Logo
FIDEL POST NEWS
በድሬዳዋ በተመሳሳይ ቁልፍ ስርቆት ሲፈጽሙ የነበሩ ከ150 በላይ ግለሰቦች በቁጥጥር ስር ዋሉ

​ በድሬዳዋ የወንጀል አፈጻጸም ስልታቸውን በመቀየር፣ የመኖሪያ ቤቶችንና የተሽከርካሪ አካላትን ሲሰርቁ የነበሩ ከ150 በላይ ተጠርጣሪዎች በፖሊስ ቁጥጥር ስር መዋላቸው ተገለጸ።

​ተጠርጣሪዎቹ ቀደም ሲል ይፈጸም የነበረውን የሌሊት ስርቆትና ጣራ የመቅደድ ዘዴ በመተው፣ አዲስ ስልት በመጠቀም ላይ ተሰማርተው እንደነበር የድሬዳዋ ከተማ ፖሊስ አስታውቋል።


​የድሬዳዋ ከተማ ፖሊስ ጠቅላይ መምሪያ የገፅታ ግንባታ እና ሚዲያ ዲቪዥን ኃላፊ ሳጅን መሀመድ አብደላ እንደገለጹት፤ ተጠርጣሪዎቹ ​በአካባቢው ያለውን እንቅስቃሴ በጥናት በመለየት ሰዎች በሌሉበት ሰዓት ተመሳሳይ ቁልፎችን (Master Keys) በመጠቀም ወደ ቤቶች ገብተዋል።

​በቀንና ሰዎች በሚንቀሳቀሱበት ወቅት ማንም አለመኖሩን በማረጋገጥ የቤት ውስጥ ቁሳቁሶችን ዘርፈዋል።

​በተጨማሪም በየመንገዱ የቆሙ ተሽከርካሪዎችን አካላት በመፍታት ስርቆት ፈፅመዋል ተብሏል።

ፖሊስ እንደገለፀው ​ከህብረተሰቡ በደረሰ ጥቆማና በተደረገ ጠንካራ ክትትል ከተጠርጣሪዎቹ ጋር በርካታ ንብረቶች ተይዘዋል። ከእነዚህም መካከል፦
​ለኮሪደር ልማት የተገጠሙ የሶላር ባትሪዎች፣
​የቴሌኮም እና የመሰረተ ልማት ንብረቶች፣
​ቴሌቪዥኖች እና የተለያዩ የቤት መገልገያ ቁሳቁሶች ይገኙበታል።

​ፖሊስ የተያዙትን ንብረቶች ለባለቤቶቻቸው ለመመለስ ዝግጅት እያደረገ መሆኑን ገልጿል።

በመሆኑም ንብረት የተሰረቀባችሁ ግለሰቦች በድሬዳዋ ፖሊስ ጠቅላይ መምሪያ ወንጀል ምርመራ ዘርፍ ቢሮ በአካል በመቅረብና ማስረጃ በማቅረብ ንብረቶቻችሁን መለየትና መረከብ የምትችሉ መሆኑን ጥሪ ቀርቧል።
5 months ago

No replys yet!

Be the first to share what you think — your comment will appear here.