Logo
FastMereja
ብሔራዊ የቲቢ ጥምረት ተመሰረተ!
#fastmereja I በአለማችን ላይ በገዳይነታቸው ከፍተኛ ከሚባሉ በሽታዎች አንዱ የሆነው የቲቢ በሽታ በየጊዜው ስርጭቱን እየጨመረ አሳሳቢነቱም ከዕለት ዕለት እያደገ ይገኛል። እንደ አለም አቀፉ የጤና ድርጅት በኢትዮጵያ በዜጎች ላይ እስከ ሞት ከሚያደርሱ በሽታዎች ዝርዝር ውስጥ በቀዳሚነት ካስቀመጣቸው ተላላፊ በሽታዎች መካከል አንዱ የቲቢ በሽታ ነው።

በአሁኑ ወቅት ባለው ሪፖርት በኢትዮጵያ ከ19ሺህ በላይ ዜጎች በቲቢ በሽታ ይሞታሉ ስለሆነም ይህንን በዜጎች ላይ ከፍተኛ ጉዳት በማድረስ ላይ የሚገኘውን በሽታ ከተቻለ ከሀገራችን ማጥፋት ካልተቻለም የሚያደርሰውን ጉዳት መቀነስ ይቻል ዘንድ የሁሉንም ርብርብ ይፈልጋል። ይህንንም ጥረት ማሳካት የሚችል ብሔራዊ የቲቢ ጥምረት በላቭ ኢን አክሽን ኢትዮጵያ እና በጤና ሚንስቴር ትብብር በግሎባል ፈንድ ደጋፊነት በአዲስ አበባ ሳሬም ሆቴል የተለያዩ በቲቢ በሽታ ላይ በሀገራችን የሚሰሩ መንግስታዊና መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች በተገኙበት ተመስርቷል።

ጥምረቱ በሽታው በሀገራችን በሚገኙ ዜጎች ላይ የሚያደርሰውን ጉዳት ከመከላከል ባሻገር በጋራ በትብብር ለመስራት መደላድልን የሚፈጥር መሆኑን የገለፁት በጤና ሚኒስቴር የቲቢ የስጋ ደዌና የሳንባ በሽታ መከላከልና መቆጣጠር ዴስክ ሀላፊ የሆኑት አቶ ታዬ ለታ ለጥምረቱ ምስረታ መሳካት አስተወፅኦ ለነበራቸው አካላት ምስጋናቸውን አቅርበው በቀጣይ ሚንስቴር መስሪያ ቤቱ ከጥምረቱ ጎን በመሆን አስፈላጊውን ድጋፍ ያደርጋል ብለዋል።

ላቭ ኢን አክሽን ኢትዮጵያ ከግሎባል ፈንድ በተገኘ ድጋፍ ከጤና ሚንስቴር ጋር በመተባበር የቲቢ በሽታን በመከላከል ረገድ የማህበረሰቡን ግንዛቤ ማሳደግ የሚችሉ የተለያዩ ስራዎችን እየሰራ የሚገኝ ሲሆን ይህን ጥምረት ለማሳካት ከዚህ ቀደም በርካታ ጥረቶች ቢደረጉም ባለመሳካቱ ከፍተኛ ቁጭት ውስጥ መሆናቸውን የገለፁት የምስረታው ተሳታፊዎችና መስራቾች ዛሬ ምስረታው እውን ሆኖ በማየታቸው በሽታው እያደረሰ ያለውን ጉዳት ለመከላከል ያላቸውን ዕምነትና ተስፋ እንደጨመረላቸው ተናግረዋል።

11 months ago

No replys yet!

Be the first to share what you think — your comment will appear here.