Logo
Getu Temesgen
የግብረ ሰናዩ ላየንስ ክለብ ኢንተርናሽናል ኢትዮጵያ እና ሎሬት ዶ/ር ጥበበ የማነብርሃን
#ethiopia | COVID 19 - ኮሮና ከነጠቀን ባለአበርክቶዎች ኢትዮጵያውያን የጤና ዘርፉ ሻምፒዮኖች መካከል የላየንስ ክለብ አለም አቀፍ ማህበር ዐብይ ተልዕኮ ፈፃሚው ሎሬት ዶ/ር ጥበበ የማነብርሃን አይዘነጉም።

እኔ ሳውቃቸው ትኩረት በሚሹ የሃሩራማ በሽታዎች በተለይም የዓይን ማዝ (Trachoma) እና ጊኒ ዎርምን ጨምሮ በወባ መከላከል፥ቁጥጥር እና በሕክምና ከነበራቸው ጉልህ አስተዋጽኦ ጋር በተያያዘ ነው።

በተለይም በአማራ ክልል የትራኮማ (Trachoma) ስርጭት ከፍተኛ መሆኑን ተከትሎ ወባም (Malaria) እንዲሁ የሕብረተሰብ ጤና ስጋት ስለነበር ሁለቱን በሽታዎች ባቀናጀ በካርተር ሴንተር የሕብረተሰብ አቀፍ የጤና ቁጥጥር ፕሮጄክት (Mal-Tra)ጉልህ ድርሻ ነበራቸው።

በዚህ ረገድ ሎሬቱ ከቲ.ኤፍ. ግሎባል ሄልዝ (Taskforce for Global Health) የአፍሪካ ተጠሪ ከዶ/ር ተሾመ ገብሬ እና ከካርተር ሴንተር የኢትዮጵያ ተጠሪ ከዶ/ር ዘሪሁን ታደሰ ጋር በአጋርነት የከወኑትን አካትቼ በሰፊው እመለስበታለሁ።

ዛሬ ላይ ይህ የላየንስ ክለብ እንቅስቃሴ እንዴት ነው?

"እናገለግላለን" (We Serve) የሚል መሪ ቃልን አንግቦ ነው የተነሳው።
በሕብረተሰብ አገልግሎት ልቆ ለመገኘት ሰውን በጥልቅ የልብ ፍቅር መውደድ ይሻል።
በኢትዮጵያ ላየንስ ክለብ የግብረ ሰናይ ስራ ከጀመረ ከስድስት አስርት አመት በላይ ሆኖታል።

የቀድሞው የኢፌዲሪ ፕሬዚደንት ነፍስኄር ግርማ ወ/ጊዮርጊስ ከላየንስ ክለብ ኢትዮጵያ አምስት የቻርተር አባላት አንዱ ነበሩ።

ለዓይነ ስውርነት የሚዳርጉ በሽታዎችን ለምሳሌ በዓይን ማዝ (Trachoma)፥ በዓይን ሞራ ግርዶሽ Cataract)፥ በውሃ ወለድ መዘዝ የዓይነ ስውርነት (River blindness) በሽታዎች ለሚሰቃዩ ቅድሚያ በመስጠት በሕክምና ጥበብ እይታቸው እንዲመለስና ወደ አዲስ የተሻለ ሕይወት እንዲሸጋገሩ ማድረግ የግብረሰናይ ተልዕኮው ቀዳሚ ትኩረት ሆኖ ነው የቆየው።

እነኚህን በሽታዎች በዘላቂነት ለመከላከል ከእህት የላየንስ ክለቦች፥ ከካርተር ሴንተር፥ ከኢንተርናሽናል ትራኮማ ኢኒሺዪቲቭ፥ ከክሪስቶፌል ብላየንድነስ ሚሽን እና ከሌሎችም አጋሮች ጋር በመሆን የ2ኛ ደረጃ የዓይን ሕክምና አገልግሎትን በማስፋፋት የጤና ዘርፉን ሲደግፍ ቆይቷል።

በቀዶ ሕክምና ዜጎች በተለይ አቅመ ደካሞች የዓይን ብርሃንቸው ተነጥቀው እንዳይቀሩ ብሎም 2ኛ ደረጃ የዓይን ማዕከላት በባህርዳር፥ ደብረ ብርሃን፥ አርባምንጭና ጅግጅጋ መቋቋማቸውን የድርጅቱ ሰነድ ያመለክታል።

የመንግስት ሆስፒታሎችን አቅም በማሳደግ ረገድ ራስ ደስታ፥ ልዕልት ዘነበወርቅ ሆስፒታል፥ ራስ ደስታና ቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታሎች ሊጠቀሱ የሚችሉ ናቸው።

60 አመታትን ያስቆጠረው ላየንስ ክለብ በተጨማሪም በአዲስ አበባ ጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ግቢ የስኳር ሕሙማን ማዕከል እንዲቋቋምም አድርጓል።

ላየንስ ክለብ በኢትዮጵያ ሕብረተሰባዊ ምግባረ ሰናይ ተግባሩ እንዲጠናከር አባላት በማፍራት ያለበትን ውሱንነት በመቅረፍ የአባላት ማቀፍ እድሎችን ማስፋፋት እንደሚያሻ የክለቡ የኢትዮጵያ አመራሮች በአፅንኦት የሚያነሱት ነው።

ሎሬት ዶ/ር ጥበበ የማነ ብርሃን ኢትዮጵያ ካፈራቻቸው የቆዳ ሕክምና ስፔሻሊስቶች (Dermatologists) መካከል ተጠቃሽ ናቸው።

የቆዳ፣ የስጋ ደዌ፣ የአባላዘር፣ የትራኮማ እና ሌሎች ችግሮች የት የሃሩራማ በሽታዎች ቁጥጥር ላይ በተለይም በአለም አቀፍ ዲፕሎማሲ የሕብረተሰብ ጤና ትኩረት እንዲያገኝ ወሳኝ አካላትን በማግባባት (በ-advocacy) ሚናቸው ታላቅ እንደነበር ለዘርፉ ባለኝ ቅርበት ምስክር ነኝ።

ከሐኪምነታቸው በተጨማሪ የሀገር ሽማግሌ፣ እርዳታ አስተባባሪ፣ የፐብሊክ ዲፕሎማሲ ቡድን አባል፣ የእርቀ ሰላም ኮሚሽን አባል እና በብዙ የበጎ ፈቃደኝነት ስራ ሀገራቸውን አገልግለዋል።

ጥቅምት 22 ቀን በ1941 ዓ.ም በሐረርጌ ጠቅላይ ግዛት፣ ሐረር ከተማ የተወለዱት ዶ/ር ጥበበ ትምህርት የተከታተሉት በአዲስ አበባ ሽመልስ ሀብቴ ት/ቤት ነው።

አባታቸው ሻለቃ የማነብርሃን ወ/ሥላሴ በጦር ሰራዊቱ መኮንን ስለነበሩና የሚታየው ዲሲፕሊንና አለባበስ ከስካውት (Scout) ዲስፕሊንና አለባበስ ጋር የሚቀራረብ ስለነበር ጥበበ በዚያ ተማርከው የስካውት ክበብ አባል ሆነዋል።

ጥበበ 8ኛ ክፍልን ሳሉ የተቸገሩ ልጆችን በት/ቤቱ አካባቢ አይተው ከጓደኞቻቸው ጋር ተማከሩና ከድርሻ የኪስ ገንዘባቸው ቀንሰው በማጠራቀም ሞከሩና፤ ኋላም ‹‹የ10 ወንድማማቾች ማኅበር›› የተባለ ማኅበር መሰረቱ።

የጦር ሰራዊት እና የክብር ዘበኛ የሙዚቃ ቡድኖችን ጋብዘው ስራዎቻቸውን ለተማሪዎች እንዲያሳዩ በማድረግ ከዚያ የሚገኘውን ገንዘብ ለችግረኛ ተማሪዎቹ እንዲሰጥ መላ ዘየዱ።

ከዝግጅቶቹ ያገኙት ገንዘብ የተማሪዎቹን የምግብና የደንብ ልብስ ወጪ ለመሸፈን አስቻላቸው።

ይህ የበጎ ፈቃደኝነት ጥረት ተጠናክሮ ከተደገፉት ተማሪዎች ውስጥ እስከ ዩኒቨርሲቲ ተምረውና ትልቅ ደረጃ ደርሰው በምዕራባውያኑ ባህር ማዶ ሀገራት የሚኖሩም አሉ።

ጥበበ በልጅነታቸው ዲፕሎማት የመሆን ምኞት የነበራቸው ቢሆንም እናታቸው ታመው ሆስፒታል የገቡበት አጋጣሚ ግን የጥበበን ፍላጎትና የሕይወት መንገድ ቀየረው።

እናታቸው ታመው አሁን ጦ/ኃይሎች ሆስፒታል ከሚባለው የልዕልት ፀሐይ መታሰቢያ ሆስፒታል ገቡ።

የእናታቸውን ቀዶ ሕክምና በስኬት ያከናወኑትን ኢትዮጵያውያን ዶክተሮችን (ፕሮፌሰር አስራት ወልደየስን፣ ፕሮፌሰር ታዬ መኩሪያንና ሌሎች ሐኪሞችን) ሲመለከቱ ሐኪም የመሆን ምኞት አሸነፋቸውና ሃሳብ ቀየሩ።

ከዚያም የሩስያ ወዳጅነት ማኅበር የትምህርት እድል ሲሰጥ ጥበበ እድሉን አግኝተው ወደ ሩሲያ ሄደው ለ6 አመታትየሩስያ ቋንቋና የሕክምና ትምህርትን ተምረው በማዕረግ አጠናቀዋል።

በቆዳ ሕክምና የ2ኛ እና የ3ኛ ዲግሪያቸውንም አገኙ፤ የአለም አቀፍ የፖለቲካ ሳይንስ ትምህርትን ማከላቸው ለኋላው ዲፕሎማሲን ለሚሻው የጤና ልማት የማግባባት አድቮኬሲ ስራ ብዙ እንዳገዛቸው መገመት ይቻላል።

ዶ/ር ጥበበ ከ1972 እስከ 1985 ዓ.ም ድረስ በሉቮቭ ስቴት ዩኒቨርሲቲ ሪፈራል ሆስፒታል ውስጥ በአማካሪ ስፔሻሊስትነትና ተባባሪ ፕሮፌሰርነትም አገልግለዋል።

ወደ ኢትዮጵያ ተመልሰው የመላው አፍሪካ የሥጋ ደዌ ማገገሚያና ስልጠና ማዕከል (All Africa Leprosy Rehabilitation & Training Center - ALeRT) ዋና የቆዳ ሐኪምና የክፍሉም ኃላፊ ሆነው ሰርተዋል።

የዶ/ር ጥበበ ከተሳተፉባቸው ዋነኛ ጉዳዮች አንዱ የላየንስ ክለብ ኢንተርናሽናል ፋውንዴሽን (Lions Clubs Inter­national) ነው።

በዚህ ክለብ ተሳትፏቸው በተለይ አፍለኛ የዓይን ማዝ ቁጥጥር (control of active trachoma) እና የዓይን ሞራ ግርዶሽ (cataracts) ሕክምና እንዲሁም የዓይን ቆብ ቀዶ ሕክምና (trachomatus trichiasis) ላይ ሳይጠቀሱ አይታለፍም።

ትኩረት ከሚሹ የሃሩራማ በሽታዎች አንዱ የጊኒ ወርም በሽታ ሲሆን ከጊኒ በመወገዱ የኢትዮጵያ ዎርም ተብሎ ስም ለውጥ እንዳይደረግ ያሰጋል።

እናም ይህን በሽታ ለማጥፋት በተያዘ ፕሮግራም የበጎ ፈቃድ አምባሳደርም ሆነው አገልግለዋል።

ሎሬት ዶክተር ጥበበ የሎሬትነት ማዕረግን ያገኙት ከሰሜን አሜሪካ ነው።
የዓለም ሎሬቱ ዶ/ር ጥበበ በርካታ ሽልማቶችን አግኝተዋል። እንደውም በአንድ የሽልማት ሁነት ላይ እንዲህ እል:-
"… ማንም ሰው የትም አገር ሄዶ ሽልማት ሊሸለም ይችላል፤ በአገሩ የተሸለመው ሽልማት ግን ታላቁ ነው ብዬ አምናለሁ። ለእኔ ትልቁ ሽልማቴ በ2002 ዓ.ም ባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የሰጠኝ የክብር ዶክትሬት ነው"።

በዓለም የጤና ድርጅት፣ በዓለም ባንክ፣ በብሪታኒያና አሜሪካ የቆዳ ሕክምና ማህበርና አካዳሚ፣በዓለም አቀፍ የቆዳ ሕክምና ማኅበር፣ በአፍሪካ የኤድስ (AIDS) መከላከል መርሃ ግብር፣ በዊልያም ዱ ቦይስ የአፍሮ-አሜሪካ የምርምር ተቋም እንዲሁም በሌሎች ተቋማትም አገልግለዋል።

ከሩሲያው ፕሬዝደንት ቩላድሚር ፑቲን ዘንድ ለሩሲያም ሆነ ለቀሪው ዓለም መልካም ተግባር ላከናወኑ ሰዎች የሚሰጠውን ከፍተኛ ሽልማት ተበርክቶላቸዋል።

ከ39ኛው የአሜሪካ ፕሬዝደንት ጂሚ ካርተር ጋር በ-Carter Cen­ter እና ሎሬቱ ከፍተኛ አመራር በነበሩበት የላየንስ ክለብ ኢንተርናሽናል ፋውንዴሽን ጥምረት አማካይነት ሰፊ የጤና ልማት ስራ ስለመከናወኑ በብዙ የመስክ ስራዎች ራሴም ተገኝቼ መሬት የነካ ሃቅ መሆኑን ታዝቤያለሁ።

‹‹ገና ላሳካው ፈልጌ ያልፈጸምኩት ብዙ ቀሪ ክንውኖች አሉኝ›› ሲሉ የነበሩት ሎሬት ዶ/ር ጥበበ ዓለምን ባርበደበደው ኮሮና በሽታ የካቲት 13 ቀን 2013 ዓ.ም በ72 ዓመታቸው ከዚህ ዓለም ድካም አርፈዋል።

በቺካጎ ከተማ የዛሬ110 አመት ገደማ ላየንስ ክለብ የተመሰረተው ሲሆን 1.4 ሚሊዮን አባላትን በማቀፍ በ183 ሀገራት ውስጥ ከ43,300 ክለቦች በላይ በ714 የአገልግሎት ማስተባበሪያ አውራጃዎች ተቀናጅቶ እየተመራ ነው።

ክለቦቹ ከመደበኛ ማህበራዊ ስብስብነት በላይ አባላቱ ተልኳቸው ጊዜያቸውን፥ እውቀታቸውንና ሃብታቸውን አቀናጅተው ለበጎ ምግባር በማዋል እርዳታናድጋፍ የሚሹትን የሕብረተሰብ ክፍሎች መታደግ ነው።
........
(Composed by:- Eshetu Geletu - Public health advocate & Champion of NTDs Control)

9 months ago

No replys yet!

Be the first to share what you think — your comment will appear here.