Logo
Getu Temesgen
" አሁን ያለባቸውን ችግር በራስ አቅም ይፍቱ " - የሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን
#ethiopia | የደመወዝ ማሻሻያው በወቅቱ በሁሉም አካባቢዎች ለምን ተፈጻሚ መሆን እንዳልቻለ ማብራሪያ እንዲሰጥ የሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን ተጠይቋል።

ኮሚሽኑ ጥያቄውን የተጠየቀው ዛሬ የሶስት ወር የስራ ክንውን ሪፖርቱን ለህዘብ ተወካዮች ም/ቤት የሰው ሃብት ልማት ስራ ሰምሪት እና ቴክኖሎጂ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ባቀረበበት ወቅት ነው፡፡

የቋሚ ኮሚቴውን ጥያቄ ያቀረቡት ወ/ሮ ጀማነሽ ወ/ሚካኤል ፤ የደመወዝ ማሻሻያው መልካም መሆኑን ጠቅሰው " ክፍያው እስከ ጥቅምት አጋማሽ እንዲከፈል ቢታዘዝም እስካሁን የደመወዝ ማሻሻያ ያልደረሳቸው አካባቢዎች አሉ " ብለዋል።

ስራ እንዳይስተጓገል በሁሉም ደረጃ ለምን በወቅቱ የደመወዝ ማሻሻያው ተፈጻሚ መሆን አልቻለም ? ሲሉ ጠይቀዋል፡፡

ለጥያቄዎቹ መልስ የሰጡት የሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር ጌታቸው ጀምበር (ዶ/ር) በደመወዝ ክፍያው ላይ ለተስተዋለው ችግር ክልሎችን ተጠያቂ አድርገዋል።

አስቀድሞ የፌዴራል መንግስት ደመወዝ ማሻሻያ ሊሰራ ሲል የሰራው በቀድሞ መረጃ መሰረት መሆኑን ተናግረው ማሻሻያ የተሰራው ክልሎች በሰጡት መረጃ መሰረት ነው ብለዋል።

አንዳንድ ክልሎች ማሻሻያው ከተሰራ በኋላ " ያንሰናል " የሚል ቅሬት በደብዳቤ እና በአካል ማቅረባቸውን ያስረዱት ምክትል ኮሚሽነሩ " ከአንዳንድ የክልል ፕሬዝዳንቶች ጋር በጉዳዩ ላይ ተነጋግናል ችግሩም የእኛ ሳይሆን የእነሱ መሆኑን ተማምነናል " ሲሉ ተናግረዋል።

ችግሩ በስፋት የተፈጠረው በቀድሞ ደቡብ ክልል ስር በነበሩ ክልሎች መሆኑን አስታውሰው " እኛ ማሻሻያ የሰራነው ከሰኔ 2016 ዓ.ም በፊት በቅጥር ላይ ላሉ ሰራተኞች ነው " ብለዋል።

ከዚያ ወዲያ ለነበሩ ሰራተኞች ቅጥር ኮሚሽኑ እንደማይመለከተው ተናግሮ አሁን ያለባቸውንም ችግር " በራስ አቅም ይፍቱ " ሲሉ ተናግረዋል።

ምንም እንኳን የሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን ችግሩ ከክልሎች እንጂ ከኮሚሽኑ እንዳልሆነ ቢገልጽም ሰራተኞች ደመወዙ እንዲከፈላቸው የክትትል ስራ እንደሚሰራ መግለጹን ሸገር ኤፍ ኤም 102.1 ሬድዮ ጣቢያ ዘግቧል።

9 months ago

No replys yet!

Be the first to share what you think — your comment will appear here.