29 days ago
ከውጭ ቱሪስቶች ገቢ ጥገኝነት ለመውጣት የደብረ ሮሓ ቅዱስ ላሊበላ ገዳም በዘላቂ የልማት ሥራዎች ላይ ይገኛል
#ethiopia | በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ሥር የሚገኘው ታሪካዊው የደብረ ሮሓ ቅዱስ ላሊበላ ገዳም ዓለም አቀፍ ቅርስ አስተዳደር ጽሕፈት ቤት፣ ከውጭ አገር ቱሪስቶች በሚገኝ ገቢ ላይ ብቻ ጥገኛ ላለመሆን፣ ራሱን በዘላቂነት ለማጠናከር እና የተጣለበትን መንፈሳዊና ማኅበራዊ ኃላፊነት ለመወጣት በርካታ የልማት ፕሮጀክቶችን በመተግበር ላይ ይገኛል።
ይህ የልማት እንቅስቃሴ ገዳሙ በኢኮኖሚ ጥንካሬ ከመደገፉ ባሻገር፣ ለአካባቢው ማኅበረሰብ እና ለካህናቱ ምቹ አገልግሎትን መስጠት የሚያስችል አዲስ ምዕራፍ ከፍቷል።
የገዳሙን የልማትና የመሠረተ ልማት እንቅስቃሴዎች በተመለከተ የጽሕፈት ቤቱ የግንባታ ክፍል ኃላፊ ዲያቆን ታደሰ ዓለሙ እንዳብራሩት፣ ገዳሙ የራሱን ገቢ በዘላቂነት ለማሳደግና አገልግሎቱን በአንድ ጣራ ሥር ለማጠቃለል የሚያስችሉ በርካታ የግንባታ ሥራዎችን አከናውኗል።
ከእነዚህም መካከል በ900 ካሬ ሜትር ቦታ ላይ ያረፈውና 24 ክፍሎች ያሉት አዲሱ የአስተዳደር ሕንፃ ተጣቃሽ ነው። ይህ ሕንፃ ተገልጋዮች ከአንድ ቦታ ወደ ሌላ ቦታ ይንከራተቱበት የነበረውን አሠራር ያስቀረ ሲሆን፣ አጠቃላይ የካህናትና የአስተዳደር አገልግሎቶችን በአንድ ጣራ ሥር በማድረግ የአገልግሎት ክፍተቱን በከፍተኛ ደረጃ ቀንሷል።
ከዚህ በተጨማሪ በቅርቡ ተጠናቆ ለባንኮችና ለተለያዩ የንግድ ተቋማት ማከራየት የተጀመረው በቅዱስ ላሊበላ ከተማ የሚገኘው 14 ክፍሎች ያሉት ነባር የG+2 ሕንፃ፣ እንዲሁም በከተማው አደባባይ አካባቢ በ500 ካሬ ሜትር ቦታ ላይ እየተገነባ የሚገኘው የG+4 ሁለገብ ሕንፃ የገዳሙን ገቢ በእጅጉ ያሳድጋሉ ተብለው ይጠበቃሉ።
ገዳሙ ከሕንፃዎች በተጨማሪ እንደ እክስካቫተር፣ ሲኖትራክና ዘመናዊ የእንግዶች መቀበያ ተሽከርካሪዎችን በመግዛት ለኮንስትራክሽን ሥራዎችና ለአካባቢው ልማት በማከራየት ተጨማሪ ገቢ እያስገኘ ይገኛል።
ወደፊትም ከከተማው 2 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በሚገኘው ገዳመ ቆሮንቶስ በተባለ ቦታ ለእናቶች መነኮሳት መኖሪያ የሚሆን ግንባታ እና በ20 ሺህ ካሬ ሜትር ቦታ ላይ የሃይማኖት ትምህርትን የሚያስፋፋ የ«መካነ ልዕልት» ፕሮጀክት ታቅደው በሂደት ላይ ይገኛሉ።
በሌላ በኩል፣ የጽሕፈት ቤቱ የምሕንድስና ክፍል ኃላፊ ኢንጂነር ጌቱ ዳኛው በበኩላቸው በሰባት ወይራ ሆቴል አካባቢ የቅርሱን ተፈጥሯዊ ገጽታ ሳይጋፉ የሚከናወኑ የገበያ ማዕከላት ግንባታዎችን ሂደት ገልጸዋል። የመጀመሪያው ዙር ሕንፃ ተጠናቆ አገልግሎት መስጠት የጀመረ ሲሆን፣ በቀጣይም ከተፈጥሮ ጋር የተጣጣሙ ከG+1 እስከ G+4 እንዲሁም G+2 የሆኑ ደረጃቸውን የጠበቁ የገበያ ማዕከሎችን የመገንባት ሥራ ይከናወናል።
አሁን ባለው ሁኔታ አዲሱ የቢሮ ቦታ ተጠናቆ አገልግሎት በመስጠቱ፣ ነባሩ ቢሮ 95 በመቶ ያህል ወደ ገበያ ማዕከልነት የመቀየር ሥራው ተጠናቆ ለሥራ ዝግጁ ሆኗል።
በተመሳሳይ ዘርፍ፣ በጽሕፈት ቤቱ ስር የሚተዳደረው የቤተ አብርሃም ሆቴል ዋና ሥራ አስኪያጅ ዲያቆን አበበ ዓለሙ እንደተናገሩት፣ ሆቴሉ ከ1960ዎቹ ዓ.ም ጀምሮ በገዳሙ አባቶች ተጋድሎና ጥረት የተመሠረተ ታሪካዊ ተቋም ሲሆን፣ በአሁኑ ወቅት 49 ክፍሎችን በማደራጀት ለአገር ውስጥና ለውጭ አገር እንግዶች ጥራት ያለው አገልግሎት በመስጠት ላይ ይገኛል።
ሆቴሉ ለአገር ውስጥና ለውጭ አገር ቱሪስቶች የሚሰጣቸውን አገልግሎቶች በተገቢውና ፍትሃዊ በሆነ የዋጋ ተመን የሚያቀርብ ሲሆን፣ የአካባቢውን እውነተኛ ባህላዊ እሴቶች፣ እንግዳ ተቀባይነትና ታሪካዊ ቅርሶች ጠብቆ ማቆየት ላይ አተኩሮ እየሰራ ይገኛል።
በሆቴሉ የሚሰጡ መስተንግዶዎች የቅዱስ ላሊበላንና የአካባቢውን ባህላዊ ወግ መሰረት ያደረጉ በመሆናቸው፣ ደንበኞች ከዘመናዊ አሰራር ጋር የተጣጣመና ሰላማዊ ድባብ ያለው ማረፊያ እንዲያገኙ ስራዎች መሠራታቸውን ዲያቆን አበበ አብራርተዋል።
ከዚህ ጎን ለጎን ገዳሙ ገቢ ማግኘት ላይ ብቻ ሳይሆን ትውልድን በማነፅ ላይ በማተኮር፣ ከኬጂ እስከ 8ኛ ክፍል የሚያስተምረውን «ኬርዮና» ትምህርት ቤትን ገንብቶ ለማህበረሰቡ በተመጣጣኝ ዋጋ አገልግሎት እየሰጠ ይገኛል። እንዲሁም አራት ጉባኤያትን ያቀፈውን ጥንታዊ የአብነት ትምህርት ቤት በዘመናዊ መንገድ በማደራጀት የብራና ጽሑፍንና የዜማ ትምህርቶችን ለአካባቢው ወጣቶችና ከሌሎች አካባቢዎች ለሚመጡ ተማሪዎች እያስተማረ ይገኛል።
በአጠቃላይ፣ የቅዱስ ላሊበላ ገዳም ዘርፈ ብዙ የልማት፣ የኢኮኖሚና የመንፈሳዊ ትምህርት እንቅስቃሴዎች የገዳሙን ቀጣይነት ያለው ዕድገት የሚያረጋግጡ ከመሆናቸውም በላይ ለትውልድ የሚሻገር ትልቅ መሠረት እየጣሉ ይገኛሉ።
(የደብረ ሮሓ ቅዱስ ላሊበላ ገዳም ዓለም አቀፍ ቅርስ አስተዳደር ጽሕፈት ቤት የአብያተ ክርስቲያናቱን ቅርስ ጥገና ሂደትና ተጨማሪ መረጃዎችን በቀጣይ ክፍል ይዘን እንቀርባለን።)
በጌትነት ተመስገን
#lalibela #debrerohalalibela #ethiopia #sustainabledevelopment #lalibelamonasteries #tourismethiopia #visitethiopia #beteabrahamhotel #economicsustainability

Comments