Logo
YenetaTube
በደሞዝ ጭማሪ ሰበብ ሕገወጥ ድርጊት ላይ የተሳተፉ ከ39 ሺህ በላይ ነጋዴዎች ርምጃ ተወሰደባቸው

የደሞዝ ጭማሪን ሰበብ አድርገው ሕገወጥ ድርጊት ላይ የተሳተፉ ከ39 ሺህ በላይ ነጋዴዎች ርምጃ እንደተወሰደባቸው የአማራ ክልል ንግድና ገበያ ልማት ቢሮ አስታወቀ።

የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ንግድና ገበያ ልማት ቢሮ ከደሞዝ ጭማሪ ጋር ተያይዞ እየተስተዋለ ያለውን የዋጋ ንረት እና ቀጣይ ርምጃዎችን አስመለክቶ መግለጫ ሰጥቷል።

የቢሮው ኃላፊ ኢብራሂም ሙሀመድ (ዶ/ር) በሰጡት መግለጫ እንዳስታወቁት፤ የደሞዝ ጭማሪን ተከትሎ የሚመጣን የዋጋ ንረት ለመከላከል የክትትልና ቁጥጥር ሥራዎች ተጠናክረዋል።

በዚህም የደመወዝ መጨመርን እንደ ሰበብ በመጠቀም የዋጋ ንረት እንዲመጣ ባደረጉ ነጋዴዎች ላይ ከቀላል እስከ ከባድ ርምጃ ተወስዷል ብለዋል።

በተደረገ የክትትል እና የቁጥጥር ስራም የደሞዝ ጭማሪን ሰበብ አድርገው ሕገወጥ ድርጊት ላይ የተሳተፉ ከ39 ሺህ በላይ ነጋዴዎች ርምጃ መወሰዱን አብራርተዋል።

ያለ አግባብ ዋጋ በጨመሩ፣ ምርት በደበቁ እና የምርት ጥራት አጓድለው ለገበያ ባቀረቡ ከ39 ሺህ በላይ ነጋዴዎች ከቀላል እስከ ከባድ ርምጃ ተወስዷል ብለዋል።

ህዝቡን ለምርት እጥረት ለመዳረግ ብሎም የዋጋ ንረትን ለመጨመር የተንቀሳቀሱ 380 የሚሆኑ ነጋዴዎች ምርት ደብቀው የተገኙ መሆናቸውን ጠቅሰው፤ በነጋዴዎቹ ላይ ርምጃ መወሰዱን ተናግረዋል።

ከ26 ሺህ በላይ የሚሆኑት ደግሞ የዋጋ ዝርዝር ያልለጠፉ፣ ያለ አድራሻ የነገዱ እና መሰል ችግር የታየባቸው ነጋዴዎች መሆናቸውን ገልፀዋል።

በተመሳሳይ ከህዝብ ጤንነት ይልቅ ያለአግባብ መበልፀግ እና ማደግ የጣሩ 1 ሺህ 169 ህገወጥ ነጋዴዎች ምርትን ከባእድ ነገር ጋር ቀላቅለው ለሽያጭ የቀረቡ መሆናቸውን ጠቁመው፤ በነዚህ ነጋዴዎች ላይ አስፈላጊው የእርምት ርምጃ መወሰዱን አብራርተዋል።

በተጨማሪም 1 ሺህ 778 የሚሆኑ ነጋዴዎች ትክክለኛ ያልሆኑ መለኪያ መሳሪያዎችን በመጠቀም ህዝቡን ሲያጭበረብሩ እና ሲበዘብዙ ብሎም ላልተገባ የኑሮ ውድነት እየዳረጉ እንደተገኙና የማስተካከያ ርምጃ እንደተወሰደባቸው አብራርተዋል።

ንግድን ዘመናዊ፣ ተወዳዳሪ፣ ተደራሽ እና ፍትሀዊ ለማድረግ የግብይት እና የንግድ ስርዓቱ በቴክኖሎጂ መደገፍ አለበት በሚል ሰፊ ስራ እየሰሩ መሆኑን ጠቅሰዋል።

በዚህም የነዳጅ ሽያጭ፣ የንግድ ፈቃድና እድሳት፣ የገበያ መረጃ እና የምርት ትስስር ሂደቱን በቴክኖሎጂ በተደገፈ መንገድ እየሰሩ መሆኑን ተናግረዋል።

በክልሉ 352 ሺህ ነጋዴዎች የሚገኙ መሆኑን ጠቅሰው፤ ከነዚህ ውስጥ ንግድ ፈቃድን ባወጡበት ስራ እየሰሩ መሆናቸውን ለማረጋገጥ በ278 ሺህ ነጋዴዎች ላይ የበር ለበር ፍተሻ በማድረግ ክትትልና ቁጥጥር ተደርጓል ብለዋል።

ህጋዊ ነጋዴዎችም ሆነ ህብረተሰቡ ህገወጥ የንግድ ስርአትን በማውገዝ ህጋዊ የንግድ ስርዓትን በማበረታታት የበኩሉን እገዛ ማድረግ አለበት በማለት ጥሪ አስተላልፈዋል።
#ጋዜጣፕላስ

6 months ago

No replys yet!

Be the first to share what you think — your comment will appear here.