Logo
Getu Temesgen
ስለ ድሆች ጠበቃ “ንገርልኝ”
#ethiopia | ኢየሱስ በዮሐንስ ወንጌል ምዕራፍ አራት ላይ አንዲትን የሳምራዊት ሴት በያዕቆብ የውሃ ጉድጓድ አጠገብ ተቀምጦ እንዳገኛት እና ከተጠማችው ምድራዊ ውሃ በላይ የህይወትን ውሃ እንደሰጣት መጽሐፍ ቅዱስ ይነግረናል፤

ልክ እንዲሁ ለስጋ የሆነ የውሃ ጥማቸውን በገጠር እና በከተማ የውሃ ጉድጓድ በመቆፈር የበርካቶችን ጥም ያረካው፣ በእነዚያ የውሃ ጉድጓዶች አማካኝነት ለበርካቶች የህይወትን ውሃ ሲያካፍል የኖረው፣ የባሌው ፍሬ፣ የኢትዮጵያ ጉባኤ እግዚአብሔር ቤተ ክርስቲያን መስራች 3 መጋቢዎች መካከል አንዱ፣ ለአገሩ በጎ ፈቃድ አምባሳደር፣ የድሆች ጠበቃ እና የብዙዎች መካሪ መንፈሳዊ አባት መጋቢ ከተማ ክንፈ ዛሬ ወደ ሚወደው እና ወዳገለገለው ጌታ በክብር ተሸኘቷል።

የተከበሩ ታገሰ ጫፎ (የኢ.ፌ.ዲ.ሪ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባኤ)፣ አምባሳደር አሰፋ ዲንጋሞ (በኩባ የኢ.ፌ.ዲ.ሪ ልዩ መልክተኛ እና ባለሙሉ ስልጣን አምባሳደር) መጋቢ ጻድቁ አብዶ (የኢትዮጵያ ወንጌላውያን አብያተ ክርስቲያናት ኅብረት ፕሬዝዳንት)፣ የመጋቢ ከተማ ቤተሰቦች፣ ከፍተኛ የመንግስት የሥራ ኃላፊዎች፣ የቤተ እምነት እና የአጥቢያ መሪ መጋቢዎች፣ የቅርብ ወዳጆች እና ቤተሰቦች ድንጋጤ እና ከፍተኛ የሃዘን ድባብ ተላብሰው 6 ኪሎ በምትገኘው የጉባኤ እግዚአብሔር ቤተ ክርስቲያን ከቀኑ 5:00 ሰዓት ላይ ተሰባስበዋል።

“መጽሐፍ ቅዱስ አታልቅሱ የሚል ነገር የለውም፤ ይልቁንም ተስፋ እንደሌላቸው ሰዎች አታልቅሱ ነው የሚለው” በማለት ከእንባ ጋር እየታገሉ ቃለ እግዚአብሔር ያካፈሉት የመጋቢው የቅርብ ወዳጅ መጋቢ ጻድቁ አብዶ “ድንኳን የሚሆነው ምድራዊ መኖሪያችን ቢፈርስ፥ በሰማይ ያለ በእጅ ያልተሠራ የዘላለም ቤት የሚሆን ከእግዚአብሔር የተሠራ ሕንጻ እንዳለን እናውቃለንና።” የሚለውን የ2ቆሮ ምዕራፍ 5 ቃል በማንሳት ክርስቲያን ዘላለማዊ ተስፋ እንዳለው አጽንኦት ሰጥተዋል፤

በመልዕክታቸውም መካከል በድንገተኛ የልብ ህመም ከአጠገባቸው ስለ ተነጠቁት መጋቢ ከተማ ክንፈ አስታውሰው ናይሮቢ በምስራቅ አፍሪካ ስነመለኮት ኮሌጅ በጋራ ሲማሩ እንደተዋወቁ በማንሳት በተለይም እንደ ጉባኤ እግዚአብሔር ያሉ ቤተ እምነቶች መጋቢ ከተማ የጀመረውን መንፈሳዊ እና የልማት በጎ አድራጎት አገልግሎቶች ከማስቀጠል አንጻር ሊተጉ እንደሚገባችው ተናግረዋል።

“በተለይ ያለፉትን 6 ዓመታት እንደ መካሪ አባቴ አብሮኝ ከስሬ በመሆን ብዙ ፕሮጀክቶችን እንድ ጀምር ምክንያት የሆነኝ እርሱ ነበር” ሲሉ በእንባ ንግግራቸውን የጀመሩት የኢትዮጵያ ጉባኤ እግዚአብሔር ቤተ ክርስቲያን ፕሬዝዳንት መጋቢ አያንሳ ኦብሲ “መጋቢ ከተማ የበርናባስ መንፈስ ያለበት ብዙ ወጣት መሪዎች ወደ ፊት እንዲወጡ የሰራ ሰው ነው” ሲሉ ገልጸዋል፤ አክለውም “በእርሱ አገልግሎት እኔ እንኳን ሳውቅ ከ620 በላይ የውሃ ጉድጓዶች ተቆፈረዋል፤ በተለይም የኢትዮጵያ ጉባኤ እግዚአብሔር ቤተ ክርስቲያን ወሎ ሰፈር አጥቢያ እንድትመሰረት መጋቢ ከተማ ያደረገው ጉልህ ድርሻ አይረሴ ነው” ብለውናል።

“ህዝብ በተሰበሰበበት ያውም በሃዘን ስፍራ ላይ እንኳን ሳይቀር ተናግሮ የሚያስቅ፣ ፈገግታን መፍጠር የሚችል ግሩም አባት ነበረኝ፤ እኔ እንደሱ አይደለሁም፤ ይቅር በሉኝ” በማለት ስለ ወላጅ አባቱ በሽኝት መርሃ ግብሩ ላይ የተናገረው ሙዘቀኛ ዳዊት ከተማ “እስካሁን በህልም እንጂ እውነት አልመስል ብሎኛል” ብሎ ታዳሚውን አስለቅሶታል፤

ዳዊት ሲናገር “አባቴ በቤት ውስጥ ወላጅ አባቴ፤ በስራ ቦታ ደግሞ አለቃዬ ነበር፤ አብሬው በተጓዝኩባቸው ስፍራዎች ሁሉ ደከመኘ ሲል ሰመቼው አላውቅም፤ በውሃ ጥም ሲቸገር በነበረ ማኅበረሰብ መካከል አንድ የውሃ ጉድጓድ ሲቆፈር የሚፈጠረውን ደስታ የሚያውቅ ሰው ዛሬ እዚህ መካከል አባቴ አርፎ ሲመለከት ተረጋግቶ መቆም ይችል እንደሆነ እጠራጠራለሁ” በማለት ሃዘኑን የሚጋሩ በርካቶች መሆናቸውን ተናግሯል።

“ንገርልኝ” በሚል ርዕስ ሃዘኗን ግጥም ጽፋ ከሚኒሶታ የላከቸው የመጋቢ ከተማ ሴት ልጅ “ሃብት ሰው መሆኑን አስተምሮን እንዳለፈ ንገርልኝ” ስትል በግጥም መልዕክቷን አድርሳለች።

መጋቢ ከተማ የአፍሪካ ዳይሬክተር በመሆን እያገለገሉበት ከቆዩበት ወርልድሰርቭ ዓለም አቀፍ (WorldServe International) ተወክለው የዓለም አቀፍ ቢሮ መልዕክት ያቀረቡት የወርልድሰርቭ ዓለም አቀፍ የኬኒያ ቢሮ ዳይሬክተር መጋቢ ዴቪድ ካንጌቴ “መጋቢ ከተማ ጌታን አውቆ ደግሞ ጌታን ሰብኮ የሄደ ሰው ነው፤ ስለዚህ አትረበሹ ጌታን አውቀው የሞቱ ሁሉ ይነሳሉ” ሲሉ መልዕክታቸውን አድርሰዋል፣ መጋቢ ከተማንም ሲያስታውሱ “እግዚአብሔር ዳዊትን እንደ ልቤ እንዳለ ለእኔ መጋቢ ከተማ ለእግዚአብሔር እንደዛ ያለ ሰው እንደሆነ አስባለሁ” ብለዋል።

የፕሪዝን ሚኒስትሪ እና የጀስቲስ ፎር ኦል ዳይሬክተር መጋቢ ዳንኤል ገብረስላሴ ወዳጅ ጓደኞቹን ወክለው ባደረጉት ንግግር “መጋቢ ከተማ በእርግጥም የድሃ ጠበቃ ነበር፤ መጋቢ ከተማ በስራ እና በአገልግሎት ያገኘውን ዓለም አቀፍ ግንኙነት ለአገሩ በጎ ፈቃድ አምባሳደር በመሆን ተጠቅሞበታል፤ በተለይም እርቅ በሚያስፈልጋቸው በርካታ የአገራችን አካባቢዎች ልምዱን እና የነበረውን መልካም ስም በመጠቀም እርቀ ሰላም እንዲወርድ በበርካታ ቦታዎች ላይ ለእርቅ የሰራ ሰው ነበር” ሲሉ ገልጸዋል።

መጋቢ ከተማ በኢትዮጵያ እንዲመሰረት ያደረጉት እና በዳይሬክተርነት ከሚመሩት ኤል ኤም ኢንተርናሽናል (LM International) ለዚሁ የሽኝት መርሃ ግብር አገር አቋርጠው የተገኙት ወንድም ኤንደርሶን “መጋቢ ከተማ ጥሩ ታሪክ ተናጋሪ ሰው ነበር፤ በአንድ ወቅት ብዙ ልምድ እያለው እኔ ገና ብዙም ልምድ ሳይኖረኝ አለቃው በመሆን አብሬው ሰርቻለሁ፤ በዚህም አንድ ወቅት እንዴት እንዲህ ለመስራት ትችላልህ ስል ላቀረብኩለት ጥያቄ መጋቢ ከተማ ‘መልሱ ቀላል ነው አንተ ትመራልህ እኔ እከተላለሁ’ ሲል እውነተኛ አገልጋይ መሪነቱን አሳይቶኛል” ብለዋል።

“ከ27 ዓመታት በፊት ወደ አዲስ አበባ ስመጣ ካገኘኋቸው መጋቢዎች መካከል አንዱ መጋቢ ከተማ ነበር” ያሉት የaptea executive director መጋቢ ዶ/ር ዳግ “ጸጋን የተሞላ፣ ፍቅርን የተላበሰ እና ይቅርታን የሚያውቅ ግሩም ሚሲዮናዊ ነበር፤ እሱ ባለበት ሁሉ ደስታ እና ሃሴት አለ፤ በእርሱ የተነሳ ከበርካታ ሚሲዮናውያን የሃዘን መልዕክት እየተቀበልን ነው፤ አሁን መጋቢ ከተማ የለኮሰውን የወንጌል ችቦ ሁላችን ተቀብለን ሰዎች ሁሉ ይህንን ወንጌል እስኪሰሙ ድረስ የጀመረውን ስራ እናስቀጥል” የሚል ጥሪ አቅርበዋል።

የሽኝት መርሃ ግብሩን በጸሎት ያስጀመሩት የጉባኤ እግዚአብሔር 6ኪሎ አጥቢያ ዋና መሪ የሆኑት ሐዋርያ መርጊያ አብዲሳ ናቸው።

በመጨረሻም የኢትዮጵያ ጉባኤ እግዚአብሔር ቤተ ክርስቲያን ምክትል ፕሬዝዳንት መጋቢ ወይሳ ቱራይሎ መጋቢ ከተማ በተለይ ወደ መንፈሳዊ ህይወት ከመጡበት የናይሮቢ ቲካ ስደተኞች ጣቢያ ጀመሮ አሁን ድረስ በኢትዮጵያ ከተሞች እና ገጠር ከተሞች ሳይቀር በውሃ፣ በትምህርት ቤት ግንባታ እና በምግብ ራስን በማስቻል ያደረጉትን በጎ አስተዋጽኦ ከእንባ ጋር በማካፈል የመርሃ ግቡ ፍጻሜ የሆነ ሲሆን መጋቢ ከተማ ወደ መንፈሳዊ እና የበጎ አድራጎት ሥራ ከመሰማራታቸው በፊት በኢትዮጵያ አየር ሃይል ግሩም የሆኑ ግራውንድ ቴክንሺያን እንደነበሩ እና በተለይ በኬኒያ ቲካ ስደተኞች ካምፕ ለነበሩ ለበካቶች አባት እንደነበሩ ተጠቅሷል።

መጋቢ ዐቢይ ታደለ (ኪያ)
ኤክሌሲያ ሚዲያ /ECCLESIA MEDIA/

6 months ago

No replys yet!

Be the first to share what you think — your comment will appear here.