Logo
FIDEL POST NEWS
ዓለም አቀፉ የዩቲዩብ ኮከብ አይሾው ስፒድ (IShowSpeed) በአዲስ አበባ፡ የዓድዋ መታሰቢያን በባዶ እግሩ ጎብኝቷል


​ታዋቂው አሜሪካዊ የዩቲዩብ ኮከብ እና የቀጥታ ስርጭት አቅራቢ ዳረን ዋትኪንስ ጁኒየር (በቅፅል ስሙ አይሾው ስፒድ) በኢትዮጵያ እያደረገ ባለው ጉብኝት መላውን የኢንተርኔት ዓለም ትኩረት ስቧል።

ወጣቱ ኮከብ በአሁኑ ወቅት በአዲስ አበባ ከተማ የሚገኙ ታሪካዊ ቦታዎችን እየጎበኘ የሚገኝ ሲሆን፣ የኢትዮጵያን ባህልና ታሪክ ለሚሊዮን ተከታዮቹ እያስተዋወቀ ይገኛል።

​የ21 ዓመቱ አይሾው ስፒድ ወደ አዲስ አበባ ሲደርስ በቱሪዝም ሚኒስትሯ ሰላማዊት ካሳ ደማቅ አቀባበል ተደርጎለታል።

ይህ ጉብኝት "Speed Does Africa" በሚል መጠሪያ በ20 የአፍሪካ ሀገራት እያደረገ ያለው ሰፊ ጉዞ አካል ነው። ስፒድ በኬንያ በነበረው ቆይታ በአንድ ቀን ውስጥ ብቻ 300 ሺህ አዲስ ተከታዮችን ማግኘቱ የሚታወስ ሲሆን፣ አሁን ላይ የዩቲዩብ ተከታዮቹ ቁጥር 48 ሚሊዮን ደርሷል።


​ከጉብኝቱ እጅግ አስገራሚ ትዕይንቶች አንዱ ስፒድ በአዲስ አበባ የሚገኘውን የዓድዋ ድል መታሰቢያን በባዶ እግሩ መጎብኘቱ ነው።

ለኢትዮጵያ ታሪክ ያለውን አክብሮት በገለጸበት በዚህ ቆይታው፣ በመታሰቢያው ውስጥ የሚገኙ ታሪካዊ ቅርሶችን ሲመለከት የነበረውን ስሜት በቀጥታ ስርጭት (Live Stream) ለተከታዮቹ አጋርቷል። ስርጭቱን በአንድ ጊዜ ከ 191 ሺህ በላይ ሰዎች ሲከታተሉት ተመልክተናል።

​በአትሌቲክስ ስሟ በገነነችው ኢትዮጵያ ከታዋቂ አትሌቶች ጋር ጊዜውን ያሳለፈው ስፒድ፣ "ኢትዮጵያ የፈጣን ሰዎች ሀገር መሆኗን አውቃለሁ" በማለት አድናቆቱን ገልጿል።

በቆይታውም፦
👉​የኢትዮጵያን ሰንደቅ ዓላማ በመያዝ ፍቅሩን ገልጿል፤
👉​ባህላዊ ልብሶችን በመልበስና እስክስታ በመለማመድ ተሳታፊ ሆኗል፤
👉​የኢትዮጵያን ባህላዊ ምግቦች በተለይም 👉👉እንጀራን በመቅመስ ምስክርነቱን ሰጥቷል።

​በማህበራዊ ሚዲያ ከ60 ሚሊዮን በላይ አጠቃላይ ተከታዮች ያሉት የዚህ ወጣት ጉብኝት ለኢትዮጵያ ቱሪዝም ትልቅ ዕድል ተደርጎ ተወስዷል። የሀገሪቱን ገጽታ፣ እንግዳ ተቀባይነት እና ዘመናዊ የቱሪስት መዳረሻዎችን ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ በተለይም ለወጣቱ ትውልድ በማስተዋወቅ ረገድ ከፍተኛ ሚና እየተጫወተ ይገኛል።

​አይሾው ስፒድ በቀጣይ ቀናትም ሌሎች ታሪካዊ ቦታዎችንና የቱሪስት መስህቦችን እንደሚጎበኝ ይጠበቃል።
5 months ago

No replys yet!

Be the first to share what you think — your comment will appear here.