Logo
YenetaTube
የምትሠሩት ለሀገር እና ለቤተክርስቲያን ነው ብሎ መንግሥት በጀት አይመድብልንም። አንድም በጎ አድራጊም አንድ ብር ሰጥቶን አያውቅም። መክፈል ያልቻሉ ግለሰቦች እና ተቋማት ደግሞ በአሠራራችን መሠረት በነፃ ያለምንም ክፍያ አገልግሎት ይሰጣቸዋል። በዚኽም በርካታ ተቋማት እና ግለሰቦች ተጠቃሚ ኾነዋል። በነፃ ያለምንም ክፍያ የሠራንላቸው ግለሰቦችን እና ተቋማትን ዝርዝራቸው በመጨረሻ ተመልከቱ። በዕውነት ነገሩ በጣም ያሳዝናል።

የሰሞኑን የስም ማጥፋት ዘመቻ የትኩረት ነጥቦች
1).ሎዛ ኹነቶች አዘጋጅ በኮሚሺን ወይም በፐርሰንት እየሠራ ነው የሚል ነው። መልሳችን በፍፁም ውሸት ነው የሚል ነው። አልሠራንም ነው። ሠርተንም አናውቅም። አንሠራምም። ጭራሺ በፐርሰንት የሚሠሩ ግለሰቦች ላይ ከፍተኛ ተቃውሞ አለን። ነገሩ ጩኽቴን ቀሙኝ ነው። ሠርተዋል የሚል ካለ ባለቤቱ ወጥቶ አዎ ከእኔ ጋር ሠርተዋል ይበል። ወሬ ሳይኾን የሚነበብ ማኅተም ፊርማ፣ ሕጋዊ ውል እና ስምምነት ይዞ ይምጣ። 100% የምንነግራችኹ፤ አንድም ተቋም አንድም ግለሰብ ከሎዛ ኹነቶች ጋር በፐርሰንት ወይም በኮሚሽን በፍፁም አሠርቻለኹ ብሎ አይመጣም። ምክንያቱም እንደዚኽ ዐይነት ሥራ መሥራት ተገቢ ነው ብለን ስለማናምንበት፤ አልሠራንም። ምስክሮቻችን እስከዛሬ አብረውን የሠሩ ግለሰቦች እና ተቋማት ናቸው

2. ማኅበራዊ ሚዲያ ላይ እየተዘዋወረ ባለው ዶክመንት ጉዳይ፦

ሀ.) ዶክመንቱ ኹነቱ የተዘጋጀው ከህዳር 12 እሰከ ህዳር 26/2018 ይላል። ሎዛ ኹነቶች በዚኽ በተባለው ቀን በፍፁም ሐዋሳ ላይ ኹነቶችን አላዘጋጀም።

ለ). ዶክመንቱ እኛን ባይመለከተንም ሰዎች ልከውልን ተመልክተነዋል። በዚኽም እንደ አንድ ኦርቶዶክሳዊ እና እንደ አንድ ሕሊና ባላቸው ሰዎች እንደሚመራ ተቋም በጥንቃቄ ለማየት ሞክረናል። በመኾኑም በርካታ የሐሰት ውንጀላዎች ተካተውበታል።ብዙ ውሸቶችንም ይዟል።

ጥቂቶቹ
ሐ), ማነው ይኼ ደብር? ኹነቱን ማን ነው ያስተባበረለት? የውል ስምምነታቸው የትአለ? ስምምነቱስ ምን ይላል? ደብሩ በግልፅ መግለጫ ለምን አልሰጠም? ደብሩ ተበደልኩ ለምን አላለም? የተበደለውስ ምንድን ነው? የማይነበብ ማኅተም ለምን ማዘዋወር ተፈለገ? ምእመናን ነገሩ እየገባችኹ ነው? በሳል አእምሮ ያለው ይጠይቅ። በዝርዝር በስም ተጠቅሶ ለማን ምን ተከፈለ? ገንዘብ የተቀበሉበት ፊርማ ወዘተ አለ? ክፍያውስ የተፈጸመው ያለገለገሉበትን ነው ወይስ ያላገለገሉበትን? ያልሠሩበትን ነው ወይስ እንደተባለው ዘርፈው ነው? አስገድደው ነው? ኮሚቴው ፈቅዶ እና አምኖበት ነው ያደረገው? አምኖበት ካደረገው በኋላስ ለምን ሚዲያ ላይ ማሠራጨት አስፈለገ? እውነት ከኾነ ዶክመንቱን ሙሉውን ለምን አለቀቁትም። ለምን ቆረጧት? ሰው ይኼን እንዴት መጠየቅ ያቅተዋል? የምጣዱ እያለ የእንቅቡ ተንጫጫ ለምን እንዲኾን ተፈለገ ዓላማው ሌላ ስለኾነ ነው።

መ) ቲክቶከሮቹን ማጥቃት የፈለገ አካል መኖሩን ማሳያ የዘማርያን የሰባኪያን አበል የታለ? መርሐግብሩ የተካኼደው ያለዘማርያን ነው? ውሸት፤

ሠ) አምስት መቶ ምናምን ሺ ብር ምግብ እንዴት? ፍፁም ውሸት። እውነት እንኳን ቢኾን አገልጋዮቹ እዚህ ሆቴል ካልኾነ አንተኛም ብለው ነው? ውሸት። መጀመሪያውኑ ወጪ የሚቀንስ ምግብ፣ ወጪ የሚቀንስ ምኝታ ለምን አላዘጋጁም? አገልጋዮቹ እና ሚዲያዎቹ እዚህ አንተኛም። ይኽንን አንበላም እንደማይሉ የታወቀ ጉዳይ ነው። ምክንያቱም አገልግሎቱ ሐዋሳ ብቻ አይደለም። ብዙ ቦታወች ተሰጧል። የጎላ ድስት ወጥ በልተው፣ ሰ/ት/ቤት አዳራሽ ተኝተው ጥንቅቅ ያለ መርሐግብር አዘጋጅተዋል።

ረ). ወጪ ለማጋነን የተቀሰጡ ወጪዎች አሉ ለምን? ለምሳሌ ቁጥር 2 ለመወንጀል ከመጣደፋቸው የተነሣ በትክክል እንኳ መደመር አልቻሉም።

3. ዶክመንቱ እኛን የማይመለከተን ኾኖ ሳለ የሎዛ ኹነቶችን ስም በዚኽ መጠን ማጥፋት ለምን አስፈለገ? ዘመቻውን ያስጀመሩት አካላት እነማን ናቸው? ዓላማቸውስ ምንድን ነው? የሚለውን መመረመር ያስፈልጋል።

ሀ). የመጀመሪያዎቹ በፍፁም ቅንነት ለቤተክርስቲያን ያሰቡ መስሏቸው የተንጋደደ መረጃ ሰምተው ዘመቻውን የተቀላቀሉ ናቸው። ለእናንተ መልሳችን ሕሊና የሚባል ነገር አለ አጣሩ። ነግ በኔ በሉ። ሰው የዘራውን ነው የሚያጭደው። ቢያንስ ጉዳዩን ከኹለቱም ወገን ስሙ። ከዚያም መፍረድ የሚያስችል መንፈሳዊነት፣ ሞራል እና ስነልቡና ካላችኹ ፍረዱ። ሕጋዊ መረጃ እና ማስረጃ ሳትይዙ የግለሰብ ስም እና የተቋም ስም ከሚያጠፉ ሰዎች ጋር አትተባበሩ። ቆም ብላችኹ ጠይቁ። ቢያንስ ከሳሽ ሳይኖር ተካሣሽ ላይ አትፍረዱ። አሁን እየኾነ ያለው ሕጋዊ ከሳሺ እና ወቃሺ ሳይኖር አሯሯጮች መኾን አይገባንም።

ለ.) የአእላፋትን ዝማሬ ቲክቶከሮቹ ይደግፋሉ የሚል ነው። ስለዚኽ በሏቸው ነው። ቲክቶከሮቹን የሚያስተባብረው ደግሞ ሎዛ ኹነቶች ነው። እርሱንም በሉት
ሐ. እንደነዚኽ ዐይነት መርሐግብር ለምን አልተሳተፍንም የሚል ውስጣዊ ቅናት ያንገበገባቸው ናቸው። እንዚህ አካላት ደግሞ ያልተጋበዙት የኮሚቴዎቹ ምርጫ ስላልኾኑ። በቦታ ርቀት። ስልክ ስለማያነሱ። በብዙ ምክንያት ሳይጋበዙ የቀሩ። ነገሩ ትክክል ስለኾነ ስላልኾ ሳይኾነ እነሱ ስለሌሉበት። እነሱ ስላልጀመሩት። እነሱ ቡራኬ ስላልሰጡበት ነው።

መ). ወቅታዊ አጀንዳ ለማስቀየር። ይኽ ጉዳይ በሚነሣበት ወቅት ምን ዐይነት አጀንዳ ይናፈስ ነበር የሚለውን መፈተሽ ተገቢ ነው።

ሠ.) ምእመናን አገልጋዮችን፣ ኦርቶዶክሳዊ ዩቱበሮቹን፣ ቲክቶከሮቹን፣ ፊስቡከሮችን እና የኪነጥበብ ባለሙያውችን እንዲጠሉ፤ እንዲጠራጠሩ። አይይ ምን ሰው አለ? በማስባል ፈተና ውስጥ በማስገባት ለክህደት ጉዞ ማመቻቸት ነው፤

ረ). ዝናን፣ ዕይታን እና ገንዘብን ናፋቂነት ነው። ስም ያላቸውን ሰዎች ያለበቂ ምክንያት ያለ ሕጋዊ መረጃ እና ማስረጃ ፎሎወር እና ሰበስክራይበር ለመጨመር ትኩረት ለመሳብ ስም ያላቸው ሰዎች ማወረድ ትናንት የነበረ። ዛሬም እየኾነ ያለ። ለወደፊትም የሚቀጥል እኩይ ተግባር ነው። ለእነዚኽ አካላት መልሳችን የሚኾነው፤ ውሾች ይጮኻሉ፤ ግመሎችም ይኼዳሉ ነው::

በሙገሳ ብዛት የሚቀጥል አገልግሎት የለንም። በተራ ስም ማጥፋት የሚገታ ሥራ አይኖረንም። እኛ ሠናይ ዓላማ አለን። ዓላማችን ደግሞ ያለፈተና እንደማይሳካም ጠንቅቀን ስለምናውቅ ጉዟችን ወደፊት ነው።

ሰ.) አንዳንድ ተመሣሣይ ሥራ እና አገልግሎት የሚሠጡ አካላት ተቋማችን እያገኘ ባለው ስም እና ዝና ምክንያት ደስተኞች እንዳልኾኑ እናውቃለን። ኾኖም መጠላለፉ አይጠቅምም። ብፁዕ አቡነ ጎርጎርዮስ ሥራህን ሥራ እንዳሉት ኹላችን በሥራችን እንገለጥ ነው መልሳችን።

ሸ. ) የሰይጣን ሥራ ነው፤ ምክንያቱም እየሠራነው ያለው መንፈሳዊ አገልግሎት እና ሥራ ነው። መንፈሳዊ ሥራ ደግሞ ያለፈተና አይሠራም። ፈተና ከሌለውም ቅድመ እግዚአብሔር አልደረሰም ይላሉ አበው። ይኽንን ፈተና በብዙ መልኩ ለምደነዋል። ደግሞም በድል አቁሞናል። ዐቢያተ ክርስቲያናት እየታነፁ ነው፤ አብነት ት/ቤቶች እየተገነቡ ነው፤ ወንጌል እየተስፋፋ ነው። ዝማሬው እየቀለጠ ነው። በዚኽ ያልተበሳጨ ሰይጣን በምን ይበሳጭ? እንዲያውም ይኽ ፈተና መምጣቱን እግዚአብሔር አገልግሎታችን እንደተቀበለልን እንቆጥረዋለን።

ቀ.) እንደሚታወቀው በርካታ ገዳማት፣ አድባራት፣ አብነት ት/ቤቶች ፣ ማኅበራት፣ ሰ/ት/ቤቶች፣ የነዳያን መርጃ ተቋማት፣ ግለሰቦች ይኽንን አገልግሎት ይፈልጉታል። በዚኽ አገልግሎትም ወንጌል ስለሚስፋፋ፣ ድኾች ስለሚረዱ፣ አድባራት እና ገዳማት ስለሚታነፁ፤ ይኽ እንቅስቃሴ እና አገልግሎት ደግሞ አንዳንድ የቅባት፣ የተሐድሶ እና የምንፍቅና አራማጆችን ያስቆጣል። አስቆጥቷል። የመናበባቸው ምስጢርም ይኼው ነው። ስለዚኽ ጥያቄው በእነሱ ስም ማጥፋት ዘመቻ አገልግሎቱን እና ሥራውን እናቁመው ወይስ እንቀጥለው ነው? ጉዳዩ፤ አናቆምም ነው መልሳችን።

4. ለሚያገለግሉን ግለሰቦች እና ተቋማት ደም ወዝ መክፈል ነውር ነው ወይ? ክፍያ መፈጸም ኃጢአት ነው ወይ?
የሚችል እና ሌላ መተዳደሪያ ያለው በነፃ ያገልግል። የማይችል ግን ራሱን እና ቤተሰቡን የሚያስተዳድርበት ዋጋው ሊከፈለው ይገባል። ቤተክርስቲያን ያስተማረችንም ይኽው ነው። ቅዱስ ፓትርያርኩ፣ ጳጳሳቱ፣ መነኮሳቱ፣ ካህናቱ፣መምህራኑ፣ ዘማርያኑ፣ ወዘተረፈ በምን የሚተዳደሩ ይመስላችኋል? ከአንዳንድ ቦታወችና አባቶች ውጪ ምእመናን በሚሰጡት ገንዘብ ነው። ከመንግሥት ቀጥሎ ሚሊየኖችን ቀጥራ ደሞዝ ከፍላ የምታሠራ ለብዙዎች የሥጋም የነፍስም መጠጥና ምግብ የኢ/ኦ/ተ/ቤ ን ናት። ዘዳግም 25፡4 "እህል የማያበራየውን በሬ አፉን አትሠር " ተብሎ ተጽፏል። ቅዱስ ጳውሎስም "እግዘብሔርን ስለበሬዎች ይገድዋልን?"1ኛ ቆሮ 9፥9 ፤ ስለአገልጋዩ ነው ወዳጄ። ቀጥሎ ጳውሎስ "ለሠራተኛ ደሞዙ ይገባዋል" ይላል። ሠራተኛ ይዝረፍ አይልም። ይስረቅ አይልም።

ለሠራተኛ ዋጋው ይገባዋል ነው ያለው። እኛ ሠርቀው የሚበሉትን እንጂ ሠርተው የሚበሉትን አንቃወምም። ሠርቀዋል ካላችኹ ማስረጃ አምጡ። ነገር ግን ማስረጃ የላችኹም። ስም ማጥፋት ብቻ ከኾነ ግን በሥጋም በነፍስም ከተጠያቂነት አናመልጥም።

5. ቲክቶከሮችን እና ዩቱበሮችን በተመለከተ
አንድ ዓለማዊ ቲክቶከር ለአንድ ማስታወቂያ ስንት ነው የሚከፈለው? አንድ ዶክመንተሪ ለመሥራት በዓለማውያን ስንት ይጠየቃል? በራሳችን ሰዎች ላይ ምን ያህል ጨካኝ እንደኾንን የገባን ለኦርቶዶክሳውያን ለቲክቶከር እና ዩቱበር ለምን ይከፈላል? ብለን የስም ማጥፋት ዘመቻውን ስናሟሙቀው ያየነው ዕለት ነው። ሠርቀዋል? ውሸት። መረጃ የለም። ዘርፈዋል? ውሸት መረጃ የለም።

ተከፍሏቸው በንጽሕና ሠርተው ከኾነ ምንድን ነው ኅጢአቱ? ቤተክርስቲያኑ
ሢሠራ፣ ቀለሙ ሲቀባ፣ አጥሩ ሲታጠር ይኽን የሠሩት ሰዎች የሌላ ዕምነት ተከታዮች ናቸው? በብዛት አይደሉም። ኦርቶዶክሳውያን ተቋራጮች፣ መሐንዲሶች፣ ግንበኞች፣ ቀለም ቀቢዎች፣ ኤሌክትሪሻኖች ናቸው።

ለእነዚኽ ሁሉ ከፍለን አሠርተን፤ ለዩቱበር እና ለቲክቶከር ሲኾን ለምን ተበሳጨን ብለን ስንጠይቅ መልሱ ጨካኞች ስለኾንን ነው። እነሱም የቤት ኪራይ አለባቸው። እነሱም የቢሮ ኪራይ አለባቸው። እነሱም የካሜራ ማን ደሞዝ አለባቸው። እነሱም ኮ ሰው ናቸው እንደኛ ይበላሉ ይጠጣሉ። እነሱም የሞባይል ካርድ ይፈልጋሉ። እነሱም በክንፋቸው አይበሩም ትራንስፖርት ይፈልጋሉ። እንደ ዓለማውያኑ ቲክቶከሮች አንበሳ እና አበባ እየተሰጣቸውአይደለም የሚገለግሉት የሚታሠሩት የኛዎቹ ቲክቶከሮች፣ የሚሰደዱት ኦርቶዶክሳውያን ቲክቶከሮች፣ ከመናፍቅ እና ከተሐድሶ ጋር አንገት ለአንገት የሚተናነቁት መንፈሳዊ ቲክቶከሮች፤ ምን አድርጉ ነው የምንላቸው? ለምን የሁለት ዓለም ስደተኞች እናደርጋቸዋለን?

ሠርቶ የሚበላን መደገፍ፤ ሠርቆ የሚበላን መንቀፍ ተገቢ ነው። ስለመስረቃቸው አንድ ማስረጃ የለም። ካለ እንኳን ግለሰቡን መጠየቅ እንጂ በስመ ቲክቶከር ሁሉንም መጨፍጨፍ ተገቢ አይደለም። ክርስትናም አይደለም።

በመጨረሻ የእኛን ንጽሕና እና የተቋማችን የአገልግሎት ተደራሽነት የምታውቁ ሥራችን ለሁሉ ይደረስ ዘንድ ጸልዩልን። የማታውቁን ጠይቁ። እያወቃችኹ በክፋት እና በምቀኝነት ለተነሣችኹብን የምንላችኹ ሶሻል ሚዲያ ፍርድ ቤት አይደለም። መረጃ እና ማስረጃ ይዛችኹ ክሠሡን። ያኔ ውርደታችኹን ትከናነባላችኹ። ደስ የሚለው አትከሥሡንም። ምክንያቱም ወሬ እንጂ ፍሬ የላችኹም። ምክንያቱም መረጃ እንጂ ማስረጃ የላችኹም። ምክንያቱም ሠርቆ መብላት እንጃ ሠርቶ መብላት ወንጀል ስላልኾነ። ምክንያቱም አገልግሎ መቀበል መጽሐፍ ቅዱሳዊ እንጂ ኃጢአት ስላልኾነ። እናም ክሠሡን። ያኔ የእናንተ ትክክለኝነት ይታያል።

በቀጣይም በሀገር ውስጥ ተቀምጠው ስማችንን ጠቅሰው የተቋማችንን ስም እና ክብር ያጎደፉትን ግለሰቦች በሕግ የምንጠይቅ ይኾናል። ከሀገር ውጭ ያሉትን በተመለከተ ዋነኛ ተዋናዮች እንደኾኑ እናውቃለን። እዚህ ያሉትም ስደቡልን አዋርዱልን እያሉ የሚልኩትም ውጪ ላሉት ነው። እነሱም በቅርበት እንደማይገኙ ቢከሠሡም ፍርዳቸው ሩቅ እንደኾነ ስለሚያውቁ ለእግዚአብሔር እናመለክታለን።

በቅርበት እኛንም ተቋማችንም የምታውቁ በተፈጠረው የሐሰት ፕሮፓጋንዳ ሳትበገሩ እሰከ መጨረሻው በጸሎታችኹም በሃሳባችኹም አብራችኹን ለነበራችኹ ወዳጆቻችንን እና የአገልግሎት ተጠቃሚወቻችን ቀን አይታችኹ ስላልተሸራተታችኹ፤ ጩኽት ፈርታችኹ ስላልከዳችኹን እናመሰግናለን። ክርስትና ይኽ ነው። በሆሳዕና ዕለትም በዕለተ አርብም አብሮ መቆም። የሚያስከፍለውን ዋጋ ከፍሎ ነፃ መውጣት።

እናመሰግናለን ።

6 months ago

No replys yet!

Be the first to share what you think — your comment will appear here.