Logo
Getu Temesgen
ስመ ጥሩ የሚድያ ሰው መርዕድ በቀለ በአትላንታ አረፈ

. በደርግ ጊዜ የማስታወቂያ ምክትል ሚኒስትር ነበር

ከዕዝራ እጅጉ (ተወዳጅ ሚድያ)
#ታሪክ በኢትዮጵያን ሄራልድ፣በየዛሬይቱ ኢትዮጵያ ጋዜጦች፣እንዲሁም በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት በመምሪያ ኃላፊነት ያገለገለው አቶ መርዕድ በቀለ ትናንት ህዳር 4 2018 በአትላንታ ህይወቱ ማለፉ ተሰምቷል።

የደርግ ዘመን ማብቂያ ላይ የማስታወቂያ ምክትል ሚኒስትር የነበረው የሚድያ ሰው አቶ መርዕድ በሥነ ፅሁፍ ችሎታው የተመሠከረለት ነበር። የሕይወት ታሪኩ የአማርኛ ኢንሳይክሎፒዲያ "መዝገበ አእምሮ ቅፅ ሁለት ላይ የሰፈረለት አቶ መርዕድ በቀለ በ2016 በተደረገው የክብር ሽልማት የህይወት ዘመን ተሸላሚዎች ከእጩዎቹ አንዱ ነበር።

አቶ መርዕድ ተወዳጅ ሚድያ የሚያከናውናቸውን የስነዳ ሥራዎች የሚደግፍ ፣ የሚያበረታታ የቅርብ ሰው ሲሆን በህልፈቱም የተሰማንን ሀዘን እንገልጻለን። የካቲት 26 2018 ሲመጣ 80 ዓመቱን ይይዝ የነበረው አቶ መርዕድ ከሰዎች ጋር በቀላሉ የሚግባባ እና የፅሑፍ ሥራንም በጥንቃቄ የሚያከናውን ነበር። እኛም የህይወት ታሪኩን እንደሚከተለው እናቀርባለን።

ትውልድ እና ልጅነት

መርዕድ በቀለ በ1938 ዓ.ም. የካቲት 26 ቀን አዲስ አበባ ቀጨኔ መድኃኔዓለም ቤተ ክርስቲያን አካባቢ ተወለደ። አባቱ አቶ በቀለ ወ/ኪዳን የአብነት ትምህርት ቤት ገብቶ የቤተ ክርስቲያን ትምህርት እንዲማር ፍላጎቱ ቢኖራቸውም፣ እናቱ ወ/ሮ ጽጌ ወርቅ ተክለ ጻዲቅ ግን ልጃቸው ከአጠገባቸው እንዳይርቅ በማሰብ በቤት ውስጥ መምህር ቀጥረው ፊደል ከቆጠረ በኋላ በአካባቢው በነበረው የየኔታ ትምህርት ቤት ገባ።

ትምህርት

በኋላም በአምኃ ደስታ የአንደኛ፣ በዳግማዊ ምኒልክ ትምህርት ቤት ደግሞ የኹለተኛ ደረጃ ትምህርቱን አጠናቀቀ። አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ገብቶ በውጭ ቋንቋዎች እና ሥነጽሑፍ በእንግሊዘኛ ቋንቋ በ1965 ዓ.ም. ተመረቀ።

ወደ ሥራ ዓለም

በዚያው ዓመት ነበር በቀድሞው ልዩ ካቢኔ ቢሮ በታላቁ ቤተመንግሥት ውስጥ የተቀጠረው። ልዩ ካቢኔ በነበረበት ወቅትም ዋና ሥራው ከተለያዩ የዓለም ዜና ምንጮች (Reuters, AFP, BBC… ወዘተ) ከሚሠራጩ ዜናዎች ውስጥ የተመረጡትን እየተረጎመ በአለቃው በኩል ለንጉሡ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ማቅረብ ነበር። ሆኖም በዚህ ሥራ ከሦስት ሳምንት በላይ አልዘለለም።

በወቅቱ የማስታወቂያ ሚኒስቴር ለኢትዮጵያን ሄራልድ እንግሊዘኛ ጋዜጣ የሪፖርተር ቅጥር ያወጣውን ፈተና አልፎ፥ የማታ ኤዲተር ሆኖ ሥራ ጀመረ። ብዙም ሳይቆይ ወደ ቀን ተዘዋወረ።

የህትመት ሚድያ

መርዕድ በ1967 ዓ.ም. ባገኘው የትምህርት ዕድል ወደ ሞስኮ አቅንቶ ነበር። በዚያም ለአንድ ዓመት ስለ ሶሻሊዝም ፅንሰ ሐሳብ ካጠና በኋላ ወደ አገሩ ተመልሶ በዚያው በኢትዮጵያን ሄራልድ በአዘጋጅነት ለተወሰኑ ዓመታት አገልግሏል። ቀጥሎም ወደ “የዛሬይቱ ኢትዮጵያ” ጋዜጣ በዋና አዘጋጅነት ዕድገት አግኝቶ እንዲሠራ ተደረገ። ብዙም ሳይቆይ ወደ አዲስ ዘመን ዕለታዊ ጋዜጣ በዕድገት ተዛውሮ በምክትል ዋና አዘጅነት ለኹለት ዓመታት ከሠራ በኋላ ዋና አዘጋጅ ሆኖ እንዲሠራ ተመደበ።

ከኢዜአ እስከ ምክትል ሚኒስትር

በሥራው ባሕርይ የተነሣ መርዕድ በተደጋጋሚ ‘‘ለጥያቄ ትፈለጋለህ’’ እየተባለ ወደ ደርግ ጽሕፈት ቤት ይጠራ ነበር። እንደ እኤአ 1975/76 ሁለት የደኅንነት ሰዎች ከመሥሪያ ቤቱ መጥተው ወደ ማዕከላዊ እስር ቤት ወሰዱት። ሁኔታው ነገሩ ለሕይወቱ እንደሚያሰጋው በመገንዘብ ከቦታው እንዲዛወር አለቃው የነበረውን ደራሲ በዓሉ ግርማን ደጋግሞ ይጠይቅ፣ ይወተውትም ጀመር። ውትወታው ተቀባይነት አግኝቶ በዕድገት የሕዝብ ግንኙነት መምሪያ ሐላፊ ሆኖ ተዛወረ፡፡ እዚያ ለአንድ ዓመት እንደቆየ፥ የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት መምሪያ ሐላፊ ሆኖ እንዲሠራ ተመደበ። ለኹለት ዓመታት ካገለገለ በኋላ፥ ከሀገር እስከወጣበት ጊዜ ድረስ የማስታወቂያ ምክትል ሚኒስትር ሆኖ አገልግሏል።

አበርክቶ

መርዕድ በሥራ ላይ በነበረበት ጊዜ በተለያዩ ዓለም አቀፍና አህጉራዊ ስብሰባዎች ላይ ኢትዮጵያን በመወከል፣ አንዳንዴም በልኡካን ቡድን አባልነት ታድሟል። እ.ኤ.አ በ1990/91 መንግሥት ከሻዕቢያ ጋር የሰላም ውይይት በመጀመሪያ በአትላንታ ጆርጂያ በካርተር ማዕከል፣ ቀጥሎ ኹለተኛና ሦስተኛ ዙሮች በዋሽንግተንና በኬንያ ናይሮቢ በተካኼደበት ጊዜ የልኡካኑ ቃል አቀባይ ብቻ ሳይሆን የጋዜጠኞችን ቡድን በመምራት ተሳትፏል።
ከአለቆቹ ጋር በመነጋገር በኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ የCNN ሥርጭት አገልግሎት እንዲጀመር ያደረገውም እርሱ ነው። አዲስ ዘመን ዋና አዘጋጅ በነበረበት ጊዜ ታደሰ ውቤ ያዘጋጀው በነበረው የፍትሕ ዓምድ አማካኝነት በጊዜው አብዮታዊ ዘመቻ ኮሚቴ (አዘኮ) በሚባል ‘‘ተቋም’’ በየክፍለ ሀገሩ የታሰሩ ንጹሐን ዜጎች እንዲፈቱ አስችሏል።

በወቅቱ የግብፅ ፕሬዚዳንት አንዋር ሳዳት ወደ ሥልጣን የመጡበትን 10ኛ ዓመት በዓል ላይ ለመታደም ከሌሎች ባልደረቦች ጋር ወደ ካይሮ ያቀና ሲኾን፥ የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት መምሪያ ሐላፊ በነበረበት ጊዜም የአፍሪካ ዜና አገልግሎት PANA በአዲስ አበባ ሲቋቋም፣ በኋላም በሴኔጋል ዳካር ጽሕፈት ቤቱ በተደረገ ስብሰባ ተካፍሏል።

የመጀመሪያው ‘‘Council of minister of information of non-aligned countries (COMINACI)’’ ጉባኤ በህንድ ኒውዴልሂ ሲካኼድ ኢትዮጵያን በመወከል በስብሰባው ላይ ተካፍሏል። ይኸው ጉባኤ በኢንዶኒዥያ ጃካርታ ሲካኼድ የልኡካን ቡድኑ አባል በመሆን ታድሟል።

ከዚህ ባሻገር የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ወደ ቀለም በተሸጋገረበት ወቅት፥ ሕዝቡ በየቤቱ ባለቀለም ሥርጭቱን የሚመለከትበት ቴሌቪዥን ኢትዮጵያ አልነበራትም። እናም በመንግሥት አስቸኳይ ትእዛዝ ርዳታ ለመጠየቅ በዶ/ር ፈለቀ ገድለ ጊዮርጊስ በተመራው የልኡካ ቡድን አባል በመሆን ወደ ጃፓን ቶክዮ በመሄድ ከማሩቤኒ ኩባንያ በመቶዎች የሚቆጠሩ ባለቀለም ቴሌቪዥኖች በርዳታ አግኝተው ተመልሰዋል።

ከዚህ በተጨማሪ ከሱዳን ዜና አገልግሎት (SUNA)፣ ከጀርመን ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክና ከሌሎች አገሮች የዜና አገልግሎት ተቋሞች ጋር የኹለትዮሽ ስምምነት ተፈራርሟል።
መርዕድ ካገኛቸው ሽልማቶች መካከል ኢትዮጵያን ሄራልድ በነበረበት ጊዜ በአዲስ አበባ ስታዲየም በተካኼደው መርሐ ግብር ‘‘የዓመቱ ምርጥ ጋዜጠኛ’’ በመባል የምስክር ወረቀት አግኝቷል። በአዲስ ዘመን ዋና አዘጋጅ ሳለም ዋና መሥሪያ ቤቱ ቬንዙዌላ ካራካስ ከሚገኝ ‘‘ኢንተርናሽናል ጎልድ ሜርኩሪ’’ ከተባለ ተቋም ተሸልሟል።

መርዕድ ወደ ስደት

መርዕድ በቀለ በግንቦት ወር 1983 ዓ.ም. ሕወሐት አዲስ አበባ ሊገባ አንድ ቀን ሲቀረው ነበር፥ በድሬዳዋ አድርጎ ዲክል በምትባል አነስተኛ የጅቡቲ የጠረፍ ከተማ የደረሰው። የጅቡቲ የደኅንነት ሰዎች እርሱንና ከርሱ ጋር የነበሩትን ሌሎች ሦስት ኢትዮጵያውያን አሰሯቸው። ዲክል ከአንድ ዓመት ከአራት ወራት የስደት ኑሮ በኋላ እ.ኤ.አ በ1992 ወደ አሜሪካ በማቅናት ከባለቤቱ እና ከአዳጊ ልጆቹ ጋር ተገናኝቶ ኹለተኛውን የስደት ኑሮ ምዕራፍ “ሀ” ብሎ ጀመረ።

በ1996 እኤአ በአትላንታ በተካኼደው 26ኛ የኦሎምፒክ ውድድር ወቅት የኢትዮጵያ መንግሥት መርዕድ በቀለ የኢትዮጵያ ኦሎምፒክ ቡድን ባልደረባ (envoy) እንዲሆን አልስማማም በማለቱ፥ የዓለም አቀፉ አዘጋጅ ኮሚቴ የኡጋንዳ ኦሎምፒክ ቡድን ባልደረባ እንዲሆን ወሰነ። በዚኽ ሁኔታ መርዕድ በሙሉ የኦሎምፒክ ውድድር ላይ ከመታደሙ ባሻገር፥ በወቅቱ ኹለት የኡጋንዳ ቦክሰኞች ውድድራቸውን በማካኼድ ላይ እንዳሉ በወንጀል በመታሰራቸው በግሉ ዋስ በመሆን ከእስር እንዲፈቱና ውድድራቸውን እንዲጨርሱ ረድቷቸዋል።

እኤአ 2019/20 የዓለማችን ከፍተኛ ሥጋት የነበረው የኮሮና ቫይረስ (ኮቪድ 19) ወረርሽኝ በአገራችንም በተከሠተ ጊዜ ሥርጭቱን ለመግታትና ወገኖችን ለመርዳት በኢትዮጵያ መንግሥት የቀረበውን የድጋፍ ጥሪ ተቀብሎ በአበረከተው በጎ አስተዋፅኦ ከአምባሳደር ፍጹም አረጋ የምስጋና የምስክር ወረቀት ተሰጥቶታል፡፡

መርዕድ በጆርጂያ

መርዕድ በጆርጅያ ‘‘Department of juvenile justice’’ በሚባል መንግሥታዊ መሥሪያ ቤት ውስጥ በአይ. ቲ. ክፍል ለ13 ዓመታት አገልግሏል። ከዚህ በኋላ በአትላንታ ትልቁ የታክሲ ኩባንያ ‘የሎው ካብ’ yellow cub የአትላንታው ቅርንጫፍ ምክትል ፕሬዚዳንት ሆኖ ጡረታ እስከወጣበት እስከ 2020 ዓ.ም. በርካታ ኢትዮጵያውያንን የዩጋንዳ፣ የኬንያ፣ የሱዳንና የበርታ አረብ ሀገር ዜጎችን አገልግሏል።

ከዚህ ሌላ በአትላንታ መጀመሪያ አካባቢ ወርሃዊ ጋዜጣ ማሳተም ጀምሮ ነበር። ሆኖም ከጥቂት ዕትሞች በኋላ በተለያየ ምክንያት ሊቀጥል ባለመቻሉ ኅትመቱ ቆሟል።

እ.ኤ.አ በ1994 የማኅደረ አንድነት የሲቪክ ማኅበር በተቋቋመ በዓመቱ የሬዲዮ ፕሮግራም ሲከፈት ከሌሎች ባልደረቦቹ ጋር በመሆን የሬዲዮ ፕሮግራሙን ይዘት፣ ፖሊሲና የመሳሰሉትን በመጻፍ ከፍተኛ አስተዋፅኦ አበርክቷል።

መርዕድ የኢትዮጵያና የአሜሪካ ግንኙነት ይበልጥ እንዲጠናከርና የአሜሪካ ምክር ቤት ኢትዮጵያን የሚጎዳ ሕግ እንዳያወጣ የሚታገለው፥ በኢትዮጵያውያን የተቋቋመው የመጀመሪያው የlobyalot ድርጅት ‘‘American Ethiopian Public Affair Committee’’ የአትላንታ ቅርንጫፍ ሊቀመንበር ሆኖ በማገልገል ላይ ነው።

አቶ መርዕድ በቀለ ለ49 ዓመታት የትዳር አጋሩ ከሆነችው ከወይዘሮ ኤፍራት እንደሻው፤ኤፍራት ቤሉል መርዕድ እና ዮናታን መርዕድ የተባሉትን ልጆቻቸውን አፍርተዋል፡፡ ሶፍያ ካሊዬሮ ደግሞ የልጅ ልጃቸው ናት፡፡ ለቤተሰቡ መፅናናት ይሁን።

9 months ago

No replys yet!

Be the first to share what you think — your comment will appear here.