Logo
FastMereja
ከሎዛ ኹነቶች የተሰጠ ወቅታዊ መግለጫ

የተወደዳችኹ ኦርቶዶክሳውያን በያላችኹበት ሠላመ እግዚአብሔር ይብዛላቹ! ሰሞኑን በአንዳንድ እና ጥቂት ማኅበራዊ ሚዲያ ተጠቃሚ ግለሰቦች ዘንድ በተቀናጀ እና በተደራጀ መንገድ ሎዛ ኹነቶች አዘጋጅን - Loza Events organizer ን እና ከሎዛ ኹነቶች አዘጋጅ ጋራ አብረው ይሠራሉ የተባሉ ሚዲያዎችን፣ የኪነ ጥበብ ባለሙያዎችን፣ ዩቱበሮችን እና ቲክቶከሮችን አስመልክቶ ያልተገባ መልክ በመስጠት የስም ማጥፋት ዘመቻ መክፈታቸውን ተመልክተናል።

እንዲህ ዓይነት የስም ማጥፋት ዘመቻ ባደረጉ አካላት ላይ በእጅጉ አዝነናል፤ አፍረናልም፡፡ እግዚአብሔር ወደ ልባቸው እንዲመልስቸው እንለምናለን፡፡ ነገር ግን እኒህ አካላት በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ ያለስማችን ስም በመስጠት በሐሰት የስም ማጥፋት ዘመቻ ስለዘመቱብን፣ ሁሉም ኦርቶዶክሳውያን እና ኦርቶዶክሳውያት እውነታውን ማወቅ ስላለባቸው እና በጉዳዩ ዙሪያ ያለውን እውነታ አውቀው የራሳቸው ኅሊናዊ ፍርድ እንዲሰጡ ይህንን ወቅታዊ መግለጫ መስጠት አስፈልጓል፡፡

ስለዚህ የተወደዳችሁ ኦርቶዶክሳውያን እና ኦርቶዶክሳውያት! ‹‹ነገርን ከሥሩ ውኃን ከምንጩ›› እንዲሉ፡፡ እውነታውን በማኅበራዊ ሚዲያ በሚነዛ አሉባልታ መነዳት ሳይሆን እውነቱን ከምንጩ እንሆ፡፡

1. ሎዛ ኹነቶች ማን ነው?
ሎዛ ኹነቶች የቤተመንግሥትም
የቤተክህነትም ሕጋዊ ፈቃድ ያለው ተቋም ነው። በሀገራችን ብቻ ሳይኾን በቤተክርስቲያናችን ታሪክ የመጀመሪያው እና ፈር ቀዳጁ መንፈሳዊ እና ሳይንሳዊ በኾነ መንገድ ኹነቶች እያዘጋጀ ያለ በአጭር ጊዜ ስምና ዝናን ያተረፈ ድንቅ ተቋም ነው።

ተቋሙ የሚሠራው ኦርቶዶክሳዊ ኹነቶችን ነው። ከእርሱ በኋላም መንፈሳዊ ሠርጎችን የሚያዘጋጁ ተቋማት እንዲበዙ አርአያ የኾነ፤ ተዋሕዶ በልምድ ብቻ ሳይኾን በትምህርት በተደገፈ ቅጥ(pattern) አገልግሎት መስጠት የሚችሉ ልጆች እና ተቋማት እንዳሏት ያሳየ ስንዱ እመቤት እንደኾነች በተግባር ያረጋገጠ እንዲኹም በር የከፈተ ተቋም ነው። በዚኽም እልፍ የምስጋናና እና የምስክር ወረቀቶችን አግኝቷል።

የሚሠጣቸው አገልግሎቶችም መንፈሳዊ ሠርጎችን ማዘጋጀት፣ የልደት መርሐግብሮችን፣ ጥምቀተ ክርስትናዎችን፣ የጋብቻ ክበረ በዓላትን፣ ምረቃቶችን፣ የሚዲያ ንቅናቄዎችን፣ ጋዜጣዊ መግለጫዎችን፣ የገቢ ማሰባሰቢያ መርሐግብሮችን ያዘጋጃል። ያስተዳድራል። ይመራል። ያስተባብራል።

ዓላማውም ጊዜ፣ ጉልበት እና የቦታ ርቀት ፈተና የኾነባቸውን ግለሰቦችን እና ኮሚቴዎችን የሥራ ሸክም በመሸከም፤ ድካማቸውን በመድከም ኦርቶዶክሳዊ ኹነቶችን መንፈሳዊ እና ሳይንሳዊ በሆነ መንገድ ማዘጋጀት ነው። ራእይው መንፈሳዊ ኹነቶች ቤተክርስቲያኗን በሚያውቁ፣ መንፈሳዊውንና ዘመናዊውን ትምህርት በቀሰሙ ልጆቿ የቤተክርስቲያኗን፣ ዶግማ፣ ቀኖና እና ትውፊት በጠበቀ ኹኔታ፣ ደረጃቸውን እና ከፍታቸውን ይዘው ከሌብነት፣ ከመጓተት እና ከብልሽት በጸዳ ፍኖት ኹነቶች ሲዘጋጁ ማዬት ነው።

ሎዛ ኹነቶች እንደ ተቋም እንደ መሪም በነፃ አገልግሎት የሰጠባቸው ተቋማት እና ግለሰቦች በጥቂቱ:-

1. የጎንደር ሐመረ ብርሃን ደብረ ምጥማቅ ማርያም ሕንፃ ቤተክርስቲያንን ለማስፈጸም ከጥር 23/2017 እሰከ ጥቅምት 03/2018 ለ 8 ወር ቀን እና ሌሊት ያለምንም ክፍያ አንዳንድ ጥቃቅን የቡድኑን ወጪዎች ጭምር ራሱ በመሸፈን ያስተባበረ፣ የመራ በራሱ ሚዲያም ለሦስት ቀናት በቀጥታ ሥርጭት ያስተላለፈ ድንቅ ተቋም ነው፤ በወቅቱ የሰጡትን ምስክርነትም ቪዲዮ ላይ ተመልከቱ። 100% የምንኮራበት አገልግሎታችን ነው።

2. ለራማ ኪዳነ ምሕረት ገዳም በሚሊኒዬም አዳራሽ የተዘጋጀውን መርሐግብር ከትኬት ሽያጭ ውጭ ያለውን ሥራ ያለምንም ክፍያ ሙሉ በሙሉ የማማከር እና የማስተባበር ሥራ ከመሥራት በተጨማሪ ዶክመንተሪ በነፃ የሠራ ተቋም ነው። ሌሎችንም በአጭር በአጭር ከዚኽ በታች ተቀምጠዋል፦

3.የመምህር በጽሐ ዓለሙ ጉባኤ ቤት የግዮን ሆቴል የቀጥታ ሥርጭት በነፃ አስተላልፏል እና የማስታወቂያዎችን ፕሮዳክሽን ያለምንም ክፍያ ሠርቷል፤

4. የጎንደር አዘዞ ሎዛ ማርያም ህዳር ጽዮን መርሐግብር እና አስተርእዮ ማርያም በሎዛ ማርያም (በነፃ መሥራት ብቻ ሳይኾን ገንዘብ ከራሱ ወጪ ያደርጋል)

5.2015 ያንን የመሰለ ከ300,000 ሰው በላይ የታደመበት ዝክረ አበው ለአዘዞ ደብረ ገነት ቅዱስ ሚካኤል ከኮሚቴዎቹ ጋር በመተባበር (ኢቨንቱን በነፃ መሥራት ብቻ ሳይኾን ገንዘብ ከራሱ ጭምር አውጥቶ ያስተባበረ ነው)

6. ማኅበረ ቅዱሳን አዲስ አበባ ማዕከል ግንፍሌ ለሚያስገነባው ሕንፃ የተሰጠውን ጋዜጣዊ መግለጫ አስተባብሯል፤

7. ለታዕካ ነገሥት ባዕታ ለማርያም ገዳም ጋዜጣዊ መግለጫ አስተባብሯል

8. ስምከ ሕያው ዘኢይመውት በሚል መሪ ቃል ሚሊኒዬም አዳራሽ ለተዘጋጀው ጉባኤ የሚዲያ ካምፔን የማስተባበር ሥራ በነፃ ሠርቷል፤

9. ለቂልጦ ቅድስት ማርያም ገዳም በየዓመቱ ሰኔ ማርያም ወደ ቂልጦ ማርያም በሚል መሪ ቃል ሚዲያዎችም በነፃ ሎዛ ኢቨንትም በነፃ ለበርካታ አመታት አስተባብሯል፤ ለወደፊትም ያስተባብራል፤

10. ተአምረ ማርያም ከግዕዝ ወደ ኦሮምኛ በብፁዕ አቡነ ናትናኤል ተተርጉሞ በማኅበረ ቅዱሳን አሳታሚነት ለንባብ የበቃውን የምረቃ እና ጋዜጣዊ መግለጫ አገልግሎት በነፃ አስተባብሯል፤ አዘጋጅቷል።

11.ለአምቦ ኪዳነ ምሕረት የተዘጋጀውን የዶክመንተሪ፣ የማስታወቂያ፣ የእራት እና የቀጥታ ሥርጭት መርሐግብር አምቦ እና አዲስአበባ ላይ የማማከር እና የማስተባበር ሥራ ያለ መታከት ያለ ክፍያ በነፃ በመሥራቱ ምስጋና እና አድናቆት ተበርክቶለታል።

12. 2016 ሆሳዕናን በሆሳዕና የማማከር እና የማስተባበር ሥራ እንደ ሎዛ ኢቨንት መርሐግብሩን መርቷል። እንደ ሚዲያም የቀጥታ ሥርጭቱን በነፃ አስተላልፏል።

13. ጻድቃኔ ማርያም ስትመረቅ ያደረግነው እንቅልፍ የሌለውን ሥራ፤ የዶክመንተሪ፣ የማስታወቂያ፣ የቀጥታ ሥርጭት፣ የሚዲያ ዘመቻ ተቆጥሮ የማያልቀውን የመምራት እና የማስተባበር ሥራ እንደ ግልም እንደ ቡድንም ያለምንም ክፍያ ለደከምነው ድካም ከእግዚአብሔር ውጪ ማን ሊከፍለን ይችላል?

14.ለሰሜን ወሎ ሀገረስብከት በዚያ የመከራ ዘመን ለሰጠነው የማማከር፣ የማስተባበር እና የማሰልጠን ሥራ ብፁዕ አቡነ ኤርሚያስን ብቻ መጠየቅ ተገቢ ነው።

15. ለኮምቦልቻ ገብርኤል የገቢ ማሰባሰብ የቀጥታ ሥርጭት፣ የማታ ጉባኤ እና ሩጫ ሁለት እና ሦስት ቀን ለሰጠነው የሚዲያ ሽፉን እንኳን ገንዘብ ልንቀበል የተቀየረውን የአውሮፕላን ትኬት እንኳ እራሳችን እንደከፈልን ምስክራችን ቅ/ገብርኤል፣ ኮሚቴው እና መምህር ደረጀ ዘወይንዬ ናቸው፤

16. ለደቡብ ኦሞ ሀገረ ስብከት በቅድስት ሥላሴ ዩኒቨርሲቲ የተዘጋጀውን ጋዜጣዊ መግለጫ ያስተባበረው ያለምንም ክፍያ ሎዛ ኢቨንት ነው፤

17. በለሳ የሚገኘውን ሙት አንሣ ማር ቅዱስ ሚካኤ አንድነት ገዳምን ከሰኔ 17/2017 ጀምሮ ለማስተዋወቅ ለመጀመሪያ ጊዜ የተደረገውን ጉዞ፣ ጉባኤ፣ ዶክመንተሪ፣ ማስታወቂያ፣ ጋዜጣዊ መግለጫ በረሃ ለበረሃ እየዞረ በነፃ ያለምንም ክፍያ ያስተዋወቀው፣ የመራው፣ ያማከረው ሎዛ ኹነቶች ነው፤

18. የያያ ዘልደታን ልደት ምክንያት በማድረግ ቦሌ የተደረገውን የነዳያን ምግባ በነፃ ያስተባበረው የሞንታርቦ ወጪ የሸፈነው ሎዛ ኹነቶች ነው።

19. የግሸን ማርያም ኮሚቴዎች ቢሯችን መጥተው በጠየቁን ያስተባብሩልን ጥያቄ መሠረት የማማከር ሥራውን ያለምንም ክፍያ የሠራው ሎዛ ነው። በዚኽ የተደሰቱት ኮሚቴዎች የቢሮ ኪራይ አለባችሁ፤ የሠራተኞች ክፍያ አለባችኹ ክፍያ እንፈጽምላችሁ ምን ብለን እንደመለስንላቸው ኮሚቴዎቹ እነ ዲ/ን አንተነህ የደሴውን ልጂ ጠይቁ ይነግሯቹሃል።

20. በመልአከ መዊዕ ተስፋዬ መቆያ አባትነት የሚመራው የሜሪላንድ ጽርሐ ጽዮን መንፈስ ቅዱስ ቤተክርስቲያንና የምእራፈ ቅዱሳን ቅድስት አርሴማ አንድነት ገዳምን በተመለከተ በኤሊያና ሆቴል የተሰጠውን ጋዜጣዊ መግለጫ በነፃ ያለምንም ክፍያ አስተባብሯል። ከዚያ በኋላ የነበረውን አገልግሎት በተመለከተ የማማከር ሥራ ሠርቷል። ገንዘብ ከኪሳችን አውጥተናል። 1 ብር ግን አልጠየቅናቸውም።

21. አዘዞ አየር ማረፊያ ሰሚው ሚካኤል ላይ የተሠራው የዶክመንተሪ አገልግሎት ሎዛ ኹነቶች በራሱ በነፃ የማስተባበር ሥራ ሠርቷል።

22.ክፍለ ሀገር ለሚገኘው የአቡነ ሐራ ገዳም የማማከር ሥራ በነፃ ሠርቷል።
23. ዘመን ተዋሕዶ ኤክስፖ ያለምንም ክፍያ ማርኮናል ኢቨንትስን በማገዝ የተሠራው።

24. ለአሐዱ ባንክ 2015 ከግንቦት 21 እሰከ ሰኔ21 /2015 ለተደረገው የሚዲያ ዘመቻ ያለምንም ክፍያ አንደ ወር ሙሉ በነፃ አስተባብሯል::

25. በእህታችን ዲዛይነር ሔቨን ጌታቸው የሚመራው ቤተ ሚካኤል ማኅበር 10ኛ ዓመት የምሥረታ በዓሉን ሲያከብር የማማከር እና የቀጥታ ሥርጭት መርሐግብር የሚዲያ ሽፋን እንደተቋም ያለምንም ክፍያ በነፃ አገልግሎት ሰጥቷል።

26. የጎጃም ጌራ መድኃኒት መድኃኔዓለም ገዳምን የማስታወቂያ ሥራ ለሎዛ ኹነቶች ድንቡሎ ሳይከፍሉ ያስተባበረላቸው እና የረዳቸው ሎዛ ነው።

27. ለአዲስአበባ ለሚገኘው ቅዱስ ሚናስ በየዓመቱ የሚዲያ የማስታወቂያ ሥራ ያለምንም ክፍያ የማስተባበሩን ሥራ የሚሠራው ሎዛ ነው።

28. የደብረ ዕንቁ ልደታን ኹነቱን ሳይኾን ዶክመንተሪውን እና የሦስት ቀኑን የቀጥታ ሥርጭት መርሐግብር በሚዲያው በነፃ የሠራው ሎዛ ነው።

29. የአቤኒን እና የባለቤቱን የቁርባን ሠርግ የቤተክርስቲያኑን እና የአዳራሽ ኹነቱን የsound፣ የሚዲያ ሽፋን በመስጠት በነፃ ያስተባበረው ሎዛ ነው፤

30. የአብራሃም ዘራጉኤልን ሠርግ የsound እና የሚዲያ ሽፋን በመስጠት ኹነቱን በነፃ ያስተባበረው እና ያማከረው ሎዛ ነው።
እነዚኽን ኹሉ በነፃ ሢሠሩ ድካማቸው እና ዋጋቸው ጠፍቶን ሳይኾን ዋጋችን በሰማይ ስለኾነ ነው። እነዚኽን ሁሉ ኹነቶች በነፃ እንደ ተቋም ሥንሠራ ድንቡሎ ሳንቲም እገዛ ያደረገልን ከደጋፊዎቻችን ይኹን ከነቃፊዎቻችን መሐል እኔ አለሁ የሚል የለም። ሌሎች ኹነቶች ላይ ሠርተን በምናገኘው እንጂ። ለበጎ ሥራችን ሺልማት ባንጠብቅም ነቀፋን ግን ለሰከንድ አልጠበቅንም። ስለሁሉም ነገር እናመሰግናለን። አገልግሎታችን በብዙ እጥፍ ተደራጂቶ እንደሚቀጥል ቃል እንገባላችኋለን።

2. ሥራዎችን እና አገልግሎቶችን እንዴት ይቀበላል?

አንድን ተግባር ለማከናወን ሃሳብ ያላቸው ኮሚቴዎች እና ግለሰቦች በጊዜ እጥረት፣ በቦታ ርቀት፣ በልምድ ማነስ ምክንያት ኹነታቸው እክል ሳይገጥመው ማዘጋጀት ሲፈልጉ ወደ ተቋማችን ይመጣሉ። በዚህ መሠረት ይኽንን ተግባር አከናውኑልን ሲሉ የጉዳዩን ሕጋዊነት ካጠናን እና ከመረመርን በኋላ በድርጅታችን ውስጣዊ አሠራር መሠረት መክፈል የማይችሉትን ያለምንም ክፍያ በነፃ እንሠራላቸዋለን። በዚኽም በርካታ ኹነቶችንም በነፃ ሠርተናል። ለወደፊትም እንሠራለን። መክፈል የሚችሉ ግለሰቦች እና ተቋማት ደግሞ ይከፍላሉ። ለዚኽም ሕጋዊ ደብዳቤ እንዲጽፉ አድርገን ቆጥረው የሰጡንን ተግባራት በንጽሕና፣ በጥራት እና በፍጥነት ቆጥረን እናስረክባለን።

ድካማቸውን ደክመን ሸክማቸውን ተሸክመን እናገለግላቸዋለን። ለዚኽም እሰከ ዛሬ ያገለገልናቸው ግለሰቦች፣ ኮሚቴዎች፣ ማኅበራት፣ ገዳማት፣ አድባራት፣ ሀገረ ስብከቶች ምስክሮቻችን ናቸው። ስለኾነም ከደንበኞቻችን በርካታ የምስጋና እና የምስክር ወረቀቶች ተበርክተውልናል።

3. ክፍያን በተመለከተ
ሀ) . በፐርሰንት ወይም በኮሚሽን በፍፁም ሠርተን አናውቅም። ለወደፊትም አንሠራም። ይኽን የማናደርገው ወንጀልም ኃጢአትም ስለኾነ ሳይኾን ከተሐድሶ እንቅስቃሴ ቀጥሎ ለቤተክርስቲያን ቀጣዩ ፈተና ነው ብለን ስለምናምን ነው። በዚኽ ምክንያት እኛ ወደዚኽ አገልግሎት ከመግባታችን በፊት በኮሚሽን ወይም በፐርሰንት ሲሠሩ የነበሩ ግለሰቦችን እና ተቋማትን በማስተማር፣ በመገሰጽ ከድርጊታቸው እንዲታቀቡ አድርገናል። 99 % ተሳክቶልናል። 1% የሚኾኑ በዚኽ አቋማችን ያኮረፉም የእኛን ጩኽት ቀምተው ቀን ጠብቀው ከውስጥ እና ከውጭ ተባብረው ዘመቻ ከፍተውብናል። እኛ ግን በዘመቻ የሚንበረከክ ተቋማዊ ውቅር ስሌለን አገልግሎታችንን በንጽሕና እንቀጥላለን።

ሎዛ ኹነቶችን በተመለከተ አንድም ግለሰብ አንድም ተቋም በፐርሰንት የሠራንበትን ማስረጃም መረጃም ማቅረብ አይችልም። በፍፁም፣ በፍፁም፣ በፍፁም። እንደ ግለሰብም እንደተቋምም እንደዚኽ ዐይነት ስብእና እንደሌለን ብዙዎቻችኹ ታውቃላችኹ። የማታውቁንም እንድትጠይቁ በእግዚአብሔር ስም አደራ እንላለን።

ለ.) የመንግሥት ግብር፣ የቢሮ ኪራይ፣ የሠራተኞች ደሞዝ እንዴት ትከፍላላችኹ? ብሎ አዝኖልን የጠየቀን የለም፤ ስንት ግዙፍ ሥራዎችን ገንዘብ ከኪሳችን ጭምር እያወጣን በነፃ ስንሠራ ያላዘኑ፤ ያልጠየቁ፤ ምን እንርዳችኹ? እንዴት አናግዛችኹ ብለው አጠገባችን ያልነበሩ፤ ለዲኮር እና መሰል ጉዳዮች በሚሊዬን ደረጃ ሲከፈል ኮሚቴ ኹነው በሚሠሩበት ቦታ ዝም ያሉ፤ ለቴሌቪዥን ጣቢያዎቻችን ለአንድ ደቂቃ ማስታወቂያ እና ለአንድ ዶክመንተሪ ስንት እንደሚከፈል የሚያውቁ መርጦ አልቃሾች እና ግለሰቦች ዘመቻ ሲከፈቱብን ግን ሳያመዛዝኑ ግራ ቀኝ ሳይጠይቁ ለመፍረድ እና ለመሳደብ ብሎም የሚሸማቀቅ የለም እንጂ ለማሸማቀቅ የቀደማቸው የለም።

ተቋማችን ግን ለግለሰቦች እና ለተቋማት የሚሰጠው አገልግሎት እና ሥራ በተቋሙ አሠራር መሠረት ተመጣጣኝ ክፍያ ያስከፍላል። መክፈል የቻሉ ይከፍላሉ። ምክንያቱም የቢሮ ኪራይ፣ የስቱዲይ ዕቃዎች ኪራይ፣ የሠራተኞች ደሞዝ እና ልዩ ልዩ ወጭዎችን የምንሸፍነው ከጠቅላይ ቤተክህነት በተመደብልን በጀት አይደለም።

የምትሠሩት ለሀገር እና ለቤተክርስቲያን ነው ብሎ መንግሥት በጀት አይመድብልንም። አንድም በጎ አድራጊም አንድ ብር ሰጥቶን አያውቅም። መክፈል ያልቻሉ ግለሰቦች እና ተቋማት ደግሞ በአሠራራችን መሠረት በነፃ ያለምንም ክፍያ አገልግሎት ይሰጣቸዋል። በዚኽም በርካታ ተቋማት እና ግለሰቦች ተጠቃሚ ኾነዋል። በነፃ ያለምንም ክፍያ የሠራንላቸው ግለሰቦችን እና ተቋማትን ዝርዝራቸው በመጨረሻ ተመልከቱ። በዕውነት ነገሩ በጣም ያሳዝናል።

የሰሞኑን የስም ማጥፋት ዘመቻ የትኩረት ነጥቦች
1).ሎዛ ኹነቶች አዘጋጅ በኮሚሺን ወይም በፐርሰንት እየሠራ ነው የሚል ነው። መልሳችን በፍፁም ውሸት ነው የሚል ነው። አልሠራንም ነው። ሠርተንም አናውቅም። አንሠራምም። ጭራሺ በፐርሰንት የሚሠሩ ግለሰቦች ላይ ከፍተኛ ተቃውሞ አለን። ነገሩ ጩኽቴን ቀሙኝ ነው። ሠርተዋል የሚል ካለ ባለቤቱ ወጥቶ አዎ ከእኔ ጋር ሠርተዋል ይበል። ወሬ ሳይኾን የሚነበብ ማኅተም ፊርማ፣ ሕጋዊ ውል እና ስምምነት ይዞ ይምጣ። 100% የምንነግራችኹ፤ አንድም ተቋም አንድም ግለሰብ ከሎዛ ኹነቶች ጋር በፐርሰንት ወይም በኮሚሽን በፍፁም አሠርቻለኹ ብሎ አይመጣም። ምክንያቱም እንደዚኽ ዐይነት ሥራ መሥራት ተገቢ ነው ብለን ስለማናምንበት፤ አልሠራንም። ምስክሮቻችን እስከዛሬ አብረውን የሠሩ ግለሰቦች እና ተቋማት ናቸው

2. ማኅበራዊ ሚዲያ ላይ እየተዘዋወረ ባለው ዶክመንት ጉዳይ፦

ሀ.) ዶክመንቱ ኹነቱ የተዘጋጀው ከህዳር 12 እሰከ ህዳር 26/2018 ይላል። ሎዛ ኹነቶች በዚኽ በተባለው ቀን በፍፁም ሐዋሳ ላይ ኹነቶችን አላዘጋጀም።

ለ). ዶክመንቱ እኛን ባይመለከተንም ሰዎች ልከውልን ተመልክተነዋል። በዚኽም እንደ አንድ ኦርቶዶክሳዊ እና እንደ አንድ ሕሊና ባላቸው ሰዎች እንደሚመራ ተቋም በጥንቃቄ ለማየት ሞክረናል። በመኾኑም በርካታ የሐሰት ውንጀላዎች ተካተውበታል።ብዙ ውሸቶችንም ይዟል።

ጥቂቶቹ
ሐ), ማነው ይኼ ደብር? ኹነቱን ማን ነው ያስተባበረለት? የውል ስምምነታቸው የትአለ? ስምምነቱስ ምን ይላል? ደብሩ በግልፅ መግለጫ ለምን አልሰጠም? ደብሩ ተበደልኩ ለምን አላለም? የተበደለውስ ምንድን ነው? የማይነበብ ማኅተም ለምን ማዘዋወር ተፈለገ? ምእመናን ነገሩ እየገባችኹ ነው? በሳል አእምሮ ያለው ይጠይቅ። በዝርዝር በስም ተጠቅሶ ለማን ምን ተከፈለ? ገንዘብ የተቀበሉበት ፊርማ ወዘተ አለ? ክፍያውስ የተፈጸመው ያለገለገሉበትን ነው ወይስ ያላገለገሉበትን? ያልሠሩበትን ነው ወይስ እንደተባለው ዘርፈው ነው? አስገድደው ነው? ኮሚቴው ፈቅዶ እና አምኖበት ነው ያደረገው? አምኖበት ካደረገው በኋላስ ለምን ሚዲያ ላይ ማሠራጨት አስፈለገ? እውነት ከኾነ ዶክመንቱን ሙሉውን ለምን አለቀቁትም። ለምን ቆረጧት? ሰው ይኼን እንዴት መጠየቅ ያቅተዋል? የምጣዱ እያለ የእንቅቡ ተንጫጫ ለምን እንዲኾን ተፈለገ ዓላማው ሌላ ስለኾነ ነው።

መ) ቲክቶከሮቹን ማጥቃት የፈለገ አካል መኖሩን ማሳያ የዘማርያን የሰባኪያን አበል የታለ? መርሐግብሩ የተካኼደው ያለዘማርያን ነው? ውሸት፤

ሠ) አምስት መቶ ምናምን ሺ ብር ምግብ እንዴት? ፍፁም ውሸት። እውነት እንኳን ቢኾን አገልጋዮቹ እዚህ ሆቴል ካልኾነ አንተኛም ብለው ነው? ውሸት። መጀመሪያውኑ ወጪ የሚቀንስ ምግብ፣ ወጪ የሚቀንስ ምኝታ ለምን አላዘጋጁም? አገልጋዮቹ እና ሚዲያዎቹ እዚህ አንተኛም። ይኽንን አንበላም እንደማይሉ የታወቀ ጉዳይ ነው። ምክንያቱም አገልግሎቱ ሐዋሳ ብቻ አይደለም። ብዙ ቦታወች ተሰጧል። የጎላ ድስት ወጥ በልተው፣ ሰ/ት/ቤት አዳራሽ ተኝተው ጥንቅቅ ያለ መርሐግብር አዘጋጅተዋል።

ረ). ወጪ ለማጋነን የተቀሰጡ ወጪዎች አሉ ለምን? ለምሳሌ ቁጥር 2 ለመወንጀል ከመጣደፋቸው የተነሣ በትክክል እንኳ መደመር አልቻሉም።

3. ዶክመንቱ እኛን የማይመለከተን ኾኖ ሳለ የሎዛ ኹነቶችን ስም በዚኽ መጠን ማጥፋት ለምን አስፈለገ? ዘመቻውን ያስጀመሩት አካላት እነማን ናቸው? ዓላማቸውስ ምንድን ነው? የሚለውን መመረመር ያስፈልጋል።

ሀ). የመጀመሪያዎቹ በፍፁም ቅንነት ለቤተክርስቲያን ያሰቡ መስሏቸው የተንጋደደ መረጃ ሰምተው ዘመቻውን የተቀላቀሉ ናቸው። ለእናንተ መልሳችን ሕሊና የሚባል ነገር አለ አጣሩ። ነግ በኔ በሉ። ሰው የዘራውን ነው የሚያጭደው። ቢያንስ ጉዳዩን ከኹለቱም ወገን ስሙ። ከዚያም መፍረድ የሚያስችል መንፈሳዊነት፣ ሞራል እና ስነልቡና ካላችኹ ፍረዱ። ሕጋዊ መረጃ እና ማስረጃ ሳትይዙ የግለሰብ ስም እና የተቋም ስም ከሚያጠፉ ሰዎች ጋር አትተባበሩ። ቆም ብላችኹ ጠይቁ። ቢያንስ ከሳሽ ሳይኖር ተካሣሽ ላይ አትፍረዱ። አሁን እየኾነ ያለው ሕጋዊ ከሳሺ እና ወቃሺ ሳይኖር አሯሯጮች መኾን አይገባንም።

ለ.) የአእላፋትን ዝማሬ ቲክቶከሮቹ ይደግፋሉ የሚል ነው። ስለዚኽ በሏቸው ነው። ቲክቶከሮቹን የሚያስተባብረው ደግሞ ሎዛ ኹነቶች ነው። እርሱንም በሉት
ሐ. እንደነዚኽ ዐይነት መርሐግብር ለምን አልተሳተፍንም የሚል ውስጣዊ ቅናት ያንገበገባቸው ናቸው። እንዚህ አካላት ደግሞ ያልተጋበዙት የኮሚቴዎቹ ምርጫ ስላልኾኑ። በቦታ ርቀት። ስልክ ስለማያነሱ። በብዙ ምክንያት ሳይጋበዙ የቀሩ። ነገሩ ትክክል ስለኾነ ስላልኾ ሳይኾነ እነሱ ስለሌሉበት። እነሱ ስላልጀመሩት። እነሱ ቡራኬ ስላልሰጡበት ነው።

መ). ወቅታዊ አጀንዳ ለማስቀየር። ይኽ ጉዳይ በሚነሣበት ወቅት ምን ዐይነት አጀንዳ ይናፈስ ነበር የሚለውን መፈተሽ ተገቢ ነው።

ሠ.) ምእመናን አገልጋዮችን፣ ኦርቶዶክሳዊ ዩቱበሮቹን፣ ቲክቶከሮቹን፣ ፊስቡከሮችን እና የኪነጥበብ ባለሙያውችን እንዲጠሉ፤ እንዲጠራጠሩ። አይይ ምን ሰው አለ? በማስባል ፈተና ውስጥ በማስገባት ለክህደት ጉዞ ማመቻቸት ነው፤

ረ). ዝናን፣ ዕይታን እና ገንዘብን ናፋቂነት ነው። ስም ያላቸውን ሰዎች ያለበቂ ምክንያት ያለ ሕጋዊ መረጃ እና ማስረጃ ፎሎወር እና ሰበስክራይበር ለመጨመር ትኩረት ለመሳብ ስም ያላቸው ሰዎች ማወረድ ትናንት የነበረ። ዛሬም እየኾነ ያለ። ለወደፊትም የሚቀጥል እኩይ ተግባር ነው። ለእነዚኽ አካላት መልሳችን የሚኾነው፤ ውሾች ይጮኻሉ፤ ግመሎችም ይኼዳሉ ነው::

በሙገሳ ብዛት የሚቀጥል አገልግሎት የለንም። በተራ ስም ማጥፋት የሚገታ ሥራ አይኖረንም። እኛ ሠናይ ዓላማ አለን። ዓላማችን ደግሞ ያለፈተና እንደማይሳካም ጠንቅቀን ስለምናውቅ ጉዟችን ወደፊት ነው።

ሰ.) አንዳንድ ተመሣሣይ ሥራ እና አገልግሎት የሚሠጡ አካላት ተቋማችን እያገኘ ባለው ስም እና ዝና ምክንያት ደስተኞች እንዳልኾኑ እናውቃለን። ኾኖም መጠላለፉ አይጠቅምም። ብፁዕ አቡነ ጎርጎርዮስ ሥራህን ሥራ እንዳሉት ኹላችን በሥራችን እንገለጥ ነው መልሳችን።

ሸ. ) የሰይጣን ሥራ ነው፤ ምክንያቱም እየሠራነው ያለው መንፈሳዊ አገልግሎት እና ሥራ ነው። መንፈሳዊ ሥራ ደግሞ ያለፈተና አይሠራም። ፈተና ከሌለውም ቅድመ እግዚአብሔር አልደረሰም ይላሉ አበው። ይኽንን ፈተና በብዙ መልኩ ለምደነዋል። ደግሞም በድል አቁሞናል። ዐቢያተ ክርስቲያናት እየታነፁ ነው፤ አብነት ት/ቤቶች እየተገነቡ ነው፤ ወንጌል እየተስፋፋ ነው። ዝማሬው እየቀለጠ ነው። በዚኽ ያልተበሳጨ ሰይጣን በምን ይበሳጭ? እንዲያውም ይኽ ፈተና መምጣቱን እግዚአብሔር አገልግሎታችን እንደተቀበለልን እንቆጥረዋለን።

ቀ.) እንደሚታወቀው በርካታ ገዳማት፣ አድባራት፣ አብነት ት/ቤቶች ፣ ማኅበራት፣ ሰ/ት/ቤቶች፣ የነዳያን መርጃ ተቋማት፣ ግለሰቦች ይኽንን አገልግሎት ይፈልጉታል። በዚኽ አገልግሎትም ወንጌል ስለሚስፋፋ፣ ድኾች ስለሚረዱ፣ አድባራት እና ገዳማት ስለሚታነፁ፤ ይኽ እንቅስቃሴ እና አገልግሎት ደግሞ አንዳንድ የቅባት፣ የተሐድሶ አራማጆችን ያስቆጣል። አስቆጥቷል። የመናበባቸው ምስጢርም ይኼው ነው። ስለዚኽ ጥያቄው በእነሱ ስም ማጥፋት ዘመቻ አገልግሎቱን እና ሥራውን እናቁመው ወይስ እንቀጥለው ነው? ጉዳዩ፤ አናቆምም ነው መልሳችን።

4. ለሚያገለግሉን ግለሰቦች እና ተቋማት ደም ወዝ መክፈል ነውር ነው ወይ? ክፍያ መፈጸም ኃጢአት ነው ወይ?
የሚችል እና ሌላ መተዳደሪያ ያለው በነፃ ያገልግል። የማይችል ግን ራሱን እና ቤተሰቡን የሚያስተዳድርበት ዋጋው ሊከፈለው ይገባል። ቤተክርስቲያን ያስተማረችንም ይኽው ነው። ቅዱስ ፓትርያርኩ፣ ጳጳሳቱ፣ መነኮሳቱ፣ ካህናቱ፣መምህራኑ፣ ዘማርያኑ፣ ወዘተረፈ በምን የሚተዳደሩ ይመስላችኋል? ከአንዳንድ ቦታወችና አባቶች ውጪ ምእመናን በሚሰጡት ገንዘብ ነው። ከመንግሥት ቀጥሎ ሚሊየኖችን ቀጥራ ደሞዝ ከፍላ የምታሠራ ለብዙዎች የሥጋም የነፍስም መጠጥና ምግብ የኢ/ኦ/ተ/ቤ ን ናት። ዘዳግም 25፡4 "እህል የማያበራየውን በሬ አፉን አትሠር " ተብሎ ተጽፏል። ቅዱስ ጳውሎስም "እግዘብሔርን ስለበሬዎች ይገድዋልን?"1ኛ ቆሮ 9፥9 ፤ ስለአገልጋዩ ነው ወዳጄ። ቀጥሎ ጳውሎስ "ለሠራተኛ ደሞዙ ይገባዋል" ይላል። ሠራተኛ ይዝረፍ አይልም። ይስረቅ አይልም።

ለሠራተኛ ዋጋው ይገባዋል ነው ያለው። እኛ ሠርቀው የሚበሉትን እንጂ ሠርተው የሚበሉትን አንቃወምም። ሠርቀዋል ካላችኹ ማስረጃ አምጡ። ነገር ግን ማስረጃ የላችኹም። ስም ማጥፋት ብቻ ከኾነ ግን በሥጋም በነፍስም ከተጠያቂነት አናመልጥም።

5. ቲክቶከሮችን እና ዩቱበሮችን በተመለከተ
አንድ ዓለማዊ ቲክቶከር ለአንድ ማስታወቂያ ስንት ነው የሚከፈለው? አንድ ዶክመንተሪ ለመሥራት በዓለማውያን ስንት ይጠየቃል? በራሳችን ሰዎች ላይ ምን ያህል ጨካኝ እንደኾንን የገባን ለኦርቶዶክሳውያን ለቲክቶከር እና ዩቱበር ለምን ይከፈላል? ብለን የስም ማጥፋት ዘመቻውን ስናሟሙቀው ያየነው ዕለት ነው። ሠርቀዋል? ውሸት። መረጃ የለም። ዘርፈዋል? ውሸት መረጃ የለም።

ተከፍሏቸው በንጽሕና ሠርተው ከኾነ ምንድን ነው ኅጢአቱ? ቤተክርስቲያኑ
ሢሠራ፣ ቀለሙ ሲቀባ፣ አጥሩ ሲታጠር ይኽን የሠሩት ሰዎች የሌላ ዕምነት ተከታዮች ናቸው? በብዛት አይደሉም። ኦርቶዶክሳውያን ተቋራጮች፣ መሐንዲሶች፣ ግንበኞች፣ ቀለም ቀቢዎች፣ ኤሌክትሪሻኖች ናቸው።

ለእነዚኽ ሁሉ ከፍለን አሠርተን፤ ለዩቱበር እና ለቲክቶከር ሲኾን ለምን ተበሳጨን ብለን ስንጠይቅ መልሱ ጨካኞች ስለኾንን ነው። እነሱም የቤት ኪራይ አለባቸው። እነሱም የቢሮ ኪራይ አለባቸው። እነሱም የካሜራ ማን ደሞዝ አለባቸው። እነሱም ኮ ሰው ናቸው እንደኛ ይበላሉ ይጠጣሉ። እነሱም የሞባይል ካርድ ይፈልጋሉ። እነሱም በክንፋቸው አይበሩም ትራንስፖርት ይፈልጋሉ። እንደ ዓለማውያኑ ቲክቶከሮች አንበሳ እና አበባ እየተሰጣቸውአይደለም የሚገለግሉት የሚታሠሩት የኛዎቹ ቲክቶከሮች፣ የሚሰደዱት ኦርቶዶክሳውያን ቲክቶከሮች፣ ከመናፍቅ እና ከተሐድሶ ጋር አንገት ለአንገት የሚተናነቁት መንፈሳዊ ቲክቶከሮች፤ ምን አድርጉ ነው የምንላቸው? ለምን የሁለት ዓለም ስደተኞች እናደርጋቸዋለን?

ሠርቶ የሚበላን መደገፍ፤ ሠርቆ የሚበላን መንቀፍ ተገቢ ነው። ስለመስረቃቸው አንድ ማስረጃ የለም። ካለ እንኳን ግለሰቡን መጠየቅ እንጂ በስመ ቲክቶከር ሁሉንም መጨፍጨፍ ተገቢ አይደለም። ክርስትናም አይደለም።

በመጨረሻ የእኛን ንጽሕና እና የተቋማችን የአገልግሎት ተደራሽነት የምታውቁ ሥራችን ለሁሉ ይደረስ ዘንድ ጸልዩልን። የማታውቁን ጠይቁ። እያወቃችኹ በክፋት እና በምቀኝነት ለተነሣችኹብን የምንላችኹ ሶሻል ሚዲያ ፍርድ ቤት አይደለም። መረጃ እና ማስረጃ ይዛችኹ ክሠሡን። ያኔ ውርደታችኹን ትከናነባላችኹ። ደስ የሚለው አትከሥሡንም። ምክንያቱም ወሬ እንጂ ፍሬ የላችኹም። ምክንያቱም መረጃ እንጂ ማስረጃ የላችኹም። ምክንያቱም ሠርቆ መብላት እንጃ ሠርቶ መብላት ወንጀል ስላልኾነ። ምክንያቱም አገልግሎ መቀበል መጽሐፍ ቅዱሳዊ እንጂ ኃጢአት ስላልኾነ። እናም ክሠሡን። ያኔ የእናንተ ትክክለኝነት ይታያል።

በቀጣይም በሀገር ውስጥ ተቀምጠው ስማችንን ጠቅሰው የተቋማችንን ስም እና ክብር ያጎደፉትን ግለሰቦች በሕግ የምንጠይቅ ይኾናል። ከሀገር ውጭ ያሉትን በተመለከተ ዋነኛ ተዋናዮች እንደኾኑ እናውቃለን። እዚህ ያሉትም ስደቡልን አዋርዱልን እያሉ የሚልኩትም ውጪ ላሉት ነው። እነሱም በቅርበት እንደማይገኙ ቢከሠሡም ፍርዳቸው ሩቅ እንደኾነ ስለሚያውቁ ለእግዚአብሔር እናመለክታለን።

በቅርበት እኛንም ተቋማችንም የምታውቁ በተፈጠረው የሐሰት ፕሮፓጋንዳ ሳትበገሩ እሰከ መጨረሻው በጸሎታችኹም በሃሳባችኹም አብራችኹን ለነበራችኹ ወዳጆቻችንን እና የአገልግሎት ተጠቃሚወቻችን ቀን አይታችኹ ስላልተሸራተታችኹ፤ ጩኽት ፈርታችኹ ስላልከዳችኹን እናመሰግናለን። ክርስትና ይኽ ነው። በሆሳዕና ዕለትም በዕለተ አርብም አብሮ መቆም። የሚያስከፍለውን ዋጋ ከፍሎ ነፃ መውጣት። እናመሰግናለን ።

5 months ago

No replys yet!

Be the first to share what you think — your comment will appear here.