የአርቲስት ያየህይራድ አላምረው (1957-2017)÷ መዘክር እና የስብስቦቹ ቤተመጻሕፍት፤
(ሠርጸ ፍሬስብሐት)
አጭር ማስታወሻ
#ethiopia | ኹላችን በምናውቀው ታሪኩ፤ ያየህይራድ አላምረው፤ የግጥም እና ዜማ ደራሲ እንዲሁም ፕሮዲውሰር እንዲያም ሲል የታላላቅ ሙዚቃዊ ፕሮጀክቶች ነዳፊ ኢንተርፕረነር ነበር፡፡ ለብዙዎቻችን በሚያስገርም እና በሚያስደንቅ፣ ብዙም ባልተነገረለት፣ ጥቂት የቅርቦቹ በኾኑ ወዳጆቹ እና በቤተሰቦቹ ዘንድ ብቻ በሚታወቅ ልምዱ ደግሞ፤ የንባብ ፍቅሩን ብዙ እጥፍ የሚያስከነዳ መጽሐፍ ሰብሳቢነቱ አስደናቂ ነበር፡፡
ከኅልፈቱ በኋላ የተገለጸው ምሥጢሩ ይህ መጻሕፍትን እጅግ አድርጎ የመውደዱ ነገር ነው ቢባል ማጋነን አይኾንም፡፡ “ምን ሲያደርግ ሰበሰባቸው?” የሚያስብሉ መጻሕፍትን እና ያልታተሙ መዛግብትን ሰብስቧል፡፡ የኅልፈቱ ዜና ከተሰማበት ታኅሣሥ 24 ቀን 2017 ዓ.ም. ቀደም ባሉ ቀናት የወጡ ዐዳዲስ መጻሕፍትን ሳይቀር ገዝቶ እያነበበ ነበር፡፡ እነዚህን መጻሕፍት በወጉ አደራጅቶ የሚያስቀምጥበት ቤት እንደሚያስፈልገው ለቤቶች ኮርፖሬሽን ማመልከቻ እስከመጻፍ ባደረሰ ፍቅር፣ መጻሕፍቱን የሚያስቀምጥበት ክፍል ቢጠበውም እንኳ፣ መጻሕፍትን ከመሰብሰብ ግን አልቦዘነም፡፡
ምናልባት የግጥም ድርሰቶቹ ጠለቅ ማለት፣ የሀገር ፍቅርን፣ ታሪክን፣ ሃይማኖታዊ ጉዳዮችን፣ ለየት ያሉ የሕይወት ፍልስፍናዎችን እንዲያነሳ ሰበቡ ከንባብ ልምዱ የተነሳ ነበርን? ብለን እንድናስብ የሚያደርጉ፣ በሕይወት ዘመኑ ሙሉ የሰበሰባቸውን መጻሕፍት አግኝተን ተደንቀናል፡፡
በአንድ መልኩ በክዋኔ ጥበባት ባለሙያዎች (በከያንያን) ልማድ ውስጥ “እምብዛም አይስተዋልም” የሚባለውን የንባብን ጉዳይ፣ “ለካ እንዲህ በጥልቀት የሚያነበም አለ፤” እንድንል የ“ቆምታ” ዕድል ፈጥሮልናል፡፡
እንዲህ ለመኾን መቼም መሠረት ያስፈልጋል፡፡ መሠረቱ ከወላጆቹ፣ በተለይም ከወታደር አባቱ ከሻለቃ አላምረው መንገሻ የተነሳ ይመስላል፡፡ የእናቱ የወ/ሮ አዳም ከበደ አስተዋጽዖም ለያየህይራድ አላምረው በሀገር ፍቅር የነደደ ማንነት የራሱ ድርሻ ነበረው፡፡
የወታደሮች ካምፕ (ሚሊተሪ ካምፕ) የነበረው፣ የጦር ሠራዊት የሙዚቃ ክፍልን ዕያየ ለማደግ ዕድል የሠጠው የልደታ አቅራቢያው የቶሎሣ ሠፈር ልጅ መኾን በራሱ፣ የሙዚቃንም የሀገር ፍቅርንም አዛንቆ ለማደጉ ሰበብ ሳይኾን ይቀራል? የተማረባቸው ተማሪ ቤቶች÷ ተስፋ ኮከብ እና ልዑል መኮንን ከስማቸው በሚነሣ ማንነት፣ ያየህይራድን በሀገር እና በጥበብ ፍቅር አንጾ፣ በንባብ ልምድ ቀርጾ ለማሳደግ የሚበቃ የተማሪ ቤት ባህል የዘረጉ ነበሩ፡፡
እንዲያውም፤ ያየህይራድ ራሱ እንደገለጸው፤ ከዘፈን ግጥም የመጻፍ ዝንባሌው አስቀድሞ የጻፋት አንዲት የሬዲዮ ድራማ፣ በእሑድ ፕሮግራም ኢትዮጵያ ሬዲዮ ላይ የመተላለፍ ዕድል ማግኘቷ፣ በተማሪ ቤቱ መምህራን እና በተማሪ ጓደኞቹ ዘንድ ዝነኛ እና የወደፊት በጥበብ ሕይወት የመዝለቅ ተስፋውን በሩቅ እንዲያይ ዕድል የሠጠ የልጅነት አጋጣሚም ነበር ማለት ይቻላል፡፡
የጥበብ ሥራ ከክዋኔው በላይ፣ ከማጊያጊያጥ ከማሠማመሩ በላይ ፈጠራው እጅግ ጥልቅ ነው፡፡ መንገድ እና ሥልቱ የማይታወቅ፣ በቀመር የማይሠላ፣ ዛሬ የሔዱበት መንገድ ለነገው የማይሠራ፣ በየቀኑ ተአምር የመጠበቅ ያህል ከባድ ጉዳይ ነው፡፡
በተለይ እንደ ሥነ ግጥም ያለው፣ ከግጥምም፤ ለዜማ ወይም ለሙዚቃ የሚኾን ግጥምን መጻፍ እጅግ ከባድ ነው፡፡ ለዜማ የሚኾን ግጥምን የመድረስን ሥራ ከባድ የሚያደርገው፣ ግጥም ራሱ ዜማዊ መኾኑ ሲኾን፣ ይሄው ራሱ ሙዚቃዊ የኾነው ግጥም፣ ዜማዊ ሥልጣኑ ከፍ ባለው ሙዚቃ ውስጥ “ና ግባ” ሲባል፣ የራሱ መግደርደር እና እምቢ ባይነት ስላለው ነው፡፡ ግጥሙ ለዜማ ሥልጣን ለመሸነፍ ግዴታ አለበት፡፡
ዜማ ባወጣለት ሐዲድ ለመጓዝ ይገደዳል፡፡ ለዜማው ምጣኔ ሲባል ቃል ይቆረጣል፡፡ ቅርፁ እንዲያጥር ወይም እንዲረዝም ይደረጋል፡፡ የራሱን ምት ትቶ፣ የሙዚቃውን ሥልተ ምት፣ ባር እና ሪዝም እንዲከተል ይገደዳል፡፡
በብዙ የሚያከራክር ቢኾንም፤(ከዜማ ወደ ግጥም ድርሰት መምጣት ይሻላል? ወይስ ግጥሙን ወደ ዜማ መተርጎም ይሻላል? የሚለውን የማይቋጭ ክርክር ለጊዜው እናቆየውና፤) የዜማ ግጥም ጸሐፊ የኾነ ሰው፣ የዜማን ልሣን ወደ ቃል የመተርጎም ችሎታ የታደለ ቢኾን ይበልጥ ይሳካለታል፡፡
እንዲህ ያለው ተሠጥዖ ለገጣሚዎች ኹሉ የተሠጠ አይመስልም፡፡ የራሳቸውን የቃል እና የቤት ነጻነት ለሚፈልጉ ባለቅኔዎች፣ ይህ ዓይነቱ የሙዚቃዊ ዜማ ሥልጣን አይዋጥላቸውም፡፡ በቅኔያዊ መራቀቃቸው እጅግ የሚያስደንቁን ጠቢባን፣ ወደ ሙዚቃዊው የዜማ ግጥም ሲመጡ ግር የሚላቸው ለዚህ ነው፡፡
ያየህ ይራድ አላመረው፤ የዚህ ምሥጢር የተገለጠለት ድንቅ የዘፈን ግጥም ደራሲ ነው፡፡ በጻፋቸው የዘፈን ዜማ ግጥሞች ላይ ኹሉ የምናየው ጸጋው፣ የዜማን ልሳን በቃል የመተርጎም ችሎታውን ነው፡፡ ይህንንም በሕይወት ታሪኩ ላይ ለተጠቀሱት ድምጻውያን በሠጣቸው ሥራዎች ላይ ኹሉ ማረጋገጥ ይቻላል፡፡
በኢትዮጵያ ሙዚቃዊ ባህል ውስጥ ኾኖ የዘፈን ግጥም ጸሐፊ መኾን ሌላም ከባድ ነገር አለው፡፡ የጥንታዊ ሕዝብ ጠንካራ የገጣሚነት ጣጣ፡፡ በተለምዶ “ጥንታዊ ሕዝቦች ቀልድ እና ግጥም ዐዋቂዎች ናቸው፤” ይባላል፡፡
ለዚህም የመካከለኛው ምሥራቅ ጥንታውያን ሀገራትን፣ እና ኢትዮጵያንን ምሣሌ የሚያደርጉ ብዙዎች ናቸው፡፡ የኹሉንም እንተወውና የሀገራችን የገጣሚነት ባህል ጠንካራነቱ ምንም ጥያቄ የለውም፡፡ ጋሽ ጸጋዬ ገብረ መድኅን እንዳሉት “ኢትዮጵያዊ፤ ከአንቀልባው እስከ መቃብሩ በግጥም የተከበበ ነው፤” ጭራሽ፣ አዝማሪው የሚያዜመው ግጥም አልበቃ ብሎት፣ “ተቀበል” ብሎ ግጥም የሚሠጥ ሕዝብ ነው፡፡ እዚህ ገጣሚ ሕዝብ መሐል፣ አንጀት አርስ የዘፈን ግጥም ጸሐፊ ኾኖ መገኘት እጅግ ከባዱ ፈተና ነው፡፡
የያየህይራድ አላምረውን የጥበብ ሕይወት እጅግ እንድናደንቅ የሚያደርጉን ጉዳዮች ይሄንን መሠረትም ሊሰቱት አይገባም፡፡ ኹሉም የፈጠራ ጉዞዎች የየራሳቸው ፈተና ያለባቸው ቢኾንም፣ የዘፈን ግጥም ደራሲነት የሚጨምራቸው፣ ከሌላኛው የሙዚቃ ጥበብ ጓዝ እና ቅንጣቶች የሚነሱ ፈተናዎች አሉበት፡፡
እንደ ያየህ ይራድ አላመረው ያሉትን የዘፈን ግጥም ደራሲዎች እጅግ እንድናደንቃቸው የምንገደደው በዚህ እና ከራሱ ከገጣሚነት ችሎታቸው በሚመነጭ ጠቢብነታቸው ምክንያት ነው፡፡ የሻምበል አፈወርቅ ዮሐንስ፣ የተዘራ ኃይለ ሚካኤል፣ የተስፋዬ አበበ፣ የሸዋ ሉል መንግሥቱ፣ የዓለምፀሐይ ወዳጆ፣ የይልማ ገብረ አብ፣ የሙሉጌታ ተስፋዬ፣ የተመስገን ተካ እና የሌሎችም ታላላቅ የዘፈን ግጥም ደራስያን፤ የዜማ ግጥም ደራሲነት ጉዞ መንግድ፣ ሥልቱ እና ዐቅዱ ይሄንኑ ይመስላል፡፡
ያየህ ይራድ፤ ዜማን ወደ ግጥም የመተርጎም ሥራን ብቻ ሳይኾን፤ ዜማን እና ግጥምን በአንድ ላይ የመፍጠር ሥራ የሠራባቸው የሙዚቃ ሥራዎችም ቁጥራቸው ቀላል አይደለም፡፡ ዜማ እና ግጥም መንታ ኾነው ከአንድ የፈጠራ ሰው ሲወለዱ የሚታይ ሌላ ውበትም አለ፡፡
ታላቁ የዜማ እና ግጥም ደራሲ፣ ፕሮዲውሰር እና የትላልቅ ሙዚቃዊ ፕሮጀክቶች አዘጋጅ የነበረው፤ ያያየህ ይራድ አላምረው፤ ከበርካታ የድርሰት ሥራዎቹ መካከል፤
ለኩኩ ስብስቤ (“ይቺ ነች ሀገሬ” ያለበትን አልበም፤ በርካታ ሥራዎች ግጥም፤ በኋላ ደግሞ “የአፍሪካ ገናና” አልበም ውስጥ ያሉ ድርሰቶችን)፣
ለአስቴር ዐወቀ(የ“ሰበቡ” አልበም ሙሉ ድርሰት)፣
ለዳምጠው አየለ፣
ለኤልያስ ተባባል (“ቅሪብኝ”)፣
ለፀሐይ ዮሐንስ፣
ለቴዎድሮስ ታደሰ፣
ለተሾመ አሰግድ፣
ለተሾመ ወልዴ፣
ለኃይልዬ ታደሰ (ይሞታል ወይ አልበም ፕሮዲውሰሩ ራሱ ያየህ ይራድ ሲኾን፣ የኢትዮጵያ አምላክ እና ይሞታል ወይ የራሱ የያየህ ይራድ ድርሰቶች ናቸው፡፡
ለጽጌሮማን አስናቀ (ባቲ)፣
ለጸጋቸው ኃይለ ኢየሱስ (ለመለም)፣
ለታደለ ሮባ እና ለብርሃኑ ተዘራ፣
ለደረጀ ደገፋው፣
ለጌራወርቅ ነቅዓ ጥበብ፣ እና
በመጨረሻ ደግሞ፤ “ቆሜ ልመርቅሽ” የጥላሁን ገሠሠ አልበም ላይ ራሱን “ቆሜ ልመርቅሽ”ን ጨምሮ የአልበሙን ድርሰት የሠራው ያየህ ይራድ አላምረው ነበር፡፡
ያየህይራድ፤ በተምሣሌት እና በፈሊጥ የበለጸጉ ግጥማዊ ይዘቶችን እጅግ ይወዳል፡፡ በተለይም የአዝማሪዎችን የግጥም ሥልት አጅግ አድናቂ ሙዚቀኛ ነው፡፡ በአገጣጠም ሥልቶቹ ውስጥ የአዝማሪዎችን የግጥም መንገድ የተከተለባቸው ሥራዎች በርካታ ናቸው፡፡
ለማርታ አሻጋሪ፣ ለተሾመ አሰግድ፣ ለበዛወርቅ አስፋው እና ለኤልያስ ተባባል የሠጣቸው ድርሰቶች፤ ይህንን ፍላጎቱን በይበልጥ ጎልተው እንዲወጡ ያደረገባቸው ሥራዎቹ ናቸው፡፡ በአስቴር ዐወቀ ሰበቡ አልበም ውስጥ የፎክ ግጥሞችን መቀላቀሉ የዚህ አዝማሚያው ማሣያ ነው፡፡ ምናልባት፤ ታላቁን የባህል ጥበበኛ እና አዝማሪ ባሕሩ ቀኜን የማድነቁ እና ሥራዎቻችው ዓለም አቀፋዊ ዕውቅና እንዲያገኙ እና እንዲሸለሙ የማድረጉ ፍላጎትም ከዚህ የረዥም ጊዜ ጥረቱ የመነጨ ሊኾን ይችላል፡፡
በማኅበራዊ ጉዳይ ላይ ያተኮሩ በርካታ ሥራዎችንም ሠርቷል፡፡ በተለይ “እንኖራለን ገና” አልበም፤ ፕሮጀክቱን ከመምራት እስከ ድርሰት ትልቅ ሥራ የሠራበት አልበም ነው፡፡ ይህ አልበም፤ አንድን ማኅበረሰባዊ መልእክት በጥበብ ለማቅረብ ዘወትር የምንጠቀማቸውን የተሰለቹ መንገዶች እንደገና እንድንመረምር፣ በፖፕ ሙዚቃ ቅርጽ እና ደረጃ መልእክቱ ቀጥተኛ ትምህርት ሳይኾን፣ በጥበብ የተዋዛ መኾን እንደሚችል ያሣየበት ሥራው ነው፡፡
ለዚህ አልበም ስኬት፣ የሙዚቃ ባለሙያዎቹ እና የድምጻውያኑ አስተዋጽዖ ምንም ምትክ የማይገኝለት ቢኾንም፤ የፕሮዳክሽን አቅጣጫውን እና ፍልስፍናውን የመወሰን ሥራው አልበሙን እጅግ የተዋጣለት ያደርገዋል፡፡ ዛሬ ፍቅረዐዲስ ነቅዓ ጥበብ የተጫወተቺውን በዚያ አልበም ውስጥ የተካተተውን የዶ/ር ተሸገር ሺፈራው ድርሰት የኾነውን ሙዚቃ፣ ለኤች.አይ.ቪ. የተሠራ ሥራ ነው ብለን ብንናገር ብዙ ሰው እውነት አይመስለውም፡፡
ለአብነት ያህል እሱን አነሳን እንጂ፣ በዚህ አልበም ላይ የተካተቱት፤ የንዋይ ደበበ፣ የአስቴር ዐወቀ፣ የበዛወርቅ እና የኤልያስ፣ የቴዎድሮስ ታደሰ፣ የኄኖክ መሐሪ፣ የጼዴንያ ገብረ ማርቆስ፣ የዳዊት መለሰ… ሥራዎች ይሄንኑ እውነት የሚያረጋግጡልን ሥራዎች ናቸው፡፡
የዚሁ አልበም ማስተዋወቂያ ሌላ ሥራ ኾኖ የወጣው፤ ዘሪቱ ከበደ፣ አብነት አጎናፍር፣ ጆኒ ራጋ የተጫወቱት “መኖርህን ሌሎች ይሻሉ ይፈልጋሉ” የሚለው መዝሙር የግጥም ድርሰት ያየህ ይራድ አላምረው ከኤልያስ መልካ ጋር የጻፈው ነው፡፡ የመልእክት ጥልቀቱ ከኤልያስ ኅልፈት ጋር ተያይዞ በሰፊው የተተርኳል፡፡ ነገር ግን፤ የኤልያስ መልካ እና የያየህ ይራድ አላምረው ስሜት እና ሐሳብ ምን ያህል ውሕደት እንደነበረው ለማየት በአብነት የሚጠቀስ ድንቅ ሥራ ነው፡፤ የዚህ ሙዚቃ በእነዚህ ማኅበራዊ ጉዳይ ላይ በሚያተኩሩ ሥራዎቹ ውስጥ የሚታየው የጥበብ ልቀት፤ ማኅበራዊ ጉዳይን ርእሳቸው አድረገው የሚነሱ ሥራዎች፣ መዝሙር መሳይ ብቻ ሳይኾን፣ የዘመኑን የፖፕ ሙዚቃ ቅርጽ ተሸክመው፣ በጥበብ ልቀው መሠራት እንደሚችሉ መረጋገጫ እና ማስተማሪያ ጭምር ነው፡፡
ኢትዮጵያ በያየህ ይራድ ድርሰት ውስጥ የትልቅ ብዕሩ መገለጫ ነች፡፡ ከሀገር ውጪ በነበረው ሕይወት ናፍቆት ብቻ የተፈጠረች ጉዳይ አይደለቺም “ኢትዮጵያ” ለያየህ ይራድ አላምረው፡፡ እንዲያውም፤ በወታደር ልጅነቱ፣ በወታደር ሠፈር በማደጉ የተፈጠረች “ከ-ይቺ ነች ሀገሬ” እስከ “ቆሜ ልመርቅሽ የዘለቀች፣ የዕድሜ ልክ ጉዳዩ ነበረች ማለት ይቻላል፡፡ ትንቢትም ተናግሮላል፡፡
“የሺ ዓመታት የአፍሪቃ ገናና፣
ተከብራ የኖረች በዓለም ዙሪያ ገና፤
ኢትዮጵያ ዳግም እንደገና፣
ይታየኛል ያገር አውራ ኾና፤” (ኩኩ ሰብስቤ)
“የኢትዮጵያ አምላክ ይፈርዳል ሳይውል ሳያድር፣
ይጥልላታል ጠላቷን እባንዲራው ሥር፤
አይቀር አንድ ቀን መድረሱ ወቅቱን ጠብቆ፣
ማሪኝ ይላታል ጠላቷ እግሯ ላይ ወድቆ፤” (ኃይልዬ ታደሠ)
“አንገትሽ ራስሽን ችሎ ልየውና፣
ማግስቱን ይውሰደኝ ዐሥር ሞት ይምጣና፤”
(ቆሜ ልመርቅሽ-ጥላሁን ገሠሠ)
እነ “አንድ ብር ለአንድ” ወገን፣ “ሀገር ፍቅር ክብር፤ ኢትዮጵያ በፊትም ወደፊትም” የተሰኙ ትላልቅ ሀገራዊ መድረኮችን እና ፕሮጀክቶችን በመምራት፣ ከዩ.ኤስ.አይ.ዲ.፣ ከአሜሪካን ኤምባሲ፣ ከዚ.ዲ.ሲ.፣ ከወርልድ ባንክ፣ ከናይክ ፋውንዴሽን ጋር ሠርቷል፡፡
1957 ዓ.ም. ወደዚህች ዓለም መጥቶ፣ ታኅሣሥ 24 ቀን 2017 ዓ.ም. በድንገት ከዚህች ዓለም በሞት የተለየው ያየህይራድ አላምረው፣ በዚህች አጭር ማስታወሻ ተዘርዝረው የማያልቁ በጥበብ ሰውነቱ በግዝፈት ምንጊዜም የሚያስጠሩትን በርካታ ሥራዎች ሠርቶ አፏል፡፡
በሥራዎቹ ምንጊዜም የመታወሱ ነገር አንድና ኹሉት ባይኖረውም፣ በቤተሰቦቹ አማካኝነት፣ ለኢትዮጵያ ቤተመዛግብት እና ቤተመጻሕፍት አገልግሎት (ወመዘክር) የሚሠጡት(የሚበረከቱት) የዕድሜ ልክ ስብስብ መጻሕፍቱ እና እነዚህን መጻሕፍት ተረክቦ የሚያስነብብበት የማንበቢያ ክፍል ደግሞ፤ በልዩ ኹኔታ እንዲታወስ እንደሚያደርገው አይጠረጠርም፡፡
አንባብያን፤ በዚህ በያየህይራድ አላምረው ስም በተሰየመ የንባብ ክፍል ውስጥ የሚያሳልፉት ጊዜ ከንባብም በላይ ነው፡፡ የዚህን ታላቅ ደራሲ ቀልብ መግዛት የቻሉ፣ የእርሱ መዳፍ ይዟቸው፣ የዐይን ትኩረቱ ያረፈባቸውን መጻሕፍት ማንበብ ትርጉሙ “እንዲህ እና እንዲያ ነው” የሚባል አይደለም፡፡
ይህ ታኅሣሥ 22 ቀን 2018 ዓ.ም. መርቀን የምንከፍተው “የአርቲስት ያየህይራድ አላምረው÷መዘክር እና የስብስቦቹ ቤተመጻሕፍት”፤ ሌሎች ጠቢባንም እንዲሁ ሥራዎቻቸውን እና የመጻሕፍት ስብስቦቻቸውን ለዚህ ታላቅ ተቋም እንዲሠጡም ያነሣሣል የሚል ተስፋ አለን፡፡ በመጨረሻም፤ ይህ እንዲኾን ትልቁን ድርሻ የተወጡትን፣ የያየህይራድ አላምረውን ቤተሰቦች፣ በተለይም እኅቱን ወ/ሮ ኂሩት አላምረውን፣ መጻሕፍቱ በዚህ ተቋም እንዲህ ያለ ሥፍራ አግኝተው ለትውልድ የሚተርፍ ቁም ነገር እንዲሠራባቸው ላደረጉት ጥረት እና ልግስና፤ ተቋማችን እጅግ አድርጎ ያመሰግናል፡፡

5 months ago