Logo
YenetaTube
ለዓመታት በሪል አስቴቱ የተሰቃዩት ቤት ገዢዎች መንግሥት ይድረስልን እያሉ ነው

ፌም ሪል እስቴት ሀኮማል ኮንስትራክሽን ከተባለ ድርጅት ጋር በመሆን ከ2003 ዓ.ም ጀምሮ ፊጋ አካባቢ በሚገኝ ሳይቱ ቤት ሰርቶ ለማስረከብ 18 ወራት የጊዜ ገደብ እየሰጠ ለብዙዎች ቤት መሸጡ ይነገራል፡፡

ሆኖም ውሉንም ቃሉንም ሳያከብር ከ14 ዓመታት በላይ ደንበኞቹን እንዳስጠበቀ፣ለተደራራቢ ችግርና ስቃይ እንደዳረገ ቤት ገዢዎች ይናገራሉ፡፡
ሪል እስቴቱ በወቅቱ በሰራው አማላይ ማስታወቂያና በየቦታው ባሰማራቸው ሴልሶች ብዙ ቤት ገዢዎችን መሳብ ችሎ ነበር፡፡በማስታወቂያው ተማለው እና በያዙት ህጋዊ ውል ተማምነው ከ380 በላይ የሚሆኑ አባወራዎች ፊጋ አካባቢ እየተገነባ ያለውን ቤት እንደገዙ በቁጭት ያስታውሳሉ፡፡
በ18 ወራት ይጠናቀቃል የተባለው ቤት 10 ዓመታት ቢያልፈውም ቤት ሊሆን አልቻለም፡፡

ቤት ገዢዎች "ቤታችንን ስጡን" እያሉ በሪል እስቴቱ ቢሮ ቢንከራተቱም ሰሚ አላገኙም፡፡ችግሩ የባሰባቸው ከ2010 ዓ.ም ጀምሮ ቤታቸውን በራሳቸው ጨርሰው መግባት ጀመሩ፡፡አንዳቸው አንዳቸውን እያዩ የተጀመረውን ቤት ከሪል እስቴቱ በመረከብ አብዛኛው ቤት ገዢ ቤቱን በራሱ ተጨማሪ ወጪ ቤቱን አጠናቆ ገባ፣ሌላውም አከራየ፡፡

በፍርድ ቤት እና በሌላም ሙግትና ማስፈራሪያ የጥቂቶችን ቤት ሪል እስቴቱ ጨርሶ ያስረከበ ቢሆንም በዚህ ሁኔታ የማጠናቀቂያ ሥራው የተሰራለት ቤት ግን እንደነገሩና በወረደ ማቴርያል የተሰራ በመሆኑ ነዋሪዎችን ለበለጠ ኪሳራ በመዳረግ ከድጡ ወደ ማጡ ከተተ፡፡
ቤት ገዢዎቹ ከሪል አስቴቱ ቤታቸውን ተረክበው በራሳቸው አጠናቀው መግባት ቢችሉም አጠቃላይ ህንፃው እና የጋራ መገልገያ የሆኑ መሰረተ ልማቶች አልተሟሉም ነበር፡፡ መንገድ፣አጥር፣ሪል እስቴቱ አልሰራም፡፡መብራትና ውሃም ለኮንስትራክሽን ከገባ አንድ ቆጣሪ ላይ በፈረቃ ከመጠቀም ውጪ ለነዋሪዎች ምንም ዓይነት ቆጣሪ አላስገባም፡፡

ይሄ እና ሌሎች በርካታ ነገሮች የቤት ገዢዎች እዳ እና ችግር ሆኖ ለዘመናት መቀጠላቸውን ቤት ገዢዎቹ በምሬት ያስታውሳሉ፡፡

እስከ 2013 ዓ.ም ድረስ ሪል እስቴቱ ግንባታውን ባለማጠናቀቁ በግቢው ውስጥ ቢሮ ይዞ መብራትና ውሃን ከነዋሪው 45 ፐርሰንት እየሰበሰበ የአገልግሎት ክፍያውን እየፈፀመ የማስተዳደደር ሥራውን ይሰራ ነበር፡፡ሪል እስቴቱ በራሱ ፍቃድ 2013 ዓ.ም ግቢውን ለቆ ከወጣ በኋላ ነዋሪው በወረዳው አማክኝነት በህብረት ሥራ ማህበር በመደራጀት በጥቅምት 2014 ዓ.ም ህጋዊ እውቅና አገኝ፡፡በየጊዜው ገንዘብ በማዋጣት ቀስ በቀስ ሪል አስቴቱ ጭራሽ ያልሰራውንና አዝረክርኮ የተዋቸውን የአጥር፣የጥበቃ ማማ እና የውስጥ ለውስጥ መንገድ ሥራዎች እንደምንም ተብሎ ተሰራ፡፡ከዚህም ትልቁን ድርሻ የሚይዘው የውስጥ ለውስጥ የአስፋልት ሥራው ነው፡፡

የአስፋልት ሥራው ከፍተኛ ወገንዘብ፣ጉልበት እና ጊዜ የወሰደ ነበር፡፡
የቤት ባለቤቶች ከፍተኛ ወጪ እና ድክም አውጥተው የግልና የጋራ መኖሪያና አካባቢያቸውን ቢያሻሽሉም የውሃ እና የመብራት ጉዳይ እስከዛሬ ትልቅ ጫና ሲፈጥርባቸው ቆይቷል፡፡ሪል እስቴቱ ባለበት ከፍተኛ ድርጅታዊ ችግር እና ድክመት ምክንያት ካርታቸውን ሊሰጣቸው ባለመቻሉ የውሃና የመብራት ቆጣሪ በየቤታቸው ሊገባ አልቻለም፡፡በዚህም ምክንያት የውሃና የመብራት ፍጆታ ከአንድ ቆጣሪ ላይ በመሆኑ ፍጆታው ሲጨምር ማባዥውም ስለሚጨምር ታሪፉን ከፍ ያደርገዋል፡፡በዚህም ምክንያት ነዋሪዎቹ ለዓመታት ለከፍተኛ ወጪና ኪሳራ እየተዳረጉ ቀጥለዋል፡፡
ለስንት እዳና መከራ የዳረጋቸውን ሪል እስቴት ሳይከሱት የቆዩ ቢሆንም የካርታቸው ጉዳይ ግን የህልውና ጉዳይ ስለሆነ ክስ መስርተው ጉዳዩ በፍርድ ቤት እየታየ ነው፡፡
የቤት ገዢዎች ማህበር ህጋዊ መስፈርትና ቅድመ ሁኔታዎችን አሟልቶ የህብረት ሥራ ዕውቅና አግኝቶ በርካታ ቀሪ ሥራዎችንና የልማት ሥራዎችን ሲሰራ ቆይቷል፡፡አሁን ላይ ከፍተኛ ችግር የሆነባቸውን የመብራት እና የውሃ ቆጣሪ በከፍተኛ ውጣ ውረድ በማህበሩ በማስፈቀድ ችግራቸውን ሊቀርፉ ጫፍ ላይ በደረሱበት ወቅት ያልተጠበቀ ድንገተኛ መሰናክል ያጋጠማቸው መሆኑን ነዋሪዎቹ ለአቦል ሚዲያ ገልፀዋል፡፡ይህም ነዋሪው ውሃና መብራት እንዳያገኝ እና በፍርድ ቤት የተያዘው ካርታ የማግኝት ሂደት እንዲደናቀፍ ሆን ተብሎ የተሰራ ሴራ እንደሆነ ማረጋገጥ ችለናል ብለዋል፡፡
የነዋሪዎች ማህበር ህጋዊ መስፈርቱን አሟልቶ እንዲቋቋም እና ህጋዊ የማህበር እንቅስቃሴ እንዲያደርግ ዕውቅና የሰጠው የለሚኩራ ክ/ከተማ ወረዳ 9 ፅ/ቤት "ሪል እስቴቱ ከዕውቅናዬ ውጪ ተቋቁሟል ብሎ አመልክቷል" በማለት ምንም ዓይነት ማስጠንቀቂያ ሳይሰጥ ከነሐሴ 30/2017 ዓ.ም ጀምሮ የነዋሪዎቹን ማህበር አግዷል፡፡ ከተቋቋመ 4 ዓመታት በኋላ "የተደራጃችሁበት መንገድ ትክክል አይደለም" በማለት የወረዳው ህብረት ሥራ ጽ/ቤት የእግድ ደብዳቤ መፃፉ ከፍተኛ ግርምት የፈጠረባቸው መሆኑን ነዋሪዎቹ ገልፀዋል፡፡በዚህ ወቅት ይህ የተደረገው ነዋሪው ውሃና መብራት እንዳያገኝና በፍርድ ቤት የተያዘው ካርታ የማግኝት ሂደት እንዲደናቀፍ ሆን ተብሎ የተሰራ ሴራ መሆኑን ነዋሪዎቹ ለአቦል ሚዲያ አስረድተዋል፡፡
ይህ እግድ በተጻፈ ማግስት አስቀድሞ የተነገረው ጉደኛው ሪል እስቴት አይኑን በጨው አጥቦ "የማህበራችሁን ንብረት አስረክቡኝና እኔ ላስተዳድራችሁ" የሚል ደብዳቤ ይዞ በነዋሪዎች ግቢ ከተፍ ማለቱ ሌላው አስደናቂና አስቂኝ ነገር ሆኖባቸዋል፡፡ግቢው ውስጥ "ንብረት አለኝ" በሚል ሰበብ ሙሉ ለሙሉ የሚያስተዳድረውን የግቢውን ጥበቃ መሳሪያ በማድርግ "ከኔ ፍቃድ ውጪ ዕቃ መግባትም መውጣትም አይችልም" በማለት ለዓመታት ነዋሪዎች በኖሩበት ቤት የባለቤትነት ስሜት እንዳይሰማቸው ለማድረግ ሞክሯል፡፡ይህ እርምጃ በቀጣይ ያለ ውል እና ያለአግባብ ካርታ ለመውሰድ ክፈሉ ብሎ የጠየቀውንና ከውሉ ሁለት እጥፍ በላይ የሆነውን የግፍ ጥያቄ ካልከፈላችሁ አትገቡም ወደሚል ማምራቱ እንደሆነ ነዋሪዎቹ ተገንዝበዋል፡፡
"ወደው አይስቁ" እንደሚባለው ወረዳው እና ሪል እስቴቱ ተናበው በሰሩት ሥራ ነዋሪው የግርምትና የሀፍረት ሳቅ እየሳቀ አመት በዓሉን ለማሳለፍ ተገዷል፡፡

ማንም ኢትዮጵያዊ የጋራ ችግሮቹን በጋራ መፍትሄ ለማግኝት በማህበር፣በዕቁብና በመሳሰሉት ተደራጅቶ የመንቀሳቀስ የዜግነት መብት እንዳለው ይታወቃል፡፡በፊም ሪል እስቴት እና ሀኮማል በተባሉ እጀ ረጃጅም ድርጅቶች የከፍተኛ ችግርና ስቃይ ሰለባ የሆኑት ቤት ገዢዎች የደረሰባቸውን ችግርና መከራ በጋራ ለመቋቋምና ለመወጣት ሲሉ ነው ማህበር የመሰረቱት፡፡በብዙ ጥረትና ልፋት ባጠራቀሙት ገንዘብ፣የራሳቸውንና የልጆቻቸውን ፍላጎት ገድበውና ቆጥበው የገዙትና ብዙ ወጪ ያወጡበት ቤታቸውን፣ማረፊያና መጦሪያ ሳይሆናቸው ህግና ህዝብ ባለበት ሀገር ብዙ መከራና ግፍ እያደረሰባቸው ያለውን ህገወጥ ሪል እስቴት ለመቋቋም ሲሉ የመሰረቱት ማህበር መሆኑን ነው ነዋሪዎቹ የሚናገሩት፡፡የነዋሪዎች መዋጮና ሌሎች የውስጥ ሥርዓትና ደንብን እንዲያስጠብቅ በራሱ በወረዳው አማካኝነት እንዲቋቋም መደረጉ ተረስቶ ለህገወጡ ሪል እስቴት ከጠቀመ በሚል 380 አባውራን ለማስፈራራት "ማህበራችሁ ታግዷል" በሚል ከሚኖሩበት ወረዳ ደብዳቤ መፃፉ በነዋሪዎች ዘንድ ሀዘኔታን ፈጥሯል፡፡ነዋሪዎቹ ለዓመታት ከደረሰባቸው እና ካለፉበት ችግር አንፃር አጋጣሚና ሁኔታው ቢያስከፋቸውም ጉዳዩ ተራ የመልካም አስተዳደደር ችግር እንደሆነ ተገንዝበዋል፡፡ ለሚመለከተው መንግሥታዊ አካል በማሳወቅም የህዝብ እና የመንግሥት ጠላቶችን ለማጋለጥ አስፈላጊውን ሁሉ እንደሚያደርጉ ዘገባውን ላጠናከረው ለአቦል ሚዲያ አረጋግጠዋል፡፡

ህግ ያለበት ሀገር እንደመሆኑም ፍትህ በቅርብ እንደሚያገኙም ያላቸውን ጽኑ እምነት ገልፀዋል፡፡

9 months ago

No replys yet!

Be the first to share what you think — your comment will appear here.