Logo
Getu Temesgen
ሁሉንም ነገር የመቃወም አባዜ ትናንትና ዛሬ...

( የሀብታሙ ደባሱ አዲሱ የግል ሀሳብ)
#ethiopia | የአንድ ሀገር ፖለቲካዊ ብስለት የሚለካው በእውቀትና በተጨባጭ መረጃ ላይ ተመስርቶ አማራጭ ሐሳቦችን ማቅረብ ሲቻል ነው። በኢትዮጵያ ፖለቲካዊ ምህዳር( Political Space) ግን፣ በተለይም በትውልዶች መካከል፣ ሁሉንም ነገር የመቃወም አባዜ (The Culture of Rejection) እና ከእውቀት ይልቅ ስሜትን የማስቀደም ዝንባሌ ጎልቶ ይታያል።ይህ ችግር የፖለቲካ ውይይት ጥራትን በማዳከም፣ለብሔራዊ ቀውሶችና ለልማት መደናቀፍ ዋና ምክንያት ሆኗል።

የትናንቱ ትውልድ ሸክም የመካረር ፖለቲካ የኢትዮጵያ የቀድሞ የፖለቲካ ትውልዶች ያደጉት "ዜሮ ድምር" (Zero-Sum Politics) በሚባል አስተሳሰብ ውስጥ ነው። የ"ሁሉንም መጣል" አባዜ ከንጉሱ ዘመን ጀምሮ እስከ ደርግና ኢሕሃዴግ ድረስ፣ የፖለቲካ ለውጥ የሚመጣው የቀድሞውን ሥርዓት ሙሉ በሙሉ በማፍረስና በመጣል እንጂ፣ መልካም ጎኖችን ወስዶ ስህተቶችን በማረም አልነበረም።ይህ አስተሳሰብ ትውልዱ ለድርድርና ለመግባባት ዝግጁ እንዳይሆን አድርጓል።

የእውቀት ውድቅት( Political Decay) የፖለቲካው ውይይት በጥላቻ፣ በመፈረጅና በሴራ( Conspiracy and sabotage) ላይ ሲመሠረት፣ የፖለቲካ ሳይንስ፣ ኢኮኖሚክስ እና ታሪክ ጥናቶች የሚሰጡት የተሰከነ እውቀት ተቀባይነት ያጣል። ለሀገር ማሰብ የሚቻለው የሰከነ ዕውቀት ሲኖር ብቻ ነው።ሥር-ነቀልነት (Radicalism) ለችግሮች የሚፈለገው መፍትሔ ሁልጊዜም ቢሆን ሥር-ነቀልና አብዮታዊ እንጂ፣ ቀስ በቀስ የሚመጣ ተቋማዊ ለውጥ አይሆንም። ይህ ደግሞ የፖለቲካው ሂደት ከባድና ደም አፋሳሽ እንዲሆን ያደርጋል።ለሀገራቸው በጎ ሀሳብ ያላቸው ዜጎች ባይተዋር እንዲሆኑ ያደርጋቸዋል ።

የዛሬው ትውልድ ተግዳሮት የስሜት ፖለቲካ እና የማኅበራዊ ሚዲያ ፍዘት የአሁኑ ትውልድ( My Generation ) አዲስ ተስፋ ይዞ ብቅ ቢልም፣ ከቀድሞው ትውልድ የወረሰውን "ሁሉንም የመቃወም አባዜ" በማኅበራዊ ሚዲያ አጠናክሮታል። የመረጃ ፍዘት (Information Overload and Apathy) በዘመናዊው ቴክኖሎጂ ምክንያት፣ በእውቀት ላይ የተመሠረተ ጥልቅ ትንተና ከመፈለግ ይልቅ፣ ፈጣንና ስሜት ቀስቃሽ መልዕክት ቀዳሚ ሆኗል። ይህም ለፖለቲካው ልሂቅ በስሜት የመመራት ዕድል ይፈጥራል።የእወደድ ባይነት (Anti-establishment and Anti-political sentiment) የፖለቲካ ስነ-ባህሪ እና ስነ-ልቦና መጎልበት ጥልቅ አሳቢዎች እና ሀገር ወዳድ ዜጎች ከመድረኩ እንዲወጡ ሁኗል ።

የ"መለያ" ፖለቲካ (Identity Politics) በአሁኑ ወቅት የፖለቲካ ውይይቶች በአብዛኛው በማንነት፣ በዘርና በቡድን ወገንተኝነት ላይ ያጠነጥናሉ። ይህ ሁኔታ የብሔራዊ ጥቅም፣ የኢኮኖሚ ፖሊሲና የዴሞክራሲ ተቋማት ግንባታን የመሳሰሉ እውነተኛ የእውቀት ውይይት የሚሹ ጉዳዮችን በአግድም እንዲወድቁ አድርጓል።

አካሄድን የመቃወም ስልት በተቃዋሚዎች በኩል የሚታየው በመንግስት የሚቀርበውን ማንኛውንም ሀሳብ መቃወም (የቀይ ባህር ተጋሪነት ፣ የወደብ አቅርቦት ፣የታላቁ ህዳሴ ግንባታ ፣ የኮሪደር ልማት የከተማ ሽግግር ጥያቄም ቢሆን)፣ ለዚህ አባዜ እንደ አንድ ማሳያ ነው።ጥያቄው ብሔራዊ እና ሀገራዊ ቢሆንም፣ የፖለቲካው ስሌት መንግስትን በመንቀፍ ላይ ያተኩራል።

በእውቀት ላይ የተመሰረተ ውይይት ጠላትነት የሚያስከትላቸው ጉዳቶች ይህ አባዜ በሀገር ግንባታና በዴሞክራሲ ሂደት ላይ ከባድ አሉታዊ ተፅዕኖ አለው ።የሀሳብ ጥራት ማጣት (Quality Deficiency) የፖለቲካው ምህዳር በስሜትና በወገንተኝነት ሲሞላ፣የፖሊሲ ውሳኔዎች ጥራት ይቀንሳል። መፍትሔዎች ከእውቀትና ከምርምር ይልቅ ከፖለቲካዊ ግፊት የመነጩ ይሆናሉ።
የመግባባት ማጣት ሁሉንም የመቃወም አባዜ የጋራ ራዕይና የሀገራዊ ስምምነት እንዳይፈጠር ያግዳል።የፖለቲካ ፓርቲዎች ገንቢ ክርክር ከማድረግ ይልቅ፣ አንዱ የሌላውን ህልውና የሚጠራጠርበት ሁኔታ ይፈጠራል።

ዓለም አቀፍ ጉዳዮች (እንደ አባይና ቀይ ባህር ያሉ) ወጥ የሆነ ብሔራዊ አቋም ሲፈልጉ፣ የውስጥ የፖለቲካ ኃይሎች በብዥታና ( Blurriness and Allover Rejections ) በመቃወም ሲጠመዱ፣ የኢትዮጵያ የድርድር አቅም ይዳከማል።

ኢትዮጵያ “ሁሉንም ነገር የመቃወም አባዜ” እና ከስሜት መራሽ ፖለቲካ ወጥታ ዘላቂ ልማትና ዴሞክራሲን ለመገንባት፣ ሁለቱም ትውልዶች የእውቀትን የበላይነት መቀበል ይኖርባቸዋል። የፖለቲካ ውይይቶች በመረጃ፣ በጥናትና በምክንያታዊነት ላይ መመሥረት ሲችሉ ብቻ ነው፣ የሀገሪቱ የፖለቲካ ምህዳር ከጥላቻና ከፍዘት ተላቆ ወደ ገንቢ ትብብር የሚሸጋገረው።

ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ጥቅም መሳካት የድርሻዬን እወጣለሁ !
#ethiopia

11 months ago

No replys yet!

Be the first to share what you think — your comment will appear here.