምትሉ ሰዎች ከዚህ ጠማማ መፈክራችሁን ተግ በሉ !

የቆማችሁበትን የአሸዋ መድረክ ስታዩት ዛሬ የምታዘናጉትና የምታዳንቁት የዲጂታል ትውልዱ ‘አልባሌነት’ የሚያስከፍለን የነገ ዋጋ ይገባችኋል፡፡ የቤትስራውን ጨርሶ ከሚዝናና አስተማሪ ጋር ዝላይ የሚጫወት ተማሪ መጨረሻው ተማሪም አስተማሪም እንዳይሆን በዚያው ተሰባብሮ መቅረት ብቻ ነው፡፡ እነሱና እና የሌለ ልዩነት ላይ ነን፡፡ አይናችሁን ግለጡ፡፡ አሁን ባለንበት ደረጃ ከአይሾው ስፒድ ወጣቶቻችን የሚወስዱት ትምህርትም የሚቀስሙት ልምድም የለም፡፡

ወጣቶች የስፒድን 'ኮንቴንት' እንደትሬንድ ይዘው ጥድፊያና ሁካታ ውስጥ መግባት ልክ ነው ብለው ማሰባቸውን አታበረታቱ፡፡ እንደውሻ እየጮህን ሃገራችንን እናስጠራለን ያለ ጨበሬ አይቻለሁ፡፡ በምታዳንቁት የዲጂታል ትውልድ ዘንድ እንግዲህ ሃገር ማስጠራት ትርጉሙ ይህ ነው፡፡

ሃገር ተረካቢ ናቸው ሲባሉ ትምህርትም ስራም ትተው ቤት የተቀመጡና ምንም ሳይሰሩ ስኬትን በላይክ እና ኮሜንት ብቻ የሚመዝኑ የድቡሽት ላይ ጎጆዎች በዝተዋል፡፡ በመሰረቱ እነሱም ስፒድ ለማንም ምንም አይጠቅሙም፣ ጠቅመውም አያውቁም፡፡ ከጠቀሙ ለራሳቸው ብቻ ነው፡፡ ተከታዮቻቸው ላይ እንጀራ ይጋግራሉ፡፡ አለቀ!!

ሃገር የሚያተርፈውና ራሱም የሚተርፈው ትውልድ በዲጂታሉ አለም መማርና ከረሱ አልፎ የሌሎችን ሀይወት መለወጥ የሚችል ኮንቴነት ይዞ የሚመጣው የነቃ ትውልድ ነው፡፡ ከዚህ ውጪ የደሃ ሃገር ወጣት ስፒድን አይኮርጅም፡፡ ስፒድ አባቶቹ የሰሩለት የተጠናቀቀ ሃገር ያለው ልጅ ነው፡፡ ሌላ ስራ የለበትም፡፡ እኛ ገና ራሳችን ሃገራችንን እንድንሰራ የምንጠበቅ የደሃ አባቶች ልጆች ነን፡፡ ከጥድፊያና ሁካታ በፊት በጣም ብዙ ስራ አለብን፡፡ ሃገርን ድቡሽት ላይ የሚገነባ ነገ መጠለያ ያጣል፡፡

ይመቻችሁ !!

መላኩ ብርሃኑ

5 months ago

No replys yet!

Be the first to share what you think — your comment will appear here.