Logo
FIDEL POST NEWS
የኢትዮጵያ አደጋ ስጋት ሥራ አመራር የቀድሞ ኮሚሽነር ምትኩ ካሳ በተከሰሱበት ከባድ የሙስና ወንጀል ጥፋተኛ ሆነው በመገኘታቸው በ13 ዓመት ጽኑ እስራት ተቀጥተዋል።

የፍትሕ ሚኒስቴር የሙስና ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ዐቃቤ ሕግ ፤ በኮሚሽኑ የተረጂዎችን ቁጥር በማጋነን የተለያዩ የእርዳታ ዓይነቶችን ከመጋዘን ወጪ በማድረግ ለተረጂዎች ሳይደርስ ተሽጦ ለግል ጥቅም መዋሉን ገልጿል።

በዚህም በሕገ ወጥ መንገድ የተገኘ ገንዘብን ወይም ንብረትን ምንጩን ደብቆ ሕጋዊ አስመስሎ ማቅረብ ወንጀል ክስ በነሐሴ ወር 2014 ዓ.ም ተመስርቶባቸው እንደነበር አመልክቷል።

የቀረበው የክስ ዝርዝር ምን ይዟል ?

ኤልሻዳይ ሪሊፍ ኤንድ ዴቭሎፕመንት አሶሴሸን ዳይሬክተር የማነ ወ/ማሪያምና ከሌሎች ሰራተኞች ጋር ያልተገባ የጥቅም ግንኙነት በመፍጠር በሺዎች በሚቆጠሩ ተረጂዎች ስም እንዲሁም የተረጂዎችን ቁጥር በማጋነን ለበርካታ ጊዜ የምግብ ቁሳቁሶች ከኮሚሽኑ መጋዘን በማውጣት ለዱቄት ፋብሪካዎችና ለሌሎች ግለሰቦች #በመሸጥ ሕገወጥ ጥቅም ሲያገኙ ነበር።

በአማራ፣ አፋር፣ ኦሮሚያ፣ ደቡብ ክልል (የቀድሞ) ክልሎች ውስጥ በሚገኙ የግብረሰናይ ድርጅቱ (ኤልሻዳይ) ማዕከላት ለተረጂዎች ሳያደርስ በመሸጥ ለግል ጥቅም ማዋል፣ ብድርና ድጋፍ በሚል ሰበብ በሕገ ወጥ መንገድ ከኮሚሽኑ #በ100_ሚሊየን የሚገመት ለእርዳታ ድርጅቱ በገንዘብ መልክ ተሰጥቷል።

ለዚህም በአቶ ምትኩ ካሳ ቤተሰቦች ስም ከኤልሻዳይ ድርጅት በተለያዩ ጊዜ ክፍያ ተፍጽሟል።

በተለይም ፦
- ከ601 ሺህ ኩንታል በላይ ስንዴ፣
- ከ41 ሺህ ኩንታል በላይ በቆሎ፣
- ከ78 ሺህ ሊትር በላይ ዘይት፣
- ከ3 ሺህ 999 ኩንታል በላይ ሩዝ ከተራድኦ ድርጅቱና ከኮሚሽኑ ጋር በመመሳጠር እርዳታውን አዳማ ለሚገኝ የዱቄት ፋብሪካ ተሽጧል።

በሌላ ክስ ደግሞ ከ472 ነጥብ 8 ሚሊየን ብር በላይ በድጋፍ መልክ በ1ኛ ተከሳሽ አቶ ምትኩ ካሳ ፈቃጅነት በ2ኛ ተከሳሽ አማካኝነት ክፍያ እንደተፈጸመና በ3ኛ ተከሳሽ ወጪ አድራጊነት ለግል ጥቅም በመዋሉ በመንግስት ከፍተኛ ኪሳራ ደርሷል።

በአቶ ምትኩ ልጆችና ባለቤታቸው ስም ተገዝተው የተገኙ ተሽከርካሪዎችና መኖሪያ ቤቶች ተገኝተዋል።

ተከሳሾቹ አቶ ምትኩ ካሳ፣ ባለቤታቸው ወ/ሮ ሶፊያ ጀማል፣ ልጃቸው ወ/ሮ ሚልካ ምትኩ የወንጀል ድርጊት መፈፀማቸውን ተከትሎ የጥፋተኝነት ውሳኔ ተላልፏል፡፡

የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 5ኛ የሙስና ጉዳዮች ችሎት የዐቃቤ ሕግን የቅጣት ማክበጃና የተከሳሾችን የቅጣት ማቅለያ ካደመጠ በኋላ አቶ ምትኩ ካሳ በ13 ዓመት ጽኑ እስራትና በ50 ሺህ ብር የገንዘብ መቀጮ እንዲቀጡ ወስኗል፡፡

በተጨማሪም በአቶ ምትኩ ካሳ ባለቤት ወ/ሮ ሶፊያ ጀማል ላይ የ8 ዓመት ከ4 ወር እስራትና 3 ሺህ ብር የገንዘብ መቀጮ እንዲቀጡ ወስኗል።

ልጃቸው ወ/ሮ ሚልካ ምትኩ 5 ዓመት እስራትና 3 ሺህ ብር የገንዘብ መቀጮ እንዲቀጡ ውሳኔ አስተላልፏል።

FMC
8 months ago

No replys yet!

Be the first to share what you think — your comment will appear here.